“አውታር” ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ትንሣኤ!?

0
892

በኢትዮጵያ በርካታ የሥነ ጥበብ በተለይም ደግሞ በሙዚቃው ዘርፍ የተሰለፉ ግለሰቦች እንቅልፋቸውን ሰውተው ለሕዝብ የሚያቀርቧቸው የሙዚቃ ሥራዎች በተለያዩ ምክንያቶች መና ቀርቶባቸው አንገታቸውን የደፉበት ያለፉትን ዓመታት አሁን ተረት ለማድረግ እየተሠራ ይመስላል። በተደጋጋሚ ለቁጥር የሚያዳግቱ ኢትዮጵያዊያን የሙዚቃ ሰዎች አደባባይ በመውጣት ስለቅጂ እና ተዛማጅ መብቶች ጮኸዋል፣ አዚመዋል፣ የሕግ ከለላ እና ማዕቀፍ እንዲያገኙም ደክመዋል። ይህ ባለመሆኑ የጥበብ ተሰጥዖ እና አቅም የነበራቸው ድምፃዊያን ብዙ መሥራት እየቻሉ ያለዕድሜያቸው ከሙዚቃው ዓለም ራሳቸውን አግልለዋል።

ታዲያ መንግሥት በተደጋጋሚ ከቅጂ እና ተዛማጅ መብቶች ጋር በተያያዘ የሕግ ማዕቀፉን ቢያጠነክርም, ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር አብሮ እየዘመነ የሚመጣውን የኢትዮጵያን ሙዚቃ ማቀጨጭ ተግባር ግን በቂ ሊባል በሚችል ደረጃ ጥበቃ ሳያደርግለት ዓመታት ነጉደዋል። ቀደም ባሉት ዓመታት ከአሳታሚ ድርጅቶች ወይም በጊዜው ከነበሩት ታላላቅ ሙዚቃ ቤቶች ወደ ሕዝቡ የሚደርሱት ሙዚቃዎች በካሴት የታተሙ ነበሩ። በዚህ ጊዜ ታዲያ ገበያ ላይ ከሚሸጡት ሕጋዊ ካሴቶች ይልቅ በየጓዳው በሕገ ወጥ መንገድ ተባዝተው የሚሸጡት ከቁጥር ይልቁ ነበር። ይህንም ተከትሎ ቀድሞውንም የማያወላዳ ገቢ ያገኙ የነበሩትን ድምፃዊያን የባሰውን ችግር ላይ እንዲወድቁ እና ለቀጣይ ሥራ እንዳይነሳሱ ያደርግ ነበር። በዚህ የጀመረው ሕገ ወጥ ቅጂ ታዲያ ቴክኖሎጂ ሲዘምን አብሮ ተመነደገና በሲዲ ዘመንም ጎልብቶ ብቅ አለ። እንደ ካሴት ዘመን በሲዲም ዘመን ሕገ ወጥ ቅጂዎች የሙዚቀኞችን ቅስም ሰብሮ ከጥበብ ዓለም አሰናብቷል።

በዚህ ሳያበቃም በአሁኑ ዘመን በበርካታ የማኅበራዊ ድረ ገፆች አማካኝነት የሚለቀቁት የሙዚቃ ሥራዎች ተጠቃሚዎች በስልክና በሌሎች መገልገያዎች በቀጥታ ከኢንተርኔት በማውረድ ከመጠቀም ባለፈ ለወዳጆቻቸው በማጋራት ባለሙያዎች ከሥራዎቻቸው የሚያገኙትን ጥቅም በእጅጉ እንዲቀንስ እንደሚደረግ የአደባባይ ምስጢር ነው።

በቅርቡ በሙዚቀኞች ላይ የሚደርሰውና ይደርስ የነበረው ጫና ታሪክ ለማድረግ ወደ ሥራ ተገብቶ በዘመኑ ቴክኖሎጂ የታገዘ መተግበሪያ ይፋ ሆኗል።

ይህ ለበርካታ ኢትዮጵያዊያን ሙዚቀኞች ትንሣኤ ይሆናል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት አዲሱ የቴክኖሎጂ ውጤት “አውታር መተግበሪያ” ይባላል። አውታር በአራት ኢትዮጵያዊያን ሙዚቀኞች ማለትም ታዋቂው የሙዚቃ አቀናባሪ ኤልያስ መልካ፣ ድምፃዊ ጆኒ ራጋ፣ ? ዳዊት ንጉሤ እና ድምፃዊ ኃይሌ ሩትስ ሐሳብ አመንጪነትና ባለቤትነት ነው የተፈጠረው። መተግበሪያው በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሕጋዊ የሙዚቃ መገበያያ ሲሆን ከሃምሳ ዓመታት በፊት የተሠሩትን የኢትዮጵያ ሙዚቃዎችን የቅጂ መብቶቻቸው በተጠበቀ መልኩ ለተጠቃሚ የሚያቀርብ እንደሚሆን ተገልጿል።

