ልብ ያለው ልብ ይበል!

0
762

ኢትዮጵያ ውስጥ በተካሔደው የዓለም ዐቀፍ የፕሬስ ቀን አንድ በውጪ አገር ድርጅት የተዘጋጀውንና በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ለውጥ ላይ የሚያተኩር አግላይ (በዝግ የተካሔደ) የጎንዮሽ መድረክን መነሻ በማድረግ ጌታቸው መላኩ ይህ ድርጊት አገራችን በሌሎች እንድንጠለፍ ዕድል መክፈቻ በር ሊሆን ከመቻሉ ባሻገር በተለይ የመንግሥትን የፖሊሲና የሕግ ጉዳዮችን አሳልፎ የመስጠት አጋጣሚ ሊኖር ይችላ ሲሉ ስጋታቸውን አጋርተዋል።

የዓለም ዐቀፍ ሐሳብን በነፃ የመግለፅ በዓል ከሚያዚያ 23-25/2011 ለሦስት ቀናት በተከበረበት የመጀመሪያ ቀን ላይ የገጠመኝን ጉዳይ አንስቼ ላውጋችው። በዚህ ዝግጅት ውጣውረድ የተማረረው ሁሉ ይህንን ጉዳይ ቁብ እንደማይለው፤ በተለይ ደግሞ ከነበርው ቱማታና ሁካታ አንፃር ጉዳዩን ያልታዘበው ኢትዮጵያዊ በርካታ ሊሆን ይችላል።

በመጀመሪው ቀን ዝግጅቱን ለመታደም የሚደረገው ምዝገባና ወደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ምጣኔ ሀብት ኮሚሽን ለመግባት የሚደረገው ምልልስ እንደ ወትሮው በጣም አሰልቺና አድካሚ ነበር። በዚሁ ወደ ግቢው ለመግባት በሚደረግው ሒደት መጓተት ሰበብ በርካቶች የመክፈቻው መርሃ ግብሩ አምልጧቸው ነበር። ይህ በእርግጥ አንዳንዶች ባለባቸው ችግር ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አንድ ከደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ተወክሎ የመጣ ግለሰብ የመግቢያ መለያ ካርዱ በሰዓቱ ባለመድረሱ መጉላላቱን በምሬት ሲገልፅ ስመለከት, ከ92 አገራት የመጡ ወይም የወከሉ ከ2 ሺሕ በላይ ተሳታፊ ማስተናገድ ያለአንዳች እንከን ሊከናወን እንደማይችል ግምት ይዣለው።

በዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን (World Press Freedom Day) የመጀመሪያው ዕለት ዝግጅቶች ከሆኑት መካከል በጎንዮሽ ከሚካሔዱ ዝግጅቶች መካከል አንዱ በኢትየጵያ የብዙኀን መገናኛ ለውጥ ጉዳይ ላይ የሚወያየው ዝግጅት ነበር። በዚህ ዝግጅት ላይ የመሳተፍ ከዚያም ባሻገር የራሴን አስተዋፅዖ ለማድረግ ፍላጎት ስላደረብኝ ርዕሱን መርጬ ወደ መሰብሰቢ ክፍሉ አመራሁ።

በእርግጥ የዝግጅቱን መርሃ ግብርና የመሰብሰቢ አዳራሹን ያመላከተችኝ በጎ ፈቃደኛ አስተናጋጅ በግብዣ ብቻ የሚታደሙበት ስብሰባ እንደሆነ አሳስባኝ ነበር። ነገር ግን ወጣቷን ችላ በማለት ወደ መሰብሰቢው ስፍራ አመራሁ። የገጠመኝ ነገር ከአስገራሚነቱ ባሻገር አስቂኝ ነበር። እንድ ነጭ (ከእንግሊዝኛ ቅላፄው አሜሪካዊ ይመስለኛል) የመሰብሰቢው ክፍል በር ላይ ቆሞ ራሱንና የሚሠራበትን ድርጅት ካስተዋወቀኝ በኋላ ተሳትፎው በግብዣ ብቻ እንደሆነ ገልፆልኝ መግባት እንደማልችል አረዳኝ።

