የእስላማዊ ባንክ ፖለቲካ!?

0
855

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሙስሊሞች ለአፍጥር በሚሊኒየም አዳራሽ ተሰብስበው በነበረበት ወቅት እስላማዊ ባንክ እንዲመሰረት የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ ማስታወቃቸው ይታወሳል። ይነገር ጌታቸው “ከእስላማዊ ባንክ ጀርባ የሚኖረው ማነው?” የሚል ጥያቄ በማንሳት የአገራትን ተመክሮ ከባለረጃጅም እጆቹ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት በተለይም ከተባበሩት አረብ ኤምሬት የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ አንጻር የሚደረጉ ግንኙነቶች ብርቱ ጥንቃቄ ማየት እንደሚያስፈልግ መከራከሪያ ነጥቦችን አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ደስ ሲላቸው ለፖለቲካ ሚስጢራቸው አይሰስቱም። ከተባበሩት አረብ ኤምሬት ንጉሥ ቤን ዛይድ ጋር በመከሩ ሰሞን ከጋዜጠኞች ፊት ተገኝተው አቡዳቢ እስልምናን ላስተምራችሁ የሚል ጥያቄ ብታቀርብም እኔ ግን እምቢ አልኩ ሲሉ ተደምጠዋል። ዐቢይ የመርህ ሰው መሆናቸውን ለማሳየት ያቀረቡት ይኼ ማስረጃ ጓዙ ብዙ ነው። የመጀመሪያው ጉዳይ የተባበሩት ኤምሬትሶች ወዳጅነት በሃይማኖት የተቃኘ መሆኑን ገሃድ ማውጣቱ ይመስለኛል። ሌላውና ወሳኙ ነገር ደግሞ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ እስላማዊ ትምህርት ቤቶችን የመክፈት ሐሳብ ተቃወምኩ ሲሉ, የተስማሙበት ነገርስ ምን ይሆን የሚለውን ጥያቄ አለመመለሳቸው ነው።

ባለፈው አንድ ዓመት የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ የመካከለኛ ምሥራቅ ኀያላን ሳዑዲና ኤምሬት ለአራት ኪሎ ሸሪክ መሆናቸውን በተደጋገሚ አሳይተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሪያድ አቅንተው የአገሪቱን የክብር ኒሻን ተቀብለዋል። ከአቡዳቢው ሰው ቢሊዮን ዶላር ለአገራቸው አስገኝተዋል። የጥያቄያችን አዕማድ የሚሆነው ሐሳብም ከዚህ ይመነጫል። የኢትዮጵያ የለውጥ ፖለቲካ ከመካከለኛው ምሥራቅ ጋር ያለው ግንኙነት መሰረታዊ መነሻው ምንድነው? ሰሞነኛው የእስላማዊ ባንክ ጉዳይስ ከዚህ አንጻር እንዴት ይቃኛል?

ወደ አቡዳቢ ያንጋጠጠው አራት ኪሎ
መሀሪ ታደለ (ዶ/ር) የተባበሩት አረብ ኤምሬትና የአፍሪካን ቀንድ ግንኙነት በተነተኑበት ጽሁፋቸው የአቡዳቢ የውጭ ጉዳይ ፖሊስ አራት መሰረታዊ መርሆች አሉት ይላሉ። ከእነዚህ ውስጥ ኹለቱ ሃይማኖትን መነሻ ያደረጉ ሲሆኑ የቀሩት ንግድና ቱሪዝምን የተንተራሱ ናቸው።

የንጉሥ ቤን ዛይድ ስርዓት ሃይማኖትን የሻተ ወዳጅነት አንድም ፀረ የሙስሊም የወንድማማቾች ኅብረት እንቅስቃሴን የሚደግፍ ሲሆን አንድም አፍሪካ ቀንድን ከሽአ እስልምና ከማራቅ ይቀዳል። ለመሀሪ የአቡዳቢ ንጉሣዊ አስተዳደር ከኢራን እና ከሙስሊም ወንድማማቾች ጋር ያለው ልዩነት ከሃይማኖታዊ አስተምሮም የላቀ አንድምታ አለው። ለዚህ የሚሆን ማስረጃ ሲጠቅሱም የተባበሩት አረብ ኤምሬት ቴህራን የምታደርገውን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ቅንጦት አድርጋ እንደምትቆጥር ይገልፃሉ። ይህ ደግሞ አቡዳቢ ከሃይማኖት ጎን ለጎን ለአምባገነናዊ ስርዓት እንድታደላ አድርጓታል ይላሉ።

