የጀጎል ግንብ ከዓለም የቅርስ መዝገብ ሊሰረዝ ይችላል ተባለ

0
991

በተባበሩት መንግሥታት የባሕል የሳይንስ እና ትምህር (ዩኔስኮ) የጀጎል ግንብን እና በውስጡ ያሉ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች፣ በሰው ሰራሽ ችግሮች ምክኒያት ከዓለም ቅርስነት መዝገብ ሊሰረዙ ይችላሉ የሚሉ ሥጋቶች መኖራቸው ታወቀ።

ለስጋቱ መነሻ የሆነውም በጀጎል ግንብ ዙሪያ ሕገ ወጥ ቤቶች በስፋት በመገንባታቸው የቅርሱ ይዘት አደጋ ውስጥ በማግባቱ እንደሆነ የሐረሪ ክልል ባሕል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ አዩብ አብዱላሂ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል፡፡

አዩብ እንደገለጹት፣ በጀጎል አካባቢ የተገነቡት ሕገወጥ ግንባታዎች ሰባ ከመቶ የሚሆኑት ሕጉ ከሚፈቅደው ውጪ በብሎኬት የተገነቡ ናቸው። እነዚህ ቤቶች ሽንት ቤት የሌላቸው በመሆኑ፣ በዛ ያሉ ነዋሪዎች በአካባቢው በመፀዳዳት እና ፕላስቲክ እና ጠርሙስ ጨምሮ ተለያዩ ቆሻሻዎች በአካባቢው እየጣሉ አካባቢውን በመበከል ለጎብኝዎች እንቅፋት መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

ሕገ ወጥ ወራሪዎቹ መድኀኒት የሚሠሩ አድባራትን በመቆጣጠር፣ መድኀኒት እንዳያመርቱ ማድረጋቸውንና በግንቡ ዙሪያ የመኪና እጥበት ሥራ በመሥራት ግንቡ የመፈራረስ አደጋ እንዲገጥመው ማድረጋቸውን የገለጹት አዩብ፣ እነዚህ ሁሉ ችግሮች እንዲቀረፉ ለፌደራል ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን አመልክተው በቂ መልስ አለማግኘታቸውን አስታውቀዋል።

ከ1998 ጀምሮ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ መዝገብ ዝርዝር ውስጥ የተመዘገበውና 66 ሔክታር መሬት የሸፈነው የጀጎል ግንብ ከሰው ሰራሾቹ ችግሮች ባሻገርም እያጋጠሙት ያሉት የተፈጠሮ ችግሮች በቂ ትኩረት አግኝተው ጥገና አለመደረጉንም ያነሳሉ፡፡

በግንብ ዙሪያ ሕገ ወጥ ቤቶች በስፋት በመገንባታቸው፣ ቅርሱን ለአደጋ አጋልጠውታል የሚሉት አዩብ ቅርሶቹ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሳቢያ ከዓለም ቅርስ መዝገብ እንዳይሰረዙ ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የሕዝብና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ምክትል ዳይሬክተር ነጃት ጀማል በጉዳዩ ዙሪያ በሰጡት አስተያየት የሐረር ቅርሶች በራሱ በማኅበረሰቡ ተገቢው ጥበቃ ስላልተደረገላቸው፣ ሕገ ወጥ የቤት ግንባታዎች በመካሔዳቸውና የሕዝብ ቁጥሩ በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ ለአደጋ መጋለጣቸውን ያምናሉ፡፡

በቅርሶቹ አካባቢ የሕዝብ ቁጥር መጨመርን ተከትሎ የተነሱትን ችግሮችን እንደሚያውቁ ጠቅሰው ህዝቡም ለጀጎል ግንብ መደረግ ያለበትን ጥንቃቄ ባለማድረጉ ለመሰነጣጠቅ አደጋ መጋለጡን አውስተዋል፡፡ ይንንም በማስመልከት ከወራት በፊት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ወደ ስፍራው በማቅናት ለኅብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠቱን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በጀጎል አጥር ዙሪያ የውሃ ጉድጓድ እየተቆፈረ የልብስና መኪና ማጠቢያ በመሆኑ አጥሩ ለአደጋ መጋለጡን አዲስ ማለዳ በስፍራው በመገኘት አረጋግጣለች፡፡ በቅርስነት የተመዘገቡት የወሃ መውረጃ ቦዮች እና ቀጫጭን መንገዶች ጥገና ስለማይደረግላቸው አደጋ እየተሸረሸረ መሆኑን ታባለች፡፡ ምንም እንኳን የውስጥ ለውስጥ መንገዶቹ ለመኪና የተከለከሉ ቢሆንም አዲስ ማለዳ መኪኖች እና ባጃጆች በጀጎል ውስጥ ሲንቀሳቀሱም አስተውላለች፡፡

የሐረሪዎች በረዥም ዘመን የሥልጣኔ ታሪካቸው ያፈሯቸው ተንቀሳቃሽ እና የማይንቀሳቀሱ እንዲሁም የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ በርካታ ቁሳዊ እና መንፈሳዊ ቅርሶች ባለቤት ናቸው። ከእነዚህ ቅርሶች መካከልም የከተማዋ ልዩ መለያ ምልክት ከመሆንም አልፎ በ1998 በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የጀጎል ግንብ በቀዳሚነት ይጠቀሳል። በግንቡ ውስጥም ከ82 በላይ መስጊዶች እና በርከት ያሉ የሐረሪ ባሕላዊ ቤቶች ይገኛሉ። ሐረር ከፍተኛ የሥልጣኔ ዕድገት ደረጃ ላይ በደረሰችበት በ16ኛው ክፍለ ዘመንም በምሥራቅ አፍሪካ የእስልምና ሃይማኖት ትምህርት እና የንግድ ማዕከል ሆናም አገልግላለች።

ይህም የበርካታ ታሪካዊ እና ባሕላዊ ቅርሶች ባለቤት እንድትሆን አድርጓታል። የጀጎል ግንብ የሐረሪ ሕዝብ የኪነ ሕንፃ ጥበቡን የሚያስመሰክር የታሪክ እና የጥበብ መዘክር ነው። ይህ ግንብ በ16ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በአሚር ኑር አማካኝነት እንደተገነባም በታሪክ ተመዝግቧል።

ቅጽ 1 ቁጥር 35 ሰኔ 29 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here