ይህች “የመርጠህ ጥራው ወይም ተመራርጠህ ታደም” ጉዳይ ምን እንደሆነች ብገምትም ለማመን ግን ቸግሮኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የለመደብንን የመገፋፋት አባዜ ከእኛው ተምረው እየተጠቀሙበት ይሆን ብዬ አሰብኩ። በዚህ ዓለም ዐቀፍ ስብሰባ ላይና በስብሰባው ሥም የራስን አጀንዳ ይዞ መሰብሰብ ለምን አስፈለገ፤ ባልጠፋ ቦታና ቀን። በእርግጥ ሞኝ ልሁን ካላልኩ ስብሰባው የሚያስገኘውን ትኩረት ለመጋራት እንደሆን አሳባቂ አያስፈልገውም። በተጨማሪም በአገሪቱ እየተካሔደ ያለውን ዙሪያ መለስ የብዙኀን መገናኛ ዘርፍ ምክክሮችና ክርክሮች ሁሉን አካታች እንዲሆኑ እየተለፋ ባለበት ጊዜ እንደዚህ የእኛ ቡድን የሚል ዓይነት ስብሰባ አንድምታው ምን ሊሆን እንደሚችል ግለሰቦቹ የገባቸው አይመስለኝም።

በአንድ ጉዳይ ላይ “የእኛ አስተዋፅዖ ሊረዳ ይችላል” ብሎ ማሰብና ለዚህም መሥራት ቅንነት ሊባል ይችላል። ነገር ግን የእኛ አስተሳሰብ ካልገባበት ማለት ጉዳዩን በሒደት ጠልፎ ለራስ መጠቀሚ ለማድረግ የታሰበ ያስመስለዋል። ከላይ የታዘብኩትም ስብሰባ ከእንደዚህ ዓይነት ኅቡዕ ዓላማ ላለመራቁ ምንም ዋስትና የለንም። በአገራችን እንደዚህ ዓይነት ጉዳይ ክፉ ነቀረሳ ሆኖብን ሲያሰቃየን እንደከረመ ማንም አይዘነጋውም። ይህ ሁሉ የሐሳብ ልዩነት ባለበት አገር አንድ ፓርቲ ዘጠና በመቶ የምክር ቤት መቀመጫ የሚያሸንፍበት ጨዋታ ከዚህ ዓይነት አስተሳሰብና ተግባር የመነጨ ይመስለኛል። በሌላ ጠርዝ ሲታይ ደግሞ ማንኛውም የውጪ አካል አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረትም ሆነ አገራቱ በተናጠል፣ ቻይና፣ ሕንድ፣ ሩሲያ ወይም ጃፓን ሁሉም የየራሳቸው ዓላማ እንዳላቸው ማወቅ አንዱ ጉዳይ ነው። ተፅዕኗቸውን ለመቋቋም የምናደርገው ጥረት መልካም ሆኖ ሳለ፤ የእኛ በር ከፋችነት ምን የሚሉት ነው።

በእርግጥ የስብሰባው በር ላይ እኔን ያነጋገረኝ ነጭ ሥራ ፈላጊ እንደሆነ ለማንም መንገር አያስፈልግም። እርሱን ያሠማሩት የመንግሥትም ይሁኑ የንግድ አካላት ግን ፍላጎታቸው ከዚያ ብዙ ጊዜ እጥፍ ስውርና እሩቅ መሆኑን ልብ ማለት ይገባል። እንኳን መገናኛ ብዙኀንን በመሰለ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ አይደለም, በማንኛውም ጉዳይ ቢሆን እነዚህ ሰዎች ወደኋላ የሚሉ እንዳለሆኑ ከታሪካችን መማር ካልቻልን አንድ ዓይነት ችግር አለብን ማለት ነው።

