የሟቹ አራጣ አበዳሪ አየለ ደበላ ንብረት ክርክር አስነሳ

0
908

ከ6 ዓመታት በፊት ሕይወታቸው ያለፈው እና አራጣ ማበደርን ጨምሮ በተለያዩ ኢኮኖሚ ነክ ወንጀሎች 22 ዓመት እስር ተፈርዶባቸው የነበረው የአየለ ደበላ ንብረት ጉዳይ በመንግሥት፣ በልጃቸው እና የንብረቱ የቀድሞ ባለቤት መካከል የንብረት ይገባኛል ክርክር አስነሳ።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ መንግሥት ቤቱን ስለወረሰው ተሸጦ ገቢ መሆን አለበት በማለት 400 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈውን መኖሪያ ቤት የሟች ልጅ ወራሽ በመሆኔ ይገባኛል በሚል ተቃውሞ ያቀረቡበት ሲሆን የቤቱ መጀመሪያ ባለቤት ሟች ያለአግባብ በአራጣ አበዳሪው ንብረቴን ስለተቀማሁ መንግሥት ቤቴን ይመልስልኝ ሲሉ ጣልቃ ገብተዋል።

በ2002 ግንቦት ወር በ10 የተለያዩ ክሶች በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 11ኛ ወንጀል ችሎት ጥፋተኛ ተብለው የነበሩት አየለ ከ22 ዓመት ፅኑ እስራት ባሻገር በንብ ባንክ የነበራቸውን ድርሻ እንዲወረስ እና ተጨማሪ 130 ሚሊዮን ብር እንዲከፍሉም ተወሰኖባቸው ነበር። ውሳኔው የገንዘብ መቀጮው ወደ 450 ሚሊዮን ብር ከፍ እንዲል በሚል በገቢዎች እና ጉምሩክ ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ ተብሎ ሳለ በ2005 ሕይወታቸው አልፏል።

መደበኛው ክርክር ባለቀበት ወቅትም በተከፈተው የአፈጻጸም መዝገብ በወር 2 ሺሕ የአሜሪካን ዶላር በሚከራየው መኖሪያ ቤት ዙሪያ ክርክር የተነሳ ሲሆን በዚህም ብቸኛ ልጃቸው ሒሩት አየለ የወራሽነት ጥያቄን አንስተዋል። በወቅቱም የተሰጠው ውሳኔ የሦስተኛ ወገን መብት ተከብሮ ይፈፀም የሚል መሆኑ ለጥያቄዎቹ መሰረት ሆኖ ክርክር ሲደረግበት ቆቷል።

ሆኖም የሟች አየለ ደበላ ልጅ “ቤቱ ውስጥ የምኖረው እኔ ነኝ እንዲሁም የቤቱ ባለቤት መሆኔን የሚረጋግጥ ማስረጃ ስላለኝ ቤቱ የሚገባኝ ለእኔ ነው” በማለት ተከራክረዋል። ከዚህ ቀደም የቤቱ ባለቤት መሆናቸውን የሚገልፁት ግለሰብ ቤቱ በአራጣ በሟች አየለ በኩል በግፍ እንደተወሰደባቸው በመግለፅ የቤቱ ቀዳሚ ባለቤቶች እንደመሆናችን መጠን ቤቱ ሊመለስልን ይገባል ሲሉ ሞግተዋል።

ዐቃቢ ሕግም በበኩሉ ይህ ቤት የተገኘው አራጣ ከማበደር ጋር ተያይዞ በመሆኑ እንዲሁም ቤቱ ከዚህ ቀደም ተወርሶ የነበረ በመሆኑ ቤቱ ለማንም አይገባም በማለት ተከራክሯል።

የኢትዮጽያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከአራጣ ማበደር ተግባር ጋር ተያይዞ በአየለ ደበላ ላይ ክስ ያቀረበው ግለሰቡ ለባንክ ብቻ የተፈቀደውን አገልግሎት ሲሰጡ በመገኘታቸው፣ ግብር አዋጅን በመጣስ የተጨማሪ እሴት ታክስ ሳይከፍሉ መቅረታቸው እንዲሁም በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስለው በማቅረብ ገቢ ሰብሳቢ መስሪያ ቤቱን አሳስተዋል በሚል ነበር።

አየለ በወቅቱ በንብ ባንክ በዝግ አካውንት አስቀምጠውት የነበረ ብር 12 ሚሊዮን፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሚገኝ አንድ መኖሪያ ቤት እንዲሁም ኹለት ተሸከርካሪዎች የሦስተኛ ወገኖች መብት ተጠብቆ እንዲወረሱ ሲል ውሳኔ የሰጠባቸው ንብረቶች ነበሩ።

ጉዳዩን እየመረመረው የሚገኘው የልደታ ምድብ የወንጀል ችሎትም ፍርድ ቤቱም ከዚህ ቀደም ግንቦት 12/2011 በዋለው ችሎት በቀድሞው የኢትዮጽያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ፣ የባንክ ሥራ ማሠራት፣ የገቢ ግብር እና የተጨማሪ እሴት ታክስን በመሰወር ወንጀል የተፈረደባቸውን ግለሰብ ንብረት ጉዳይ ለመወሰን ቀን ቆርጦ ነበር።

ለግንቦት 12/2011 የሰጠው ቀጠሮም ቢሆንም የክርክሩ ድምፅ ከመቅረፁ ተገልብጦ ባለመምጣቱ ውሳኔ ለመስጠት ተለወጭ ቀጠሮ ለሰኔ 26/2011 ሰጥቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 30 ግንቦት 24 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here