በአስመራ የታሸገ ውሃ ፋብሪካዎች በመዘጋታቸው እጥረት አጋጠመ

0
655
  • 1 ነጥብ 5 ሊትር የታሸገ ውሃ እስከ 30 ናቅፋ (60 ብር) ድረስ እየተሸጠ ነው።

በጥሬ ዕቃዎች እጥረትና መንግሥት የውጭ ምንዛሬ ማቅረብ ባለመቻሉ የተነሳ የታሸገ ውሃ ለባለፉት ኹለት ሳምንታት በአስመራ መጥፋቱን አዲስ ማለዳ አረጋገጠች።
በዚህም የተነሳ በኤርትራ ዋና ከተማ በሆነችው አስመራ የሚገኙ ካፌዎች፣ ሬስቶራንቶችና ሱቆች እንዲሁም ሱፐር ማርኬቶች የታሸገ ውሃ መሸጥ ለማቆም መገደዳቸው ታውቋል።

በኤርትራ የሚገኙ የታሸጉ ውሃ የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ለሳምንታት ሥራ ያቆሙ ሲሆን ለዚህም የውጭ ምንዛሬ እጥረት ማጋጠሙን ተከትሎ በተከሰተው የጥሬ ዕቃዎች አቅርቦት መቋረት እንደ ምክንያት ተገልጿል።

ከዚህ ቀደም በመጋዘን ተቀምጠው የነበሩ የታሸጉ ውሃዎች (1 ነጥብ 5 ሊትር) እስከ 30 ናቅፋ (60 ብር) ድረስ እየተሸጡ ሲሆን ይህ አዲስ አበባ ካለው ዋጋ ሲነፃፀር ከአራት እጥፍ በላይ ነው።

ባጋጠመው የውሃ እጥረት የተነሳ በአስመራ የሚገኙ ኤምባሲዎች ለአገሪቷ ፕሬዝደንት ጽሕፈት ቤት ቅሬታ ያቀረቡ ሲሆን አጥጋቢ ምላሽ ማግኘት አለመቻላቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የመንግሥት ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

በተጨማሪ ምንጮች አዲስ ማለዳ እንደገለፁት በኤርትራ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ቀውስ በማጋጠሙ ከውሃ ፋብሪካዎች ባሻገር በሌሎች ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች እንደተዘጉ ለማወቅ ተችሏል።

በተመሳሳይ ችግር የተነሳ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ከኤርትራ ማግኘት አለመቻሉ በሪፖርተር ጋዜጣ ከወር በፊት መዘገቡ ይታወሳል። በዚህም የተነሳ አየር መንገዱ በአስመራ የሚገኙ በዶላር ማስከፈል መጀመሩ ለማወቅ ተችሏል።

ከሰባት የማይበልጡ አገራት ጋር ግንኙነት ያላት ኤርትራ በዓመት 336 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጉ ዕቃዎችን የምታስገባ ሲሆን ወደ 371 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ዕቃዎችን ትልካለች።

በቅርቡ ለኹለት ዐሥርት ዓመታት ተቀዛቅዞ የነበረው ምጣኔ ሀብት ከኢትዮጵያ ጋር የተደረገውን ስምምነት ተከትሎ ተነቃቅቶ የነበረ ቢሆንም ከሰላም ስምምነቱ ማግስት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር መዝጋቷ ቀጣይነቱን አጠራጣሪ አደርጎታል፡፡

አራቱም የሑመራ-ኡማነጀር፣ የዛላንበሳ ፣ ራማ -ክሳድ ዒቓ እና ቡሬ -ደባይ ሲማ ድንበሮች በኤርትራ በኩል የተዘጉ ሲሆን ለዚህም ይፋዊ ምክንያት ባይሰጥም የቪዛና ቀረጥ ጉዳዮች መልክ ለማስያዝ የተደረገ እርምጃ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በሌላ በኩል ድንበሮቹን መዘጋት ተከትሎ የሸቀጦች ዋጋ በኤርትራ እየናረ ሲሆን ለአብነትም ያህል ጤፍ እስከ 3000 ናቅፋ (6000 ብር) ድረስ እየተሸጠ መሆኑ ታውቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 35 ሰኔ 29 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here