ለማኝኛውም ወደ ጉዳዬ ልመለስና እንደዚህ ዓይነት የተናጥል “እኛ ብቻ” ስብሰብ ሊኖረው የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖና ችግር እያነሳሁ ለማሳየት ልሞክር።

ችግር አንድ
በመጀመሪያ በዚህ ግለሰብ የሚያስተባብረው በኢትዮጵያ ብዙኀን መገናኛ ለውጥ ላይ የሚመክረውን ውይይት ነው። በነበረን አጭር ሐሳብ ልውውጥ ግለሰቡ ካነሳልኝ ነጥቦች የተገነዘብኩት በዚህ ስብሰባ የተጋበዙት ተሳታፊዎች በኢትዮጵያ ሁሉን አካታች የሆነ የሚዲ ፖሊስና ምኅዳር ለመፍጠር በሚያስችል ጉዳይ ላይ አስተዋፅዖ ያደርጋሉ የተባሉ ግለሰቦች እንደሆኑ ነው። በእርግጥ ስብሰባዎችን በተለይም በእንደዚህ ዓይነት ትልቅ ስብሰባ ላይ በጎን ተዛማጅነት ያላቸውን ስብሰባዎች በግብዣ ማካሔድ የተለመደና ጠቃሚ ጉዳይ እንደሆነ ይታመናል ይዘወተራልም። ሌለው ማሰብ የሚገባው የዚህ ዓይነት ዝግጅቶች አንዳንዴ የሎጂስቲክስ ወጪያቸው ከፍተኛ ስለሚሆን፣ ተለጣፊነቱ ለአዘጋጆቹ የገንዘብ አጠቃቀማቸውን ውጤታማ ለማድረግ አንድ መንገድ ሲሆን፤ የትልቁን ስብሰባ የሚሰጠውንም ትኩረትንም ለመሻማት የሚታቀድ ስልት እየሆነ ከመጣ ዓመታት ተቆጥረዋል።

በዚህ ስብሰባ ላይ የሴት ጋዜጠኞች በድረ ገጽና ኢንተርኔት ሥራ ላይ የሚገጥማቸው ችግር ላይ የሚወያየው አንድ የጎንዮሽ ውይይት ነበር። ወደዚህ ውይይት ለመግባት በግብዣ ቢሆንም በተለይ ተሳታፊዎች ይመለከተናል ካሉ በውይይቱ ላይ እስከ ፍፃሜ ለመቆየትና በንቃት ለመሳተፍ ከመወሰን ባሻገር ሌላ መሥፈርት ያልነበረበት ዝግጅት መሆኑን ታዝቢያለሁ። ይህ መልካም መንገድ ከላይ በጠቀስኩት በኢትዮጵያ የሚዲያ ፖሊሲና ምኅዳር ለውጥ ላይ አስተዋፅዖ ያደርጋሉ ተብለው የተጋበዙት 36 ግለሰቦች ብቻ መሆናቸው ተለይቶብኛል። የውክልናው ጉዳይ፣ የብቃቱ ጉዳይ እንዲሁም ግለሰቡ እንደገለጸልኝ ሁሉን አካታች የመሆኑ ጉዳይ አስገራሚም አሳሳቢም ይመስለኛል።

አሁን እንዳለፉት ጊዜያት ምን አገብኝ የሚባልበት ጊዜ አይደለም። አሁን እንዳለፈው ጊዜ ጉዳዩ በመጨረሻ ሲጨናገፍ እናየዋለን የምንልበት ጊዜ አይደለም። እንደዚህ ዓይነት አባባሎች ምን ያህል ችግር እንደፈጠሩ ካለፈው የሦስት ዐሥርት ዓመታት አጭር የአገራችን የብዙኀን መገናኛ ታሪክ መረዳት እንችላለን። በመሆኑም ጉዳዩ ያገባኛል የሚል ስህተትም ይሁን ትክክል ጥያቄ የሚጠይቅ ሰው መኖር አለበት፤ የጥያቄ ስህተትም ትክክልም ስለሌለው። ጥያቄ ጥያቄ ነውና! በመሆኑም የዚህ ዓይነት ውይይት ከእንደዚህ ዓይነት ትልልቅ ስብሰባዎች ተጠግቶ የሚነሱ አሳሳቢ አሰራሮች ግልጽ መሆን አለባቸው።

