የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለአይካ አዲስ ቴክስታይል እና ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ያበደረውን ገንዘብ ባለመመለሱ ምክንያት ለመሸጥ ባሳለፍነው ሳምንት ግልጽ ሐራጅ አውጥቷል። ከአንድ ወር በኋላ የሚከፈተው ጨረታ መነሻ ዋጋ 1.8 ቢሊዮን ብር ይሁን እንጂ ቱርካዊያኑ ባለቤቶቹ በ1998 800 ሚሊዮን ብር ቢበደሩም በመጨረሻ ግን የሚጠበቅባቸውን 2.87 ቢሊዮን ብር ሳይከፍሉ ጥለው መውጣታቸው ይታወቃል።
ባንኩ ከዐሥር ወር በፊት አዲስ ዋና ሥራ አስኪያጅ ቀጥሮ የነበረ ሲሆን በባለሞያው ሪፖርት መሰረት ቀጣይ እርምጃዎችን እንደሚወስድም አስታውቆ ነበር። ልማት ባንክ ንበረቶቹን እንዲያስተዳድርለት ያቋቋመው ኢትዮ ካፒታል ኢንቨስትመንት ግሩፕ አይካ አዲስን ጨምሮ በስሩ ያሉ ሌሎች ንብረቶች ወደ ግል ይዞታ እስኪገቡ ድረስ ሲያስተዳድር ቆይቷል።
ኢትዮ ካፒታል ኢንቨስትመንት ግሩፕ ድርጅቱን ሙሉ በሙሉ ሲያስተዳድረው መቆየቱን እና ትርፋማ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ንብረቱን አወዳድሮ ሊሸጥ መሆኑን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
አይካ አዲስ በአንድ ቢሊዮን ብር በተፈቀደ ካፒታል የተቋቋመ ሲሆን በማቋቋም ሒደቱ ወቅትም ሦስቱ ባለንብረቶች ከ800 ሚሊዮን ብር ተበድሮ እንደነበር ይታወቃል።
አይካ አዲስ ቴክስታይል እና ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሐምሌ 16/2011 በሚከፈት ጨረታ የተለያዩ ተሸከርካሪዎችን፣ የማምረቻ መሣሪያዎችን፣ ልዩ ልዩ መለዋወጫዎችን እና እንዲሁም ለጨርቃ ጨርቅ ምርት ግብዓት የሚሆኑ ጥሬ ዕቃዎች እና ተመርተው ሙሉ በሙሉ ያለቁ ዕቃዎችን ጨምሮ በሐራጅ እንደሚሸጥ ለማወቅ ተችሏል።
የቱርክ ዜግነት ባላቸው ባለሀብቶች የተገነባው እና በ25 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው አይካ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በ2002 በ140 ሚሊዮን ዶላር የመነሻ ካፒታል በኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ዓለም ገና ከተማ መመሰርቱም ይታወሳል።
ልማት ባንክ በሐራጅ ለመሸጥ ባወጣው አይካ አዲስ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ላይ ከዚህ ቀደም በሥሩ ያስተዳድረው እንደነበርና በሥራ ላይ እንደነበር ገልፆ ለሥራው ማነቆ የነበሩትን ማሽኖች ለመተካት የተፈፀመ ግዢ ካለ በርክክብ ወቅት ገዢው በአሸነፈበት ዋጋ ላይ ጨምሮ መክፈል እንደሚኖርበት በአፅንዖት አስታውቋል።
በዓለም ገና ከተማ የተመሰረተው ግዙፍ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ሰባት ሺሕ ሠራተኞችን ቀጥሮ የሚያሠራ እና የአገሪቱን የወጪ ንግድ ፍሰት በመጨመር ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቅም ነበር።
ቅጽ 1 ቁጥር 34 ሰኔ 22 2011