የማኦኮሞ መጠለያ በሱዳን ስደተኞች ጥቃት እየደረሰበት ነው

0
670

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚገኘው የማኦኮሞ የዱር እንስሳት መጠለያ ጣቢያ በደቡብ ሱዳን ስደተኞች ተደጋጋሚ የደን ጭፍጨፋ እየተካሔደበት መሆኑ ታወቀ። ስደተኞቹ ለአደን ወደ ፓርኩ እንደሚገቡም ለማወቅ ተችሏል።

ከማኦኮሞ የዱር እንሰሳት መጠለያ በ100 ሜትር ርቀት ላይ የተሠራው የቶንጎ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ የሚገኙት የደቡብ ሱዳን ስደተኞች፣ ለቤት መሥሪያና ለማገዶ የሚሆን እንጨት እየቆረጡ ከመውሰዳቸውም ባለፈ በዱር እንስሳት መጠለያ ውስጥ የሚገኙትን እንስሳቶች ጭምር እንደሚያድኑ፥ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የፓርክና የዱር እንስሳት ልማት ጥበቃ ኀላፊ ሳሙኤል አድማሱ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ሳሙኤል ስደተኞቹ በእንስሳት መጠለያው ላይ ጉዳት ሲያደርሱና ያንንም ለመከላከል በሚደረገው ጥረት በሚፈጠረው ግጭት የኢትዮጵያ መንግሥት ለስደተኞቹ በመወገን “ስደተኞችን እንዴት ትነካላችሁ?” በማለት ከእነሱ ጎን እንደሚቆም ያወሱት ሳሙኤል፥ የፌደራል መንግሥት ስደተኞቹ እንዲነኩበት አይፈልግም በማለት ይናገራሉ። በዚህም ምክንያት ከመጠለያው በሚወስዱት የማገዶ እንጨት ምክንያት መጠለያው ጉዳት እየደረሰበት መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።

ለፓርኩ የተሰጠ ምንም ዓይነት ዋስትና አለመኖሩን የሚናገሩት ሳሙኤል፣ ችግሩን በተወሰነ ደረጃ ለመቅረፍ እንዲያስችል፣ ከክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር፣ ከዚህ በፊት ለስደተኞቹ ብቻ ይቆረቆር የነበረው የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ፣ የጉዳዩን አሳሳቢነት እንዲመለከተው በመደረጉ፣ በመጠለያ ካምፑ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች እያደረሱ ያሉትን ጥቃት በመረዳት ችግሩን በዘላቂነት ለማስወገድ አብሯቸው እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

እንደ ሳሙኤል ገለጻ፣ በአካባቢው በቶንጎ ከተማ ሸለም በሚባለው ተራራ ዳርቻዎች ላይ የስደተኞቹ ካምፕ የተሠራው በቂ ጥናት ሳይደረግበት ነው። በአሁኑ ወቅት በቤኒሻንጉል ክልል ከአራት በላይ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ያሉ ሲሆን በቶንጎ ከተማ ብቻ ከኹለት ሺሕ በላይ ስደተኞች ይገኛሉ።

2014 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የማኦኮሞ የዱር እንስሳት መጠለያ ስፍራ በርካታ የአንበሳ መንጋ፣ ብርቅዬ አዕዋፋት፣ የተፈጥሮ ፍል ውሃና በርካታ እንስሳቶች እንደሚገኙበት የነገሩን ሳሙኤል፥ ማኦኮሞ በክልሉ ከሚገኙት አራት የዱር እንስሳት መጠለያ ጣቢያዎች አንዱ መሆኑን ይናገራሉ።

በ2007 የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ባሕልና ቱሪዝም ከፌደራል የዱር እንስሳት ልማት ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በመሆን ባካሔደው ጥናት መሰረት፣ ማኦኮሞ የዱር እንስሳት መጠለያ እንዲሆን የወሰነ ሲሆን፣ የበረሃማነት መስፋፋትን እንዲቀንስና የአየር ሁኔታውን ጠብቆ እንዲቆይ ታስቦ የተሠራ መሆኑንም አክለው አስታውቀዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ ሽመልስ እንድሬ፣ በማኦኮ የዱር እንስሳት መጠለያ ጣቢያ ላይ እየደረሰ ያለውን ጥፋት ለማስቆም ከፌደራል አካባቢ፣ ደንና የአየር ለውጥ ሚኒስቴር ጋር በመሆን በመሥራት ላይ እንደሚገኙ አስታውቀው፣ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ስለ ደንና አካባቢ ጥበቃ ያላቸው እውቀት አነስተኛ በመሆኑ እነሱን በማስተማርና በማሠልጠን የባለቤትነት ስሜት እንዲኖራቸው ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 33 ሰኔ 15 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here