አወዛጋቢው የባሕር ዳር ከተማ የደረቅ ቆሻሻ ማከማቻ ግንባታ ተሰረዘ

0
1002

ከ6 ዓመታት በፊት በባሕር ዳር ከተማ በ10 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ ሊገነባ ታቅዶ የነበረው እና በአርሶ አደሮች ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት የነበረው የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ፕሮጀክት ተሰረዘ። የእርሻ መሬታቸውን በተደጋጋሚ ለተለያዩ የልማት ሥራዎች እየተወሰደባቸው ምክንያት በማድረግ የቀረውን ቦታቸውን ለቆሻሻ ማስወገጃ ፕሮጀክተቱ ላለመስጠት አርሶ አደሮቹ ሲቃወሙ መሰንበታቸው ለፕሮጀክቱ መሰረዝ ምክንያት መሆኑ ታውቋል።

የባሕር ዳር ከተማ አካባቢ ጥበቃ ጽዳትና ውበት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዘላለም ጌታሁን ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት የአርሶ አደሩን ቅሬታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ቀድሞ ከተመረጠው ቦታ 3 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ እና ድንጋያማ ቦታ ላይ ሥራውን ለመሥራት ከወር በፊት ጥናት መጀመረን ተናግረዋል።

ምንም እንኳን አዲስ የተመረጠው ቦታ አርሶ አደሩን የማያፈናቅል ቢሆንም ድንጋያማ ቦታ በመሆኑ ከፍተኛ ወጪ ሊያስወጣ ይችላል ያሉት ዘላለም የአርሶ አደሩን ጥያቄ እስከፈታ ድረስ ግን የክልሉ መንግሥት ፕሮጀክቱን ከግብ ለማድረስ እንደሚሠራ ተናግረዋል። አዲሱን ፕሮጀክት በተመለከተ በክልሉ ኮንስትራክሽን መምሪያ በኩል ጨረታ ወጥቶ ኢንቫይሮመንታል ኢምፓክት አሶሴሽን የተባለ ድርጅት በማሸነፉ ጥናቱን በማካሔድ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።

በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮች በከተማዋ ማስፋፊያ ግንባታዎች ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም መሬታቸው የተወሰደባቸው መሆኑን ጠቅሰው ተለያዩ ቅሬታዎችን ለመንግሥት ሲያሰሙ እንደነበረ ያስታወሱት ዘላለም ይህ የቆሻሻ ማስወገጃ ፕሮጀክት ተፈፃሚ ቢሆን ኖሮ ሙሉ ለሙሉ መሬት አልባ የሚያደርጋቸው እና የባሰ ችግር ላይ ሊጥላቸው የሚቸል ነበርም ብለዋል።

አርሶ አደሮቹም “ከዚህ ቀደም ለዩኒቨርሲቲ እና ለሆስፒታል ማስፋፊያ ሰጥተናል አሁን ላይ ልትወስዱብን ነው” የሚል ተደጋጋሚ አቤቱታ በማቅረባቸው የከተማ አስተዳደሩን ሐሳብ ማስቀየሩንም ተናግረዋል።

አንድ የደረቅ ቆሻሻ መጣያ ስፍራ ብቻ ያላት ባሕር ዳር፥ የቆሻሻ መጣያ ዕጥረት ከ550 ሺሕ በላይ ለሆኑ ነዋሪዎቿ ትልቅ ፈተና እንደሆነባቸው ታውቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 35 ሰኔ 29 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here