የፀረ ሽብር ሕግ ሰለባዎች የአዲስ አበባ ከንቲባ እያጉላሉን ነው ሲሉ ወቀሱ

0
826

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑ 250 የፀረ ሽብር ሕግ ሰለባዎች የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ እናቋቁማችኋለን ብለው ቃል ከገቡ 10 ወራት ቢያልፉም እስካሁን የተደረገልን ነገር የለም ሲሉ ወቀሳ አቀረቡ።

እንደ ቅሬታ አቅራቢዎቹ መንግሥት፣ በእስር ብዛት እና በድብደባ ጤናቸው፣ ኢኮኖሚያቸው፣ ሥነ ልቦናቸው ጭካኔ በተሞላበት ቅጣት ተናግቷል። ለቤተሰብ መበታተን፣ ለአካል ጉዳት እና ለሌሎች ማኅበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊና ለጤና ችግር ተዳርገዋል።

ለዚህ አስከፊ መከራ የተዳረግነው መንግሥት በአገሪቱ ላይ ባወጀው የፀረ ሽብር አዋጅ ምክንያት ነው የሚሉት የጥቃቱ ሰለባዎች በአጠቃላይ በርካታ ችግሮችን አልፈው ዛሬ ላይ መድረሳቸውን ጠቅሰው፥ መንግሥት እንዳመነው ባደረሰብን ኢ-ሰብኣዊ እርምጃ ምክንያት ሕይወታችን ተመሰቃቅሏል፤ ዕድሜያችን ባክኗል፤ ጤናችን ታውኳል፤ ከእስር ወጥተን የተረከብናቸውን ቤተሰቦቻችንም ሆነ ራሳችንን ማኖር አቅቶናልና ሲሉ ለአዲስ ማለዳ በላኩት ጽሁፍ አስታውቀዋል።

“ካሳ ይሰጠን ሳይሆን ማንም ሰብኣዊነት የሚሰማው አካል ወይም ግለሰብ እንደሚያደርገው ሁሉ መንግሥት ያቋቁመን” በሚል አንድ ዐቢይ ኮሚቴ አቋቁመው ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውንም ገልጸዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል ጥር 25/2011 የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ፥ ጠበቆች እና ሚዲያዎች በተገኙበት በካፒታል ሆቴል ከጥቃቱ ሰለባዎች ጋር ሰፊ ውይይት ማካሔዳቸው ይታወሳል። የዚሁ መድረክ ቀጣይ ክፍል የሆነውና የፀረ ሽብር አዋጅ ተጎጂዎች ሰኔ 4/2011 ግማሽ ቀን የፈጀ ስብሰባ በመላው ኢኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ጽሕፈት ቤት አዳራሽ አድርገዋል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ፕረስ ሴክሬታሪ ፌቨን ተሾመ፥ ልናስተናግዳቸው ፈቃደኛ ነን ያሉ ሲሆን ጥቃት የደረሰባቸው ወገኖች በርካታ ናቸው። ከዚህ ማኅበር ውጪ ያሉ ብዙ ሰዎች ወደ አስተዳደሩ በመሔድ ድጋፍ ይጠይቃሉ። ለአንዱ ሰጥቶ አንዱን መንፈግ ግን አይቻልም።

ብዙ ጊዜ የማኅበሩን አመራሮች ጠርተው እንዳነጋገሯቸው ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት ፌቨን፥ በማኅበሩ አባላት ውስጥ ያሉት ሰዎች ፍላጎት ግን የተለያየ ነው ብለዋል። ሕክምና የሚፈልጉ፣ ከሥራ የተባረሩ፣ በዘላቂነት ተደራጅተው ሥራ መሥራት የሚፈልጉ፣ አቅመ ደካሞች ሆነው መጠለያ ቤት የሚፈልጉ በሚል በዝርዝር የተቀመጠ እና የማህበሩ አባላትን ጥያቄ የያዙ ግልጽ የሆነ ነገር አቅርቡልን ብለናቸው ዳግመኛ አልመጡም ብለዋል።

በአንዳንድ የማኅበሩ ሰዎች ሌላ ፍላጎት መኖሩን የሚናገሩት ፌቨን፣ ኮንዶሚኒየም ቤት የሚፈልጉ በርካታ ሰዎች መኖራቸውንም አክለው ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከፍተኛ የሆነ የቤት ፍላጎት መኖሩን የሚያነሱት ፌቨን፥ በሁሉም የሙያ ዘርፍ ላይ የሚገኙ ማኅበራትና ተቋማት የቤት ጥያቄ ከማንሳት ወደ ኋላ ብለው እንደማያውቁ ይናገራሉ። እሳቸው እንደሚሉት፣ የከተማ አስተዳደሩ ጥያቄያቸውን ግልጽ አድርገው ከመጡ ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል።

ቅጽ 1 ቁጥር 33 ሰኔ 15 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here