መንግሥት የሕግ ልዕልናን ያክብር፤ ያስከብር! በቀውስ ጊዜ የዜጎች የመረጃ ማግኘት መብት ይከበር!

0
992

ቅዳሜ፣ ሰኔ 15/2011 በአማራ ክልል መንግሥት ላይ የተቃጣው እና በመንግሥት “መፈንቅለ መንግሥት” የተባለው ደም አፋሳሽ አጋጣሚ የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር የነበሩትን አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) እና “ግድያውን መርተዋል” የተባሉትን ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ጽጌን ጨምሮ የአራት ከፍተኛ የክልሉን ባለሥልጣናት ሕይወት ቀጥፏል። ከዚሁ አሳዛኝ ግድያ ጋር ግንኙነት አለው ተብሎ በተገመተ ሌላ ጥቃት የጦር ኀይሎች ኢታማዦር ሹሙ ጀነራል ሰዓረ መኮንን እና ጡረተኛው ሜጀር ጀነራል ገአዚ አበራ ነፍስ ተቀጥፏል። እስካሁን ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች “ከመፈንቅለ መንግሥቱ” በተያያዘ በኹለቱም ወገኖች ሕይወት ቀጥፏል፤ በርካታ ጉዳትም አድርሷል። በአጭሩ ሰኔ 15 ቀን 2011 በኢትዮጵያ ታሪክ ጥቁር ጠባሳ አሳርፏል፤ መዘዙ ግን ቀጣይነት አለው። አዲስ ማለዳም በዚህ ነፍስ የቀጠፈ አሳዛኝ ገጠመኝ የተሰማትን ሐዘን ትገልጻለች።

ይሁንና ግድያው በተፈፀመ አጭር ጊዜ ውስጥ መንግሥት የተከሰተው “የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነው” በሚል የችግሩን ምንነት በፈለገው መንገድ ከገለጸ በኋላ፥ ኢንተርኔትን በመዝጋት በርካታ የመረጃ ፍሰት እንቅፋቶችን ጥሎ ጉዳዩ ምንም ሳይመረመር እና በነጻ አካላት መንግሥት ከሰጠው መረጃ ውጪ ምንም ዓይነት የማጣራት ሥራ ሚዲያዎች መሥራት የማይችሉበትን ድባብ ፈጥሯል።

አዲሱ የኢሕአዴግ አመራር ሥልጣን ከተቆጣጠረ ወዲህ ኢንተርኔት እንዲቋረጥ ሲደረግ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። በዚሁ ወር የአገር ዐቀፍ ፈተናዎች ስርቆትን ለመከላከል ይሆናል ተብሎ በተጠረጠረ ምክንያት ተቋርጦ ሰንብታል። በዚህ ጊዜ ኢንተርኔት እንዲዘጋ ያዘዘው የመንግሥት ተቋም ማን እንደሆነ እና ለምን እንዲዘጋ እንደወሰነ ባለመናገሩ ምክንያት “ግምቱ” ብቻ እንደ እውነት ተቆጥሮ ቀርቷል። ይህ አሳፋሪ ድርጊት ዜጎቹን ከሚያከብር አስተዳደር የማይቆጠር ቢሆንም የተጠናከሩ ተቋማት ባለመኖራቸው ማንም የመንግሥት አካል ተጠያቂ አልሆነም።

ከዚህም በላይ ብዙ ነገሩ ተድበስብሶ የቀረው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ‘ፑሽ አፕ’ በማሠራቱ የሚታወሰው የታጠቁ ወታደሮች ሰልፍ ጉዳይም ከዚህ ተለይቶ አይታወስም። መንግሥት የኢንተርኔት ግንኙነትን በማፈን እና የመንግሥት ብዙኀን መገናኛ ብቻ በተገኘበት “የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ” ተብሎ ከተነገረ ከቀናት በኋላ፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እርሳቸውን ለመግደል የተቀነባበረ ሴራ እንደሆነ ሌላ ጊዜ እንደዋዛ ተናግረዋል። በዚህ ሳቢያም የሰልፉ መሪዎች መታሰራቸው ይታወሳል። ከዚህ ውጪም የቡራዩውን ጥቃት ተከትሎ በአዲስ አበባ ተቃውሞ ሲቀሰቀስ፥ ኢንተርኔቱ ተዘግቶ የተቃውሞ ማፈኛ መሣሪያ ሆኗል።

ኢንተርኔት በጠፋባቸው ወቅቶች በርካታ ዜጎች ማወቅ የሚገቧቸው ነገሮች ሳይታወቁ ያልፋሉ። ከላይ የጠቀስነው የወታደሮቹ ሰልፍ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ፥ የአሁኑ የግድያ ቀውስ ሲከሰት መንግሥት “እኔ ያልኳችሁን ብቻ እመኑ” ማለት የፈለገ ይመስል፥ “መፈንቅለ መንግሥት ነው” ከማለቱ በስተቀር፣ ድርጊቱን መፈንቅለ መንግሥት የሚያሰኘው የትኛው ባሕሪው እንደሆነ አልተገለጸም። ተጠርጣሪው ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው የተጠረጠሩበትን ጥቃት ለመፈፀም ምን አነሳሳቸው? የግል ፀብ? የሥልጣን ሽኩቻ? ወይስ ሌላ? በአዲስ አበባው ጥቃት እና በባሕር ዳሩ ጥቃት መካከል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው? ከዚህ ጥቃት በኋላ በአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ውጪ የታሰሩት ከ200 በላይ የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች እነማን ናቸው? የተጠረጠሩትስ ምን ተገኝቶባቸው ነው የሚሉት ያልተመለሱና ነጻ ብዙኀን መገናኛዎችም ጠይቀው መልስ ያላገኙላቸው ወይም ጥያቄዎቹን ለመጠየቅ የፈሯቸው ጉዳዮች ናቸው።

ከቀውሱ ጋር በተያያዘ የመገናኛ ብዙኀን በተለይ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጣቢያዎች ሥራቸውን በአግባቡ እንዳይሠሩ የዚሁ የኢንተርኔት መዘጋት ጦስ ሆኖባቸው ቆይቷል።

የመገናኛ ብዙኀኖቹ አንድም ኢንተርኔት ባለመኖሩ ምክንያት ሥራቸውን በአግባቡ ለመሥራት በመቸገራቸው፣ አንድም መንግሥት ጉዳዩን በአንድ መልክ ብቻ እንዲታይ በመፈለጉ ግራ በመጋባት እና በፍራቻ ያላቸውን መረጃ ለማስተላለፍ ከመታቀባቸውም በተጨማሪ፣ አዳዲስ መረጃዎችን ፈልገው ማግኘት እንዳይችሉ ሆነዋል። በዚህም ሳቢያ የሐዘን እንጉርጉሮ ወይም በመሣሪያ የተቀነባበሩ ሙዚቃ ከማሰማት ውጪ በራሳቸው መንገድ ስለ ድርጊቱ መዘገብ፣ ጥልቀትና ሥፋት ባለው ሁኔታውን ማስተንተን ሳይችሉ፥ መንግሥት ኢንትርኔቱን ዘግቶ ራሱ በቀረፃላቸው አጀንዳ ዙሪያ ብቻ የገደል ማሚቶ ሆነው ከርመዋል።

አዲስ ማለዳ መገናኛ ብዙኀን ነጻ እና ገለልተኛ ሆነው እንዲቆዩ መረጃ የማግኘት መብት እጅግ የጎላ ሚና እንደሚጫወት ትረዳለች። እንደዚህ ባሉ ከባድ አገራዊ ቀውሶች ወቅት ብዙኀን መገናኛዎች ፈተናዎችን ተጋፍጠው ጠቃሚ መረጃ ለኅብረተሰቡ መስጠት ያለባቸው ቢሆንም፥ መንግሥትም ጋዜጠኞች መረጃ በቀላሉ እንዲያገኙ በመርዳት እና ለደኅንነታቸው ጥበቃ በማድረግ ዜጎች ማወቅ የሚገባቸውን በሙሉ እንዲያውቁ ማድረግ አለበት።

በአጠቃላይ የፖለቲካ ባሕላችን በተለይም ደግሞ የመረጃ አቅርቦት እና ዜጎች መረጃዎችን በፈለጉት መንገድ ተንትነው እና ተረድተው ዕጣ ፈንታቸውን መወሰን የሚችሉበትን ባሕል ለመፍጠር አብዮታዊ ሊባል የሚችል እርምጃ መንግሥት መራመድ እንደሚያሻው አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትፈልጋለች።

መንግሥት ዜጎቹን ፈርቶ መረጃ እንዳያገኙ እና እንዳይለዋወጡ የሚያደርግበት እና መንግሥትና ዜጎች የሚተማመኑበት ስርዓት ካልተዘረጋ በስተቀር ችግሮች በተፈጠሩ ቁጥር ኢንተርኔትን በመዝጋት እና የመረጃ እጥረት ባለበት ሁኔታ የፖለቲካ እርምጃዎችን መውሰድ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባሕል ባለመሆኑ ራሱን የቻለ ሌላ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 34 ሰኔ 22 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here