የቀድሞ የማዕከላዊ አዛዥ ኮማንደር ረታ በፖሊስ እየተፈለጉ ነው

0
727

በተለምዶ ማዕከላዊ ተብሎ ይጠራ በነበረው የፌደራል ፖሊስ የወልጀል ምርመራ ቢሮ አዛዥና በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር የነበሩት ረታ ተስፋዬ በሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ተጠርጥረው በሕግ እየተፈለጉ እንደሆነ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ከሥራ ኀላፊነታቸው ቢነሱም ለረጅም ግዜ በአዲስ አበባ ከተማ የነበሩት ረታ ከወራት በፊት ከአገር እንደወጡ ሲነገር የቆየ ሲሆን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ለኢትዮጵያ ተላልፈው እንዲሰጡ ከሚገኙበት አገር ጋር ውይይት ላይ እንደሆነ በፌዴራል ዐቃቤ ሕግ የሚገኙ ምንጮች ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ የሚገኙበትን አገር ከጽሕፈት ቤቱ ለማረጋገጥ ብትሞክርም ሊሳካ አልቻለም። ይሁን እንጂ በዐቃቤ ሕግ ውስጥ የሚገኙ ምንጮች እንደገለጹት በጀርመን ወይም አሜሪካ ውስጥ ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠረጠር ተናግረዋል።
የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ኀላፊ የነበሩት ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ በ26 የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የሥራ ኀላፊዎችና ሠራተኞች ላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ መመሥረቱ ይታወሳል። ይሁን እንጂ ዐቃቤ ሕግ ኮማንደር ረታን በክሱ ላይ ለማካተት የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ቢሰበስብም አገር ውስጥ ባለመሆናቸው ይህንን ማድረግ አለመቻሉን ምንጮቹ ጨምረው ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የቴክኒክና መረጃ ዋና መምሪያ ምክትል ኀላፊ የነበሩት ሃሺም ቶፊቅ (ዶ/ር) በሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ተጠርጥረው የነበረ ቢሆንም ክስ አልተመሠረተባቸውም። ነገር ግን ባለቤታቸው ዊዳት አሕመድ እና ሰሚራ አሕመድ የተባሉ ሌላ ሰው ምክትል ኀላፊውን በማሸሽና ሰነድ በማጥፋት ተጠርጥረው ነበር።

ዐቃቤ ሕግ በወንጀል መርማሪዎች፣ በማረሚያ ቤት የሥራ ኀላፊዎች ላይ እንዲሁም በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የሥራ ኀላፊዎችና ሠራተኞች ላይ በሦስት የተለያዩ መዝገቦች ክስ መመሥረቱ ይታወሳል። በክሶቹ ውስጥ 22ቱ ተከሳሾች በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን፥ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ አጽብሃ ግደይ፣ አሰፋ በላይ እና ሽሻይ ልዑል በተባሉ የቀድሞ የአገልግሎቱ የሥራ ኀላፊዎች ላይ በሌሉበት ሚያዚያ 29/2011 በከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ክስ መመሥረቱ ይታወሳል።

በእነዚህ የክስ መዝገቦች ላይ ረታ ተስፋዬ እንዲሁም ሃሺም ቶፊቅ አለመካተታቸውን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here