የተባበሩት አረብ ኤምሬት ከላይ እንደገለፅኩት ከማንም ጋር ያላትን ወዳጅነት በሃይማኖት አልያም በንግድና ቱሪዝም ላይ የመሰረተች አገር ናት። ይህ ሀቅ ደግሞ ለኢትዮጵያም የሚሠራ ነው። ጥያቄው የአቡዳቢ እና አዲስ አበባ ሽርክና የሚያስበልጠው ሃይማኖትን ወይንስ ንግድና ቱሪዝምን? የሚለው ይመስላል። የንጉስ ቤን ዛይድ አገር በኢትዮጵያ ያላት ኢንቨስትመንት 360 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚጠጋ ነው። የንግድ ትስስራቸውም አንድ ቢሊዮን ዶላር ለመድረስ አልታደለም። አቡዳቢ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ከአዲስ አበባ ይልቅ ተስፋ የምታደርጋቸው አገራት ኬንያ፣ ዩጋንዳና ታንዛኒያን እንደሆነ በተደጋጋሚ አሳይታለች። ይህ ዓይነቱ ፍኖት ደግሞ የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬት ወዳጅነት በሃይማኖት መቃኘቱን እርግጥ ያደርግልናል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እራሳቸው እንዳረጋገጡልንም አቡዳቢ የእስልምና ትምህርት ቤቶችን የመገንባት ፍላጎት አላት። ዐቢይ እንዲህ ያለውን የወዳጃቸውን ንጉሥ ቤን ዛይድ ምስጢር ከአደባባይ ቢያውሉትም የእሳቸውን ገመና ግን አልገለጡልንም።

የአገራት ወዳጅነት በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የሚያጠነጥን መሆኑ እሙን ነው። የሃይማኖት ደመና የከለለው የተባበሩት አረብ ኤምሬትና የኢትዮጵያ ወዳጅነትም ከዚህ እውነት የሚርቅ አይሆንም። አቡዳቢ በኢትዮጵያ የተፈጠረውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ ቢሊዮን ዶላሮችን በማፍሰስ ላይ ትገኛለች። የዐቢይ አስተዳደር ሥልጣነ መንበሩን በተረከበ ሰሞን ወንበሩ እንዲፀና አምስት ቢሊዮን ዶላር ሰጥታለች። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕይወት አደጋ ላይ መወድቁን ተመልክታም የጦር መሣሪያን የሚቋቋም መኪና በነፃ አበርክታለች። የንጉሥ ቤን ዛይድና የአራት ኪሎ ወዳጅነት ዜና መዕዋል ከዚህም ያለፉ ብዙ ያልተሰሙ ታሪኮች ያሉት መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከወዳጅ አገር አገኘሁት የሚሉት የቤተ መንግሥት ማሳደሻ ወጭም ከሞላ ጎደል ከአቡዳቢው ሰው የተገኘ መሆኑ ተረጋግጧል። ንጉሥ ቤን ዛይድ ከሚነገረው በላይ የማይነገር ውለታን ለአራት ኪሎ እየዋሉ ነው። በርግጥም ለምኒልክ ቤተ መንግሥት ዕድሳት አራት ቢሊዮን ብር የሚለግስ መሪን በዚህ ሰዓት ማግኘት አስቸጋሪ ነበር። ግን ቤን ዛይድ ይህን አድርገውታል።

