የኦዲት ግኝቶች ላይ ተጠያቂነት እንዲጣል የሚያደርግ የውሳኔ ሐሳብ ጸደቀ

0
805

በበርካታ የባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ላይ የሚታየውን ከፍተኛ የኦዲት ግኝት ተከትሎ በዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ሪፖርት ላይ የተጠቀሱ ተቋማት ተጠያቂነታቸውን የሚያረጋግጥ ረቂቅ ለመጀመሪያ ጊዜ ፀደቀ። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ መሐመድ ዩሱፍ ለምክር ቤቱ እንዳስታወቁት፤ ለኦዲት ግኝቶች ከዓመት አመት እንዲቀረፉ አለመደረግና ብሎም እየባሰ መምጣት የኦዲት ግኝቶችን ተከትሎ ማስተካከያ አለመደረግ ነው ሲሉ ይገልፃሉ።

አዋጁ በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 12 ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት አድርጎ የተረቀቀ ሲሆን ይህም በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 12 (2) ላይ ማንኛውም ኀላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኀላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚሆን እንደሚደነግግና አዲሱ ረቂቅ አዋጅም ይህን ተግባራዊ የሚያደርግ እንደሚሆን ተጠብቋል። አያይዘውም ማስተካከያ በማያደርጉ መስሪያ ቤቶች እና የሥራ ኀላፊዎች ላይ ተጠያቂነት ባለመኖሩ ችግሩ ሥር እንዲሰድ በማድረጉ የሚጸድቀው ረቂቅ ከዚህ ቀደም የታዩ ችግሮችን ከመቅረፍ አንፃር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል።

የኦዲት ግኝቶች ተብለው በፌደራል ዋና ኦዲተር ከተለዩ እና ማስተካካያ ካልተደረገባቸው በሚመለከተው አካል ተጠያቂነትን ያስከትላሉ የተባሉ ክፍተቶች በግልጽ ተቀምጠዋል። በዚህም መሰረት የመንግሥት ግዥና ፋይናንስ ስርዓትን ባልተከተለ መልኩ ግዥና ክፍያ መፈጸም፣ በሥራ ላይ ላልተገኘ ወይም ከሥራው ለለቀቀ ሠራተኛ ደመወዝ መክፈል፣ ከውዝፍ ተሰብሳቢ ሒሳብ ላይ ተገቢውን እርምጃ አለመውሰድ በተደጋጋሚ ቅሬታ የሚነሳባቸው ክፍተቶች ናቸው።

ይህንም ተከትሎ ቀደም ባሉት ዓመታት የተፈፀሙ የሐብት ብክነትና ምዝበራ በተመለከተ በሕግ አግባብ እርምጃ ተወስዶ የሕዝብና የመንግሥት ገንዘብ እንዲመለስ እንዲደረግ የውሳኔ ሐሳብ ከቋሚ ኮሚቴ ቀርቧል። ተያይዞም ሕግና አሰራር የጣሱ በየደረጃው የሚገኙ የሥራ ኀላፊዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ተወስዶ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥም በውሳኔ ሐሳቡ ላይ ተካቷል።

ለበርካታ ዓመታት ማስተካከያ እርምጃዎች ባለመወሰዳቸው መጋቢት 16/2011 ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች በተገኙበት ምክር እና አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ባስቀመጡት አቅጣጫ የኦዲት ግኝት የታየባቸው መሥሪያ ቤቶች በኹለት ወራት ጊዜ ውስጥ ማስተካካያ እንዲያደርጉ መጠየቃቸው የሚታወስ ነው። ይሁን እንጂ ግንቦት 13/2011 ዋና ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ ለሕዝብ እንደራሴው የ2010 በጀት ዓመት የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን የፋይናንስና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት የጊዜ ገደብ ከተሰጣቸው መስሪያ ቤቶች ውስጥ አምስት የሚሆኑት ብቻ ማስተካከያ እንዳቀረቡ መናገራቸው ይጠቀሳል።

በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ላይ የፌደራል ዋና ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን ሲሰጡ እንደተናገሩት “የሕግ ተጠያቂነቱን በተመለከተ አስጸድቀናል፤ ከዚህ በኋላ የሚመለከተው አካል ተከታትሎ ማጽደቅ ይኖርበታል” ሲሉ ገልጿል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በኩልም የረቂቁ መጽደቅ ዓይነተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አስታውቀው በቀጣይ በመሥሪያ ቤቱ በኩል ውይይት ተደርጎ አቅጣጫ እንደሚቀመጥለት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው ዝናቡ ቱኑ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በዚሁ ቀን ከምክር ቤት አባላት ምክር ቤቱ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች እየተከበሩ ስላልሆነ በተለይ ደግሞ የኦዲት ግኝት ያለባቸው መሥሪያ ቤቶች ከአመት ዓመት መሻሻል ባለማሳየታቸው ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊያነጋግሩን ይገባል የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተው ነበር። በዚህም መሰረት የውሳኔ ሐሳብ ተዘጋጅቶ ምክር ቤቱ ያጸድቀውና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የውሳኔ ሐሳቡን መነሻ አድርገው አስተያየት እንዲሰጡበት አቅጣጫ መቀመጡ ተጠቅሶ፤ የውሳኔ ሐሳቡ በኹለት ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ጽድቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 33 ሰኔ 15 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here