“ፊልም በፍላሽ”

0
767

እዮብ ሀብታሙ በኻያዎቹ መጨረሻ የዕድሜ ክልል የሚገኝ ወጣት ነው። ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት እሱን ጨምሮ ከሌሎች ኹለት ወንድሞቹ ጋር ነበር የውጭ አገር ፊልሞችን ለተጠቃሚ በኹለተኛ ደረጃ ማጠራቀሚያ መሣሪያ (secondary storage device) ፍላሽ ዲስክ፣ ኤክስተርናል ሃርድ ዲስክ ላይ በመጫን መሸጥ የጀመሩት። በጊዜው ማንም ሥራውን የሚያውቀው ባለመኖሩ ተጠቃሚ ማግኘትም ጭንቅ እንደነበር እዮብ ያስታውሳል።

እዮብ እንደሚናገረው፥ እንዳሁኑ የውጭ አገራት ፊልሞች በየቦታው በፍላሽ በማይገኙበት ጊዜ ሰዎች ፊልሞችን የኢንተርኔት አገልግሎት በሚገኝባቸው ቦታዎች በመሔድ ከድረ ገፆች ላይ ያወርዷቸው ወይም በቀጥታ ይመለከቱ እንደነበር ይናገራል።

“ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን ጠንካራ የኢንተርኔት ፍጥነት በሚገኝባቸው ቦታዎች ወይም መሥሪያ ቤቶች ካልሆነ በሌላ ቦታ የማይሞከር ነበር” ይላል። ከተማዋ ውስጥ በቀደሙት ጊዜያት የውጭ አገራት ፊልሞችን ለማግኘት ሰዎች በሲዲ፤ ከዛም ቀደም ባሉት ዓመታት ከሆነ ደግሞ በቪዲዮ ካሴት እየተከራዩ ይመለከቱ እንደነበር የሚታወስ እንደነበር እዮብ ይናገራል። ታዲያ ከቴክኖሎጂ ጋር አብረው በመዘመን እዮብና ወንድሞቹ በ2004 ላይ የውጭ አገራት ፊልሞችን ለተጠቃሚ በፍላሽ ወይም በሐርድ ዲስክ በመስጠት ገንዘብ መሥራት እንደሚችሉ አስበው ወደ ሥራ ገቡ።

“መጀመሪያ ላይ የነበረው የደምበኛ መጥፋት ትንሽ አስደንግጦን ነበር” ይላል እዮብ ንግዱን የጀመሩበትን የመጀመሪያ ጊዜያት መለስ ብሎ ሲያስታውስ። ይሁን እንጂ ሥራውን በጀመሩ ሦስት ወራት ባልሞላ ጊዜያት ውስጥ የእነእዮብ ሥራ ተቀባይነትን አግኝቶ በርካታ ደምበኞችን ማፍራት ቻሉ። በፈረንሳይኛ ቋንቋ ሦስት የሚል ትርጓሜ ያለው ‘ትሪዮስ’ በሚል ሥያሜ የጀመሩት የውጭ አገራት ፊልሞችን በፍላሽ እና በሌሎች ማጠራቀሚያ መሣሪያዎች የመሸጥ ንግድ ሥሙ በመላው አዲስ አበባ ተሰራጭቶ ከእነእዮብ የወጡ ፊልሞች ከተማው ውስጥ በመዘዋወር ቀጠሉ።

“ጎተራ አጎና ሲኒማ አካባቢ ነበር መጀመሪያ የጀመርነው” የሚለው እዮብ, አሁን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች አራት ቅርንጫፎችን ከፍተዋል። ትላልቅ ሕንፃዎች ላይ ቢሮዎችን በመከራየት ንግዳቸውን የሚያካሒዱት እዮብና ወንድሞቹ በየቀኑ ገቢያቸው እያደገላቸው እንደመጣ ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።

“አሁን ላይ ሳስበው የሚገርመኝ በመጀመሪያ ደረጃ ሐሳቡን ስናመጣው እና ስንጀምረው እንደቀልድ ነበር” የሚለው እዮብ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን “እውነት እውነት አይመስለኝም” ሲል ይናገራል። “አሁን ከደረስንበት ደረጃ ባለፈ በከተማው ውስጥ ለሚታዩት ፊልሞችን በፍላሽ እና መሰል መሣሪያዎች በመጫን ለሚሠራው ንግድ በር ከፋች መሆናችን ያስደስተኛል” ሲል ይናገራል።

አዲስ ማለዳ እዮብ በዋናነት በሚያስተዳድረው ቦሌ መድኀኒ ዓለም አካባቢ ወደ ሚገኘው የትሪዮስ ቅርንጫፍ ጎራ ባለችበት ወቅት በርካታ ደምበኞች የውጭ አገራት ፊልሞችንና የቴሌቪዥን ተከታታይ ሾዎችን ከፍለው ለመውሰድ ወረፋ ይዘው ተቀምጠው አይታለች።