የአቡዳቢው ሰው ምኒልክ ቤተ መንግሥት የገቡት ረብጣ ዶላር ብቻ ይዘው አይደለም። የራሳቸው ሐሳብም አላቸው። እንደየትኛውም አገር መሪ የሚሰጡትን ያህል ከአራት ኪሎ ማግኘት ይሻሉ። ይህ ፍላጎታቸው አንድ ቢሊዮን ዶላር መድረስ የተሳነውን የአገራቱን የንግድ ትስስር ማጎልበት አይመስልም። ፍላጎታቸው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ላይ የተቀመጠውን ሃይማኖታዊ ጉዳይ መነሻ ያደረገ ነው። ለአራት ኪሎ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደሚገልጹት የንጉሥ ቤን ዛይድ ሰዎች አራት ኪሎ ውሳኔዎች ላይ ጣልቃ መግባት ጀምረዋል። በእነዚህ ወገኖች እምነት በቅርቡ በሴነጋል የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው መሾማቸው ተሰምቶ የነበረው ሀሰን ታጁ የዲፕሎማሲ ሥልጠናውን ከወሰዱ በኋላ ከዚህ ተልዕኮቸው እንዲነሱ የተደረጉት ከአቡዳቢ በመጣ ትዕዛዝ ነው።

ሌላ መስኮት
ቴጅ ኦስቴቦ እና ዋለልኝ ሸምሰዲን “The Intellectualist Movement in Ethiopia, the Muslim Brotherhood and the issue of Moderation” በተባለ ጥናታቸው የድኅረ ኢሕአዴግ’ን የእስልምና ዝመና ንቅናቄ በሦስት ይከፍሉታል። ሰለፊያ እና ጀማት አል ታብሊፍንወደ ጎን ያደረገው የኹለቱ ተመራማሪዎች ዕይታ ለሙስሊም ምሁራን እንቅስቃሴ ያደለ ነው። ኦስቴቦ እና ዋለልኝ ሕወሓት መራሹ ኃይል አራት ኪሎ በገባ ማግስት የተገኘውን አንፃራዊ ነጻነት የተመለከቱት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሙስሊም ተማሪዎች አነስተኛ የውይይት ክበብ መስርተው እንደነበር ያወሳሉ። ከስግደት በኋላ በሚደረጉ ሃይማኖታዊ ውይይቶች ጉዞ የጀመረው ክበቡ በጊዜ ሒደት ከኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ማኅበር በሚያገኛቸው ዓለም ዐቀፍ የእስልምና ሥነ ጽሁፎች ላይ ተንተርሶ ሙግቶች ያካሔድ ነበር። በአንድ ቡድን ውስጥ ከስምንት እስከ ዐሥር አባላትን በመያዝም በዩኒቨርሰቲው ውስጥ ሰፊ አደረጃጀትን ለመፍጠር በቃ። አወቃቀሩን ከዓለም ዐቀፉ የሙስሊም ወንድማማቾች ኅብረት ላይ በመዋስም የየቡድኖቹ ተወካዮች የጋራ መድረክ እንዲኖራቸው አደረገ።

ከአዲስ አበባ አልፎ በፍጥነት ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የተዛመተው ይህ የሙስሊም ወጣቶች ንቅናቄ ተዋረዳዊ የሥልጣን አካል ባይኖረውም እድሪስ ሙሐመድና ሀሰን ታጁ የሚባሉ ሥሞችን ግን ዝነኛ ያደረገ ነበር። እነዚህ ወጣቶች ወዲህ ከተማሪው ንቅናቄ ጋር ሲተሳሰሩ ወዲያ ከኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ማኅበር ጋር ሥማቸው ይያያዝ ጀምረ። ኦስቴቦና ዋለልኝ ስለኹለቱ ወጣቶች ሲያነሱ በዓለም ዐቀፉ የሙስሊም ወንድማማቾች ኅብረት ላይ የነበራቸውም ልዩነት ይጠቅሳሉ። ሀሰን የኢትዮጵያ እስልምና የራሱ መልክ ስላለው እነሱ ያሉበት ማኅበር የዓለም ዐቀፉ ሙስሊም ወንድማማቾች ኅብረት አባል መሆን የለበትም የሚል አቋም ነበረው። በዚህ አስተሳሰብም በርካታ ውግዘትና ተቃውሞዎችን አስተናግዷል። የዚህ ማኅበር መዳካም ግን በአባላቱ የሐሳብ ልዩነት ተረግዞ የተወለደ ብቻ አልነበረም።

ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስብስባ ወደ አዲስ አበባ ጎራ ባሉት ሆስኒ ሙባረክ ላይ የግድያ ሙከራ ሲደረግ እጁ አለበት ለተባለው የግብፅ ሙስሊም ወንድማማቾች ኅበረት ድጋፍ ያደረገው የኢትዮጵያዊያን ሙስሊም ምሁራን ንቅናቄ ነው የሚል ጥርጣሬ በመንግሥት ውስጥ አደረ። በዚህ ምክንያትም የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ማኅበር ውስጥ ይሳተፉ የነበሩ በርከት ያሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወደ ማረሚያ ተወረወሩ። ይህ ግን ንቅናቄውን አዳፈነው እንጂ ሙሉ በሙሉ ያጠፋው አልነበረም። ከዓመታት በፊት በቃሊቲ እስር ቤት ውስጥ ከእነዚህ ወገኖች ለመገናኘት የበቃ የቀድሞ ፖለቲከኛ እንዳጫወተኝ ልዩነታቸው ማረሚያ ድረስ ተከትሎ የወረደ ነው። እንዲህ ያለው እውነት የኢትዮጵያ ሙስሊም ምሁራን የዓለም ዐቀፉ የሙስሊም ወንድማማቾች ኅብረት አካል መሆን አለበት የለበትም በሚለው ላይ ተመሳሳይ አቋም እንደሌላቸው ያሳያል። በአስተሳሰብ ደረጃም ነገሩ አለመዳፈኑን ያረጋግጣል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬት ከላይ እንደገለፅኩት የዓለም ዐቀፍ ሙስሊም ወንድማማቾች ኅብረትን በይፋ ታወግዛለች። ሳዑዲ አረብያ ጋር በመጣመር ኳታርና ቱርክን በጠላትነት መፈረጇም ከዚህ የሚመነጭ መሆኑን አስታውቃለች። አቡዳቢ የኢትዮጵያ ሙስሊም ምሁራን ከዓለም ዐቀፉ ወንድማማቾች ኅብረት ጋር እንዳያብሩ የተቻላትን ሁሉ እያደረገች ትገኛለች። የቤን ዛይድ ሰዎች እንደ ግለሰብ ሀሰን ታጁ ከአዲስ አበባ እንዳይርቅ የሚፈልጉበት መሰረታዊ ምክንያትም ከዚህ የሚቀዳ ይመስላል። ይህ በአንድ በኩል ብዝኀ ሃይማኖት ላላት ኢትዮጵያ ጥሩ የሚባል ቢሆንም በሌላ በኩል የተባበሩት አረብ ኤምሬት አርቃ በወረወረችው ችግሯ ፋንታ ምን ትተክላለች የሚል ጥያቄን ያስነሳል።

እስላማዊ ኢኮኖሚ የቀደደው እስላማዊ ፖለቲካ
በኢትዮጵያ የሚስተዋለው የሙስሊም ሊኂቃን እንቅስቃሴ ፈርጀ ብዙ የሚባል ነው። ከፊሉ ወገን የድኅረ እስልምና ንቅንቄን (post Islamism) በኢትዮጵያ ዕውን ማድረግ ይፈለጋል። የዚህ እንቅስቃሴ መሪዎች እስላማዊ ነፃነት እና እስላማዊ ዴሞክራሲን ግብ ያደረጉ ናቸው። የቀረው ወገን የበሉይ እስልምናን (classic Islamism) ማጠናከር አለብን ይላል።ኹለቱም ጎራ ከመሰሎቹ ዓለም ዐቀፍ እንቅስቃሴዎች ገንዘብ እንደሚያገኝ የሚያጠራጥር አይደለም። የሙስሊም ወንድማማቾች ኅብረትን የምትረዳው ቱርክ የአልነጃሽን መስጅድ ለማደስ ሰሜን ኢትዮጵያ ስትዳክር የእሷ ተቀናቃኝ የሆነችው የተባባሩት አረብ ኤምሬት በሰረገላ አራት ኪሎ ደርሳለች። ዶላር የተጠማው የምኒሊክ ቤተ መንግሥት ሃይማኖትን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው አካል ካደረጉት አገራት ጋር በሚችለው ነገር ሁሉ እየተደራደረ ገንዘብ ለማግኘት እየጣረ ነው።