ይህንን የሙዚቃ መገበያያ መተግበሪያ በተለይ ደግሞ በዓይነቱ ልዮ የሚያደርገው, ተጠቃሚዎች በስልካቸው ላይ ያለውን የአየር ሰዓት በመጠቀም መግዛት የሚችሉ ሲሆን አንድ ተጠቃሚ የሚፈልገውን ነጠላ ዜማ ወይም አልበም ከገዛ በኋላ ወደ ሌላ ተጠቃሚ ማጋራት እንዳይችል ተደርጎ ነው የተሠራው። ይህም ሕገ ወጥ ቅጂን በእጅጉ ይቆጣጠራል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል። በአውታር መገበያያ የአንድ ነጠላ ዜማ በ4 ብር ከ50 ሳንቲም የሚሸጥ ሲሆን አንድ ሙሉ አልበም ደግሞ 15 ብር ዋጋ ተቆርጦለታል።

አዲሱን የሙዚቃ መገበያያን በሚመለከት ከመሥራቾች አንዱ የሆነው ድምፃዊ ጆኒ ራጋ ከአዲስ ማለዳ ጋር አጭር ቆይታ ባደረገበት ወቅት ማብራሪያዎችን ሰጥቷል። “ጠንካራ ቴክኖሎጂን ተጠቅመናል” የሚለው ጆኒ ከዚህ ቀደም “አሪፍ ዘፈን” የሚባል መተግበሪያ እንደነበር በማስታወስ, ያለ ሙዚቀኞች ይሁንታ ዘፈኖችን በመጫን ለሽያጭ ያቀርብ እንደነበር ገልጿል።

ጆኒ “ያለእኔ ፈቃድ ሙዚቃዎቼ ተወስደው በአሪፍ ዘፈን መገበያያ ለሽያጭ ቀርበውብኛል። መቀመጫው እዚህ ስላልሆነ ነው እንጂ ወደ ሕግ አመራ ነበር” ሲል በሥራዎቹ የጥቅም ተጋሪ እንዳልነበረና ይልቁንም ሌሎች የራሳቸው ያልሆነ ሲሳይ ሲያፍሱ መክረማቸውን ጆኒ ስሜት በተጫነው ሁኔታ ተናግሯል። አውታር ግን በቀጥታ የባለሙያዎችን ፍቃድ ሳያገኝ ምንም ዓይነት የሙዚቃ ሥራ ለገበያ እንደማያቀርብ ይናገራል። አውታር ለሕዝብ ይፋ ከተደረገ ጥቂት ቀናትን ያስቆጠረ ቢሆንም ለመጀመሪያ ጊዜ 17 የሙዚቃ አልበሞች መተግበሪያው ላይ እንደተጫኑና ለገበያ እንደቀረቡ ያስረዳል።

በርካታ የፕሮሞሽን ባለሙያዎች፣ የፕሮዳክሽን ባለቤቶች የሙዚቀኞችን ክፍተት እንደሚፈልጉ እና ራሳቸው ብቻ የሚጠቀሙበትን ቀዳዳ እንደሚያስሱ የሚገልጸው ጆኒ, አውታር ግን ከሙዚቀኞች ጋር ሕጋዊ ውልን በማሰር ውክልናን በመውሰድ ከቅጂ ጋር በሚነሱ ጉዳዮችም ሙዚቀኛውን ወክሎ እንደሚከራከር ያስረዳል። ከሽያጭ በተጨማሪም አውታር በቀጣይ ደግሞ ከሙዚቀኞች ጋር በመነጋገር ትላልቅ ኮንሰርቶችን እና የሽልማት ሥነ ስርዓቶችን ለመጀመር በቅድመ ዝግጅት ላይ እንደሆነ እንዲሁም የራሱን የፕሮዳክሽን ኩባንያም እንደሚኖረውም ጆኒ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

የግብይት ስርዓቱ በዋናነት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የሚሠራ ሲሆን የአከፋፈል ሁኔታውንም በሚመለከት ኢትዮ ቴሌኮም ከጠቅላላ ገቢው 30 በመቶ የሚሆነውን እንደሚወስድ ጆኒ ራጋ ለአዲስ ማለዳ ያረጋገጠ ሲሆን፤ ቀሪው 70 በመቶ እንደ 100 በመቶ ተወስዶ ከዛ ውስጥ 54 እጁን ለሙዚቀኛው ገቢ እንደሚደረግ እና ቀሪው ደግሞ ለአውታር የቴክኖሎጂ ቡድን እና ለባለቤቶች እንደሚከፋፈል ታውቋል። ስለ አውታር የቴክኖሎጂ ቡድን ጆኒ ሲያብራራ፤ መተግበሪያውን ከማጎልበት ጀምሮ ጠንካራ የመቆጣጠሪያ ቋት እስከ የማስተዳደር ድረስ የሥራ ድርሻ ያለው ሌላ አካል እንዳለ እና እነሱም የገቢው ተካፋይ እንደሆኑ ጠቁሟል።

አውታር የሙዚቃ መገበያያ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ላሉ የኢትዮጵያ ሙዚቃን ለማዳመጥ ለሚፈልጉ ተጠቃሚዎች ዓለም አቀፍ የገንዘብ መክፈያዎችን ወይም ካርዶችን ተጠቅመው መግዛት እንደሚችሉ ታውቋል። በዚህም ምክንያት የሙዚቃው ዘርፉ ለኢትዮጵያ የውጪ ምንዛሬ ግኝት የራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጀምራል እንደማለት ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 31 ሰኔ 1 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here