ችግር ኹለት
እስከመቼ በራሳችን በተለይ በወሳኝ ጉዳዮቻችን የድኅነቱ አስተሳሰብ ስለወጠረን ብቻ ገንዘቡን ፍለጋ በሌሎች እንዲጠለፉ ዕድል እንሰጣለን። እስከ መቼስ የአገር ፖሊሲና ስትራቴጂ በለጋሽ አገሮች ድጋፍ የገንዘብ ችሮታ ላይ ይንጠለጠላል። እስከመቼስ በባለሙያ ሰበብና ገንዘቡን በሚለግሱን ‘ረዳቶች’ አማካይነት ሰባራና ሰንካላ ፖሊሲና ስትራቴጂ ስንቀርጽ እንኖራለን። ከዚህ ቀደም የግለሰቦችን በወዳጅነት ለመጥቀም ሲባል ብቻ ከእውቀትና ልምድ የተጣሉትን እየሰበሰቡ የተሠሩ ፖሊሲዎች ሲያስተዛዝቡን ተመልክተናል። በዕውኑ የአገራችን መንግሥት የዘርፎችን መመሪያ ፖሊሲ መንደፍ የሚችሉ ባለሙዎችንና ተቋማትን ማስተባበር አቅቶት ነው? አሁንም ደግሜ የማነሳው የታዋቂውን ጋዜጠኛና ደራሲ የግርሀም ሀንኮክን ‘Lords of Poverty’ መጽሐፍ ለአፍታ እንድንመከተው ነው።

ምን ይደረግ?
ይህንን ምክረ ሐሳብ የማቀርበው ከራሴ ልምድ ብቻ በመነሳት ሳይሆን ሌሎች ግለሰቦችም እንዲሁ ሲያነሱና ሲጥሉ፣ ሲተቹና ጠቀሜታውንና ጉዳቱን ሲያመላክቱ የነበረበት ሁኔታ ስለነበረ የእነሱንም ሐሳብ ያካትታል ብዬ ተስፋ አደርጋለው። የፖሊሲና የሕግ ጉዳዩን አንድ መንግሥት ለሌላው በተለይ በሥመ የልማት አጋር አሳልፎ ከሰጠ ጉዳዩ ሰዶ ማሳደድ እንደሚሆን ይታወቃል። በመሆኑም በተለይ እነዚህ ጉዳዮች የሚታዩበትና የሚነቀሱበት መንገድ በሕግ መደንገግ ይገባል። አሊያ ጉዳዩ የአንድ ሰሞን ጨዋታ ይሆናል።

ጉዳዬን በአንድ አጋጣሚ አንድ የሌላ አገር ዜጋ የሆነ ባልደረባዬ የሰማሁትን ላንሳና ልቋጭ። ይህ ባልደረባዬ በአንድ አጋጣሚ በሥራ ላይ የተደረሰ ስምምነት በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሲጓተትበት “በኢትዮጵያ ሕግ ማውጣት ቀላል, መተግበሩ ግን ከባድ ነው። በእኔ አገር ግን ከባዱ ሕግ ማውጣቱ ነው” ያለኝን በደንብ አስታውሳለሁ። በመሆኑም የሚመለከተው አካል ጉዳዩን በትኩረት እንዲመለከተው የሚል መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ።

ጌታቸው መላኩ የሚዲያና ተግባቦት አማካሪ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው getachewmelaku@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 30 ግንቦት 24 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here