አዲስ የሙዚቃ ስልት ይዞ ወደ ሙዚቃው ኢንዱስትሪ ብቅ ያለው ኢትዮጵያዊው ሮፍናን ኑሪ በአፍሪካ ከሰላሳ ዓመት በታች ለውጥ ፈጣሪ በሚል ከምርጥ ሰላሳ ታዋቂ ግለሰቦች በኹለተኛ ደረጃ ሆኖ በፎርብስ መፅሔት ተመረጠ። ደቡብ አፍሪካዊቷን የመንገድ ላይ ሰዓሊ እና ዲዛይነር ካራቦ ፖፒን በመከተል በኹለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የ29 ዓመት ወጣቱ ሙዚቀኛ ሮፍናን ገና የለጋነት ዕድሜው ነበር መክሊቱን ያገኘው ተብሏል።
በኤሌክትሪክ የሙዚቃ ስልት በኢትዮጵያዊያን ዘንድ አድናቆትን በማትረፍም በ2010 በተለያዩ ሦስት ዘርፎች የለዛ ሽልማቶችን መውሰዱ ይታወሳል። በአሁኑ ዙር በፎርብስ ምርጦቹን ያወዳደረበት መንገድም በንግድ፣ በፈጠራ ችሎታ፣ በቴክኖሎጂ እና በስፖርት ሲሆን ሮፍናንንም በምርጥ የፈጠራ ችሎታ ባለቤት ለውጥ አምጪ አድርጎ መርጦታል። ሮፍናን ባለው የፈጠራ ችሎታም በ2009 በአፍሪካ ከተመረጡ ሦስት ዲጄዎች ውስጥ አንዱ በመሆን በስፔን ኢቢዛ ከተማ የሙዚቃ ሥራውን እንዲያቀርብ ተመርጦ ነበር።
ቅጽ 1 ቁጥር 35 ሰኔ 29 2011



