የንግድ ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ተጠየቀ

0
481

መንግሥት ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ በዘረጋው የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ላይ በ2009 እና በ2010 በጀት ዓመት ተግባሩን በሚገባ ባልተወጡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ተጠየቀ። ባንኩ በአዋጅ በተሰጠው ኀላፊነት መሰረት ፈንዱ በሕጋዊ መንገድ ለተጠቃሚዎች መተላለፉን መቆጣጠር እና እንዲተላለፍ ማድረግ ያለበት ቢሆንም ይህን አለማድረጉ በባንኩ የሥራ ኀላፊዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ፌደራል ዋና ኦዲተር ጠይቋል።

ባንኩ አዋጁ ከሚፈቅደው ውጪ የወከላቸው በሁለም ክልል የሚገኙ የፋይናንስ ቢሮዎች በአካባቢያቸው በሚገኙ ማይሮፋይናንስ ተቋማት በኩል ከ9 ነጥብ 1 ቢሉዮን ብር በላይ ለተጠቃሚዎች በብድር መልክ እንዲሠራጭ ያደረገ ሲሆን፤ ይህን ተከትሎም በድሬደዋ ከተማ በሚገኙ ዘጠኝ ቀበሌዎች ከፈንዱ 8 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የወሰዱ 105 ኢንተርፕራይዞች በሥራ ላይ የማይገኙ (የሌሉ) መሆናቸው ተረጋግጧል።

የፌደራል ዋና ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ እንደተናገሩት ባንኩ ከሚመለከታቸው ጋር በመመካከር ፈንዱ ለተጠቃሚዎች የሚተላለፉበትን ደንቦች ሊወስን እንደሚገባ በተዘዋዋሪ ፈንድ ማቋቋሚያ አዋጅ የተደነገገ ቢሆንም፤ ከዚህ ተቃራኒው ባንኩ እስከ 2011 ዐሥረኛው ወር ድረስ ፈንዱ ለተጠቃሚዎች የሚተላለፍበትን ደንቦችና መመሪያዎች ያልወሰነ ሲሆን፤ ከዚህም ጋር ተያይዞ ለወጣቶች ከተመደበው 10 ቢሊዮን ብር ውስጥ እስከ ጥር 2011 ዘጠኝ ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ወጪ ሆኖ ለተጠቃሚዎች እንዲተላለፍ አድርጓል።

በተመሳሳይ በድሬደዋ መስተዳደር በገጠር ቀበሌዎች ከሚገኙ ሦስት ክላስተሮች በድምሩ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ገደማ ከፈንዱ ብድር ወሰዱ 19 ኢንተርፕራይዞች በሥራ ላይ የሌሉ ወይም የማይገኙ መሆናቸውን በ10/04/2011 ከድሬ ብድርና ቁጠባ ተቋም በተገኘ የሰነድ ማስረጃ ለማወቅ ተችሏል።

በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ከአዲስ በድርና ቁጠባ በጥር 2011 የተገነው የሰነድ መረጃ እንደሚያመለክተው ከፈንዱ 21 ሚሊዮን ብር ብድር የወሰዱ 124 ኢንተርፕራይዞች በአሁኑ ሰዓት በሥራ ላይ የማይገኙ ወይም የሌሉ መሆናቸው ተረጋግጧል።

የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድን በሚመለከት ደንብና መመሪያ አልወጣለትምና አፈፃፀሙ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የሚኒስቴሩን የዐሥር ወር የዕቅድ አፈፃፀም ባቀረቡበት ወቅት ጥያቄ ቀርቦላቸው ምላሽ ሰጥተውበታል። ተዘዋዋሪ ፈንዱን የሚያስተዳድሩት ክልሎች ስለሆኑ የተጠቃለለ ሪፖርት እንዳልደረሳቸው እና መመሪያና ደንብም በቅርቡ እንደሚወጣለት ተናግረዋል።

የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ለወጣቶች ከተሠራጨው ብር ውስጥ አንድ በመቶ የሚሆነው እንኳን እስካሁን እንዳልተመለሰ መግለፃቸው የሚታወስ ነው። ዋና ኦዲተሩም እንደገለፁት ተዘዋዋሪ ፈንዱ እንደ ሥሙ የሚዘዋወርና ኹሉንም የሚጠቅም መሆን እንደሚገባውና አንድ ቦታ ተይዞ የሚቀር መሆን እንደሌለበት ጠቁመዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 31 ሰኔ 1 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here