የመንግሥት ተቋማት በሙስና ዙሪያ የቀረበውን ስትራቴጂ እየተገበሩ አይደለም

0
257

የፌዴራል ሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ለሙስና ተጋላጭ በሆኑ ዘርፎች ላይ ስትራቴጂ ቢያቀርብም ተቀብሎ የሚተገብር ተቋም እንደሌለ አስታወቀ። ኮሚሽኑ የማሻሻያ ስትራቴጂ ካቀረበባቸው 280 ተቋማትም ውስጥ 196 ስትራቴጂውን ለመተግበር ፈቃደኛ ሆነው አለመገኘታቸው ታወቀ።

ኮሚሽኑ የሙስና እንቅስቃሴና ሥጋት በሚታይባቸው ዘርፎች ላይ አዲስ አበባን እና ድሬዳዋን ጨምሮ፣ የሚታይባቸውን ሥነ ምግባር ክፍተት ለመለወጥ ስትራቴጂውን እንዲተገብሩ ከተደረጉ 280 ተቋማት ውስጥ 84ቱ ብቻ ፍቃደኛ ሆነው ወደ ማሻሻል ሲገቡ፣ የተቀሩት 196 ተቋማት ይህን ስትራቴጂ ተቀብሎ ለመተግበር ዝግጁ አለመሆናቸውን የኮሚሽኑ የጥናትና ለውጥ ዳይሬክተር ተስፋዬ ሻሜቦ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ለዚህ ደግሞ ዋነኘው ምክንያት የተቋሙ አመራር ሙስናን ለመከላከል ቁርጠኛ ካለመሆኑ የተነሳ፣ እንዲሁም ደግሞ በተቋሙ ሙስናን ተከላክሎ ለሕዝቡ ግልጽነት የተሞላበት አገልግሎት ለመስጠት ያለመዘጋጀትና ለነገሩ ቦታ አለመስጠት እንደሆነም ጨምረው ገልፀዋል።

ተስፋዬ እንዳሉት፣ ኮሚሽኑ በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሰረት በተለያዩ ጊዜያት የሙስና ሥጋት እና እንቅስቃሴ በሚታይባቸው እንደ መሬት አስተዳደር፣ ገቢዎች እና መሠል ሴክተር መሥሪያ ቤቶች እንዲጠኑ ተደርጎ ምክረ ሐሳብ ቢቀመጥም ስትራቴጂውን ተጠቅሞ ችግሮችን ለማሻሻል የሚሞክር መሥሪያ ቤትም ሆነ የበላይ አመራር የለም።

ኮሚሽኑ ሰኔ 8/2011 በአዳማ ከተማ ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች እና አባላት በሰጠው ሥልጠና ላይ እንዳስታወቀው፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚገኙ የሥነ ምግባር መኮንኖች እንደጠላት እየተቆጠሩ፣ ቢሮ እንኳን የሌላቸው ባለሙያዎች መኖራቸውን ተናግሯል። እነዚህንም ባለሙያዎች ወደ ሥራቸው እንዲገቡና እንቅፋት እንዳይገጥማቸው የምክር ቤቱ አባላት ይረዱናል ብለን ተስፋ እናደርጋለንም ብለዋል።

ጠንካራ አገር ለመገንባትም ሆነ ሙስናን መከላከል ወሳኝ በመሆኑ ሰፊ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ በዚህ ወቅት መንግሥት ጠንካራ አቋም ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሆነ ገልጸዋል።

በምክክሩ ወቅትም የፌዴራል ሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አትክልቲ ግደይ፣ ጊዜ እና ገንዘብ የፈሰሰባቸውን ጥናቶች የመደርደሪያ ማሞቂያ ከመሆን ወጥተው የጥናቱ ውጤት ታይቶ የሚታረመው እንዲታረም፤ የሚገሰጸው እንዲገሰጽ መሠራት እንዳለበት አሳስበዋል።

ስትራቴጂክ ትግበራውን በአግባቡ መርምሮ የሚያያቸው የለም እንጂ፣ እንደ አገር ብዙ ብክነቶችን ልንከላከልባቸው እንችል ነበር ያሉት ተስፋዬ፣ አሁንም ቢሆን አልረፈደም የተጠኑትን ጥናቶች በመተግበር የአዲስ አበባ መስተዳድር ምክር ቤት አባላት እና ቋሚ ኮሚቴዎች ጋር በመተባበር ለመሥራት ተዘጋጅተናል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 33 ሰኔ 15 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here