ፖሊስ የዛሚ ሬዲዮን ንብረት ቆጠራ አካሔደ

0
542

የፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት በናሁ ቴሌቪዥን እና በዛሚ ሬዲዮ መካከል በተፈጠረው ያለመግባባት አማካኝነት በሰጠው ትዕዛዝ እግድ የተጣለባቸውን የዛሚ ሬዲዮ ንብረቶችን ቆጠራ ግንቦት 26/2011 የጎማ ቁጠባ ፖሊስ ጣቢያ ፖሊሶች እና የወረዳ ተወካዮች በተገኙበት መከናወኑ ታወቀ።
የናሁ ቴሌቪዥን እናት ድርጅት በሆነው ጎልደን ሮስተሪ አመልካችነት በዛሚ ኤፍ ኤም 90.7 ሬድዮ ላይ በቀረበው አቤቱታ መሰረት ኹለቱም ድርጅቶች የግልግል ዳኞቻውን መርጠው ማቅረባቸውን የናሁ ተወካዮች ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቱም የንብረት ምዝገባውን ሪፖርት ከተቀበለ በኋላም ኹለቱ ተዋዋይ ወገኖች የመረጧቸውን የግልግል ዳኞች ካፀደቀ በኋላ አንድ የመንግሥት ዳኛ ይሾማል ተምሎ እንደሚጠበቅ የናሁ ቴሌቪዥን ሥራ አስከያጅ ደረጄ ተክሌ አስታውቀዋል።

ከዚህ ቀደም ግንቦት 26/2010 በፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ የንግድ ችሎት የናሁ ቴሌቪዥን እናት ድርጅት በሆነው ጎልደን ኮፊ ሮስተሪ አመልካችነት በዛሚ ኤፍ ኤም 90.7 ሬዲዮ ላይ በቀረበው አቤቱታ መሰረት የሬዲዮ ጣቢው እንዳይሸጥ እንዳይለወጥ እንዲሁም በድርጅቱ ሥም ተመዝግበው የነበሩ ኹለት ተሸከርካሪዎች ላይ ተመሳሳይ እግድ ማውጣቱ ይታወሳል።

ከወራት በፊት በኹለቱ ድርጅቶች መካከል በተፈፀመው ውል ሬዲዮ ጣቢያውን በ16 ሚሊዮን ብር ለመሻሻጥ ተስማምተው ነበር። ለዚህም ቅድሚያ ክፍያ ወደ 5 ሚሊዮን ብር ገደማ ለሻጮች በቼክ የተፈፀመ ሲሆን ይህም ድርጅቱ ያሉበትን የግብር እዳዎች ፈፅሞ ለመጨረስ እና ከዛም የቀረውን ገንዘብ በመክፈል በአጭር ጊዜ ውስጥ ድርጅቱን ለመረካከብ የተስማሙ ቢሆንም በፊርማቸው ድርጅቱን መሸጣቸውን ያረጋገጡት ግለሰቦች በሚዲያ ወጥተው ድርጅቱ አልተሸጠም የሚል ማስተባበያ በመስጠት እና ውሉንም ለማፍረስ ጥያቄ በመምጣቱ ናሁም የቀረበውን ጥያቄ ተቀብሎታል።

ሆኖም ግን ለቅድመ ክፍያ ያስገቡት ገንዘቡ ሲመለስ ሕጋዊ የባንክ ወለድ ሊሰላበት ይገባል በሚለው ላይ አለመስማማቶች ስለተፈጠሩ ጉዳዩን ወደ ሕግ ወስደውታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 35 ሰኔ 29 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here