አሁን ስላለው ገቢም እዮብ ለአዲስ ማለዳ አልሸሸገም። “በዚህኛው ቅርንጫፍ ብቻ በቀን ከአንድ ሺሕ ብር በላይ አስገባለው” ይላል እዮብ።

እዮብ በሚያስተዳድራት ትሪዮስ ቦሌ መድኀኒ ዓለም ቅርንጫፍ አንድ ወጥ የእንግሊዝኛ ፊልም በሦስት ብር የሚሸጥ ሲሆን፤ ተከታታይ የቴሌቪዝን ሾዎች ደግሞ በክፍል አንድ ብር ዋጋ ተተምኖላቸዋል። “ይህኛው ቅርንጫፍ ከሌሎቹ አንፃር ሲታይ ገቢው ደከም ያለ ቢሆንም በቀን በአማካኝ እስከ 2 መቶ ሰዎችን አስተናግዳለሁ፤ ከእያንዳንዱም ሰው ሃምሳ ብር እና ከዛ በላይ በአማካኝ ገቢ አገኛለሁ” ሲልም ይናገራል።

አሁን በከተማችን በስፋት እና በተለያዩ ዘዴዎች የውጭ አገራት ፊልሞች እና ተከታታይ የቴሌቪዥን ሾዎች ይሸጣሉ ይከፋፈላሉ። የእዮብና ወንድሞቹ በአጋጣሚ የፈጠሩት ንግድ ዘርፍ በአዲስ አበባ በአራቱም ማዕዘን እንደ አሸን ለፈላው የንግድ ዘርፍ ፈር ቀዳጅ መሆናቸውን በኩራትና በደስታ ስሜት ተናግሯል። ይህንን ንግድ አንድ እርምጃ ያራመደው ደግሞ ‘ሰዊፍት ሚዲያ’ ነው። ይህ ድርጅት ቢሮ መከራየት ሳያሻው፣ የቢሮ ወንበርና ጠረጴዛ መግዛት ሳያስፈልገው የአንድ ሕንፃን ኮሪደር በመጠቀም እንደ አውቶማቲክ የገንዘብ መክፈያ ማሽን ዓይነት (vending machine) በመትከል ተጠቃሚዎች የሚፈልጉትን ፊልም ርዕስ ፊት ለፊት በሚታየው የኮምፒውተር ሰሌዳ ላይ በመፃፍና የሚጠየቁትን ገንዘብ በመክፈል የሚገለገሉበትን ዘዴ የፈጠረበት ነው። በዚህ ዘመን አመጣሽ ዘዴ ለመጠቀም እንዲያው ከማሽኑ ዘመናዊነት ጋር አልግባባ ብለው ግራ እንዳይጋቡ ስዊፍት ሚዲያ አጋዥ ሠራተኛ በአቅራቢያዎ አስቀምጦሎዎታል። የዚህ ዓይነት ዘመን አመጣሽ መሣሪያ አሁን በተለይም ደግሞ ቦሌ አካባቢ ትላልቅ ሕንፃዎች መግቢያ ላይ በስፋት ይሰተዋላል።

አዲስ ማለዳ ባደረገችው ቅኝት የስዊፍት ሚዲያ ንብረት በሆኑት ማሽኖች አካባቢ ኹለትና ሦስት ሰዎች በተራ አገልግሎት ሲያገኙ ታዝባ የተገልጋዮችንም አስተያየት ተቀብላለች።

ቦሌ መድኀኒ ዓለም አቢሲኒያ ሕንፃ ደጅ ላይ ያገኘነው ኒቆዲሞስ ኃይሌ በሳምንት ኹለት ቀን ወደዚህ ማሽን ብቅ እያለ ያሻውን ፊልም እንደሚወስድ ይናገራል። “ሰሞኑን ግን የመብራት መቆራረጥ ጋር ተያይዞ አንድ ፊልም ለመውሰድ በርካታ ደቂቃዎችን መቆም ግዴታ እየሆነብኝ ስለመጣ አሰልቺ እየሆነብኝ ነው” ሲል አስተያየቱን ይሰጣል። ለምን በዚህ ማሽን መገልገል እንደመረጠ ኒቆዲሞስ ሲናገር “በማሽኑ መገልገል በርካታ ፊልሞችን ለማግኘት ብትቸገርም ግን ወረፋ እንደሌሎች ቦታዎች አይኖረውም” ሲል ምክንያቱን ያስቀምጣል።

የውጭ አገራት ፊልሞችን እና የቴሌቪዥን ሾዎችን በፍላሽና መሰል መሣሪያዎች በመጫን መሸጥ በአዲስ አበባ በኹሉም አካባቢዎች የተለመደ ንግድ ቢሆንም በቦሌ እና በኻያ ኹለት አካባቢዎች ደግሞ ጎልተው ከሚታዩባቸው አካባቢዎች የመጀመሪያው ተርታ ላይ ይቀመጣሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 30 ግንቦት 24 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here