ሩብ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ መግባት ከነበረበት ጊዜ መዘግየቱ ታወቀ

0
480

እየተገባደደ ባለው በጀት ዓመት መጀመሪያ ወራት ላይ ከተፈፀመው የማዳበሪያ ግዢ ሩብ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የሚሆነው ወደ አገር ውስጥ መግባት ከነበረበት ጊዜ መዘግየቱ ታወቀ። መንግሥት በ400 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ግዥ የፈፀመው 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሲሆን ከግማሽ የሚልቀውን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባትና ለማራገፍ የተቻለ ቢሆንም 250 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የሚሆነውን በተፈጠረ የትራንስፖርት እጥረት ማስገባት እንዳልተቻለ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

የኮርፖሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አማረች በቀለ ለአዲስ ማለዳ ሲገልፁ እንደተናገሩት፤ ግዥ የተፈፀመበት ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ ጠቅልሎ መግባት ነበረበት ከወራት በፊት መሆኑን ጠቁመው ባጋጠመው የመርከብ ትራንስፖርት ችግር መዘግየቱን አስታውቀዋል። አያይዘውም ወደ አገር ውስጥ የሚገባው ብዛት ያለው የዕርዳታ ስንዴ የትራንስፖርት ችግር እንዲፈጠር ምክንያት እንደሆነው ተናግረዋል። አሁን ላይ ዐሥር መርከብ የሚሆን ማዳበሪያ ማስገባት ያልተቻለ ሲሆን እያንዳንዱ መርከብ በአማካይ 25 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ የመሸከም አቅም እንዳለው ታውቋል።

ማዳበሪያዎቹ መግባት ከነበረባቸው ጊዜያት በመዘግየታቸው ለአርሶ አደሮች የሚከፋፈሉበትን የጊዜ ገደብ የሚያዛንፍ እንደሆነና ዘር ከሚዘራበት ወራት በፊት አስቀድሞ መድረስ እንዳለባቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ ኮርፖሬሽኑ ይህንም ከግምት ውስጥ በማስገባት ወደ አገር ውስጥ በገባው ማዳበሪያ የማብቃቃት ሥራ በመሥራት ፍላጎቶችን እያረጋጋ እንደሚገኝ ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል። ኮርፖሬሽኑ አያይዞም ዘግይቷል የተባለው ማዳበሪያ ከሰኔ መጨረሻ እስከ ሐምሌ የመጀመሪያ ዐሥር ቀናት ውስጥ ተጠናቆ ይገባል ተብሎ ተስፋ እንደተጣለበት ጠቁሞ፤ ከታሰበው ጊዜ ከዘገየ ግን ትልቅ ጫና እንደሚፈጥር ከወዲሁ አስታውቋል።

ኦሲፒ ከተባለው የሞሮኮ ኩባንያ ግዢ ለመፈፀም ወደ ሥራ በተገባበት ወቅት ከኩባንያው ወገን የተጋነነ ዋጋ በመቅረቡ ጉዳዩ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ሲመከርበት እንደነበርና በድጋሚ ከፍተኛ ድርድር ተደርጎ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያን በ400 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ተቆርጦለት ወደ ግዥ እንደተገባ የሚታወስ ነው። ይህ ደግሞ ኩባንያው ከኹለት ዓመት በፊት ከአንድ ቶን እስከ 85 ዶላር ጭማሪ በማድረጉ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለኹለተኛ ጊዜ ጨረታ ለማውጣት ከተገደደበት ጊዜ ጋር ተመሳሳይ ያደርገዋል። በዚህ ዓመትም በተደረሰው የዋጋ ድርድር መሰረት ኩባያው ኤንፒኤስ፣ ኤን ኤስ ቢ፣ ኤን ፒ ኤስ ዜድ ኤን ቢ የተባሉ የተለያዩ ዓይነት ማዳበሪያዎችን ለማስረከብ ውል አስሮ የማጓጓዙ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ታውቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 34 ሰኔ 22 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here