አዴፓ ለሕወሓት መግለጫ ምላሽ ሰጠ

0
634

ሐሙስ፣ ሐምሌ 4 የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ በማካሔድ ረቡዕ፣ ሐምሌ 3 ሕወሐት ለሰጠው መግለጫ ምላሽ ሰጥቷል። በመግለጫው አገሪቷ አሁን ለምትገኝበት የፖለቲካ ብልሽት ሕወሓትን ተጠያቂ አድርጓል፤ የሕወሐትን መግለጫም የአማራን ሕዝብ ሕልውናና ክብር የማይመጥን ብሎታል።

ሕወሓት በሰጠው መግለጫ “በአሁኑ ጊዜ አገሪቷን ሊበታትን ያለው ከዚህም ከዚያም የተሰባሰበ የትምክህተኞች ቡድን ነው፤ ይህ ኀይል እንደፈለገ እንዲንቀሳቀስ ዕድል የሰጠው ደግሞ አዴፓ ስለሆነ አዴፓ በአጠቃላይ ስለ ጥፋቱ፤ በፓርቲው አመራር ላይ የተፈፀመውን ግድያ በዝርዝር ገምግሞ ራሱን ተጠያቂ እንዲያደርግ እንዲሁም የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል” ብሏል።

አዴፓ በበኩሉ ሕወሐት በፀረ ለውጥ እንቅስቃሴው አገራዊና ክልላዊ ለውጡ በጥርጣሬ እንዲታይ ከጥፋት ኀይሎች ጀርባ መሽጐ አመራር እየሰጠ ባለበት ሁኔታ፣ ሕዝብና አገር በድፍረት የዘረፉ ሌቦችን፣ በብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ልጆች ላይ ኢ-ሰብኣዊ ድርጊት የፈፀሙ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን አቅፎና ደብቆ በያዘበት ሁኔታ የትህነግ/ሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ያወጣው መግለጫ፤ የዘመናት አስመሳይነቱን ያጋለጠ፣ ራሱን ብቸኛ የኢትዮጵያ ጠበቃ አስመስሎ መቅረቡ የሞራል እና የተግባር ብቃት የሌለው ድርጅት መሆኑ እንዲታወቅም በማለት ወንጅሎታል።

ከዚህም በተጨማሪ አዴፓ በከፍተኛ አመራሮቻችን ላይ በተፈፀመው የግፍ ግድያ ሐዘን ላይ ባለበት ሰዓት ሕወሐት ይህንን መግለጫ ማውጣቱ ከ’እህት’ ፓርቲ እንደማይጠበቅ በመሆኑ ሕወሐት አዴፓን ይቅርታ መጠየቅ እንዳለበት አሳስቧል።

ሕወሓትና መሠል እኩይ ድርጅቶች በሕዝብ ