የትዴት አመራር በመቀሌ ተገዶ መርዝ እንዲጠጣ ተደረገ

0
600
  • አረጋዊ በርሄም ጥቃት እንደተፈጸመባቸው አረጋግጠዋል

በጄነራል ሰዓረ መኮንን እና ሜጀር ጄነራል ገዛኢ አበራ የቀብር ሥነ ስርዓት ላይ ለመካፈል ወደ መቀሌ ያቀኑት የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) የሥራ አስፈጻሚ አባል አማኑኤል ወልደ ሊባኖስ ተገደው መርዝ እንደተጋቱ ፓርቲው ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል። መስከረም ወደሚባል ሆስፒታል ተወስደው ሆዳቸውን ከታጠቡ በኋላ መጠነኛ ለውጥ እንዳሳዩና አሁንም በመቀሌ በሕክምና ክትትል ላይ እንደሚገኙ ተናግሯል።

የተፈጸመውን ጥቃት አስመልክቶ ፓርቲው ለክልሉ መንግሥትና ለፌደራል ፖሊስ ዝርዝር መረጃውን እንዳቀረበም አክለው ተናግረዋል።
ማንነታቸው ባልታወቁ እና በተቀናጁ ወጣቶች ጥቃት መሰንዘሩን ያከሉት የትዴት ሥራ አስፈጻሚ አባል ሙሉብርሃን ኀይሌ ድርጊቱ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል። በጄነራል ሰዓረ መኮንን እና ሜጀር ጄነራል ገዛኢ አበራ ሞት ሁላችንም ሐዘን ተሰምቶን፣ በሰላማዊ መንገድ የቀብር ሥነ ስርዓቱ ሊፈጸም ሲገባው፣ በገዛ ወንድማቸው ላይ እንዲህ ዓይነት ጥቃት መሰንዘራቸው እንዳሳፈራቸው ገልጸዋል።

አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) እና ሙሉብርሃን የቀብር ሥነ ስርዓቱ ላይ ለመገኘት የሰማዕታት ሃውልት ደጃፍ ላይ ሲደርሱ፣ ከውስጥና ከውጭ የነበሩ ካድሬዎች ያደራጇቸው ወጣቶች “መግባት የለባቸውም” የሚል ተቃውሞ በማሰማት፣ ጥቃት ለማድረስ መሞከራቸውን ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት ሙሉብርሃን፣ የክልሉ ፖሊስ ጣልቃ ገብቶ ሊከላከልላቸው እንደቻለ አስታውቀዋል።

እንደ ሙሉብርሃን ገለጻ፣ ከሕዝቡ ጋር ወደ ቀብሩን በማምራት በሩ ላይ ሲደርሱ፣ አንዳንድ ሴቶች ጫማቸውን አውልቀው አረጋዊ በርሄን (ዶ/ር) ለመማታት ሙከራ አደረጉ (የተማቱም አልጠፉም)፤ በወቅቱ በአካባቢው የነበሩ የክልሉ ኀይሎች አረጋዊ በርሄን አጅበው ወደ ውስጥ ሲያስገቧቸው፣ ሙሉብርሃንን ለደኅንነትህ በሚል ይዘውት ሔደዋል።

ይህን ተከትሎም ግርግር በመፈጠሩ ወጣቶቹ በወረወሩት ድንጋይ የፖሊስ አባላት ላይ ጥቃት የተፈጸመ ሲሆን፣ በአካባቢው በነበሩ መኪኖች ላይም ጉዳት መድረሱን ሙሉብርሃን ጠቁሟል። ፖሊስ ግርግሩን ለመቆጣጠርም አስለቃሽ ጭስ ለመጠቀም መገደዱም ታውቋል።

ከግርግሩ በኋላ አረጋዊ በርሄ ወደ ዞኑ የፖሊስ ጽሕፈት ቤት የተወሰዱ ሲሆን፤ ማምሻውን በእንግዳ ማረፍያ ማሳለፋቸውንም ሙሉብርሃን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
‘ባዶ ስድስት’ የሚባል እስር ቤት ውስጥ ታስረዋል የተባለው ስህተት እንደሆነና ሐሙስ ጧት ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን ገልጿል። ጉዳት የደረሰባቸው የፖሊስ አባላት በዓይደር ሆስፒታል ሕክምና እያገኙ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

ትዴት በክልሉ በሚያደርጋቸው ሰላማዊ እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ጥቃት እየደረሰበት መሆኑን የሚናገረው ሙሉብርሃን፣ በጉዳዩ ዙሪያ ከክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጋር ውይይት አድርገው በክልሉ በሰላማዊ መንገድ መንቀሳቀስ እንደሚችሉና እነርሱም ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው ቃል ገብተውላቸው እንደነበር ተናግረዋል። ጉዳዩ እዛ ደረጃ ቢደርስም እስካሁን ያገኘነው እልባት የለም ሲሉም አክለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 34 ሰኔ 22 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here