በኦሮሚያ፣ በደቡብና በሶማሌ ክልል የአተት በሽታ ገባ

0
628

በኦሮሚያ ክልል ጭሮ ወረዳ 15 ሰዎች፣ በዴሳ ከተማ 2 ሰዎች፤ ኦዳ ቡልቱ 68፣ በሶማሌ ክልል ቦቆሎማዬ ወረዳ 33 ሰዎች፣ በደቡብ ክልል በአርባ ምንጭ ዞን በመለኮዛ ወረዳ 70 ሰዎች በአተት በሽታ መያዛቸውን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

በተጨማሪም በጭሮ እና በኦዳ ቦልቱ የተከሰተውን የአተት ወረርሽኝ ምልክት ምርመራ በአዳማ ሆስፒታል የተደረገ ሲሆን፣ ውጤቱም የቪብሮ ኮሌራ ባክቴሪያ አለመኖሩ ሲረጋገጥ ኤሮሞናስ የተባለ ባክቴሪያ መከሰቱን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር በየነ ሞገስ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

በደቡብ ክልል በአርባ ምንጭ ዞን በመለኮዛ ወረዳ ከ70 በላይ ሰዎች አጣዳፊ ተቅማጥ መያዛቸውንና የ2 ሰዎች ሕይወት ማለፉም ታውቋል። በአማራ ክልል በአጠቃላይ በአተት በሽታ 190 ሰዎች የተያዙ ሲሆን 14 ሰዎች ከበሽታው ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው አልፏል።

ከላይ ለተጠቀሱት ክልሎች አጎራባች በሆኑ ወረዳዎች የበሽታው ምልክቶች ባይታዩም የቅኝት ሥራዎች ተጠናክሮ እየተሠራ መሆኑን ምክትል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በአንድ ወር ውስጥ በአማራ፣ ትግራይ፣ ሶማሌ፣ ሐረሪ፣ ቤኒሻንገል ጉምዝ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 85 ወረዳዎች የአተት፣ እከክ፣ የሆድ ትላትል፣ የሳምባ ምች፣ ተቅማጥ፣ የዓይን ሕመምና ከፍተኛ ትኩሳት ያለባቸው በአጠቃላይ ከ51 ሺሕ 786 በላይ ሰዎች የሕክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን ታውቋል።

ወረርሽኙን መቆጣጠር እንዲቻል በተጨማሪ በአማራ ክልል በአበርጌሌ፣ በጠለምትና በየዳ ወረዳዎች 651 ሺሕ የውሃ ማከሚያዎች ተልኳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 30 ግንቦት 24 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here