ያልጠራው የኢትዮጵያ ሙስሊም ምሁራን የመብት ጥያቄም አሁንም ከአራት ኪሎ ደጃፍ አልራቀም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቅርቡ እንደገለፁት ሙስሊሞች የራሳቸው ባንክ እንዲኖራቸው የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ ብለዋል። ጥያቄው ያለው እዚህ ላይ ይመስለኛል። ነገ ከሚከፈተው እስላማዊ ባንክ ጀርባ የሚኖረው ማነው? ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ከሆኑ ደስታው የጋራ ነው። ግን ከዓለም ዐቀፍ ነባራዊ ሁኔታዎች አንፃር ከተመለከትነው ፍፁም ኢትዮጵያዊያን የሆኑት ሙስሊሞች ርብጣ ገንዘብ ባላቸው የውጭ ኃይሎች የመዋጥ ስጋት እንዳለባቸው እሙን ነው።

እዚህ ላይ ሱዳን በ1970ዎቹ ገጥሟት የነበረው የኢኮኖሚ ቀውስ ከእኛ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ስለሚመሳሰል እሱን ለማየት እንሞክር። የቀድሞው የሱዳን ፕሬዘዳንት ጃፋር ኒሜር አገራቸው በኢኮኖሚ አጣብቂኝ መላወሻ ስታጣ ኹለት አማራጮችን ተጠቅመው ነበር። የመጀመሪያው መንግሥትና ሃይማኖት የሚለያዩበትን ድንበር ጥሰው ገንዘብ አመጣለሁ ላላቸው ሁሉ በራቸውን ክፍት አደረጉ። መሪነታቸውን ረስተው ሃይማኖታዊ ውዳሴዎች ላይ ተሰማሩ። በዚህ ቀዳዳም የእስልምና ፖለቲካ ኃይሎች ሱዳንን አጥለቀለቁ።

ኒሜሪ በዚህ አላበቁም። የእስላማዊ ባንክ ምስረታን ፈቅጃለሁ አሉ። ሳዑዲ አረቢያ የመነሻ ካፒታሉን አቅርባ በሚታይም ሆነ በማይታይ መንገድ የአመራርነቱን ሰገነት ተቆጣጠረች። ይህም ለፖለቲከኞች የፋይናንስ ምንጭ ምቹ መደላድልን ፈጠረ። የቀድሞው የኮለኔል መንግሥቱ ወዳጅ ከዚያ በኋላ ሥልጣን ራቃቸው። የሱዳን ፖለቲካና ኢኮኖሚ ከእጃቸው ወጣ። ኒሜሪ በምክትላቸው ተፈነቀሉ። ሱዳንም እስላማዊ መንግሥትን መሰረተች።

በእርግጥ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ከዚህ በብዙ መልኩ የተለየ መሆኑ አያከራክርም፤ ግን በፖለቲካው ዓለም አይሆንም የሚባል ነገር የለም። አገር ዐቀፍ ሥያሜን አላብሶ እስላማዊ አጀንዳን የያዘ ፓርቲ ለመመስረት ጥረት በሚደረግባት ኢትዮጵያ የእስላማዊ መንግሥት ምስረታ ሥጋት ባይሆን እንኳን አክራሪነት የባጃጅ ጣሪያ ያህል ቅርብ ነው። በመሆኑም ከእስላማዊ ፖለቲካ ባልመነነችው አገር ላይ የሚመሰረተው እስላማዊ ባንክ ጥንቃቄ ያሻዋል።

ይነገር ጌታቸው ተለያዩ መገናኛ ብዙኀን በማገልገል ላይ የሚገኙ ባለሙያ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው mar.getachew@gmail.com ሊገኘኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 30 ግንቦት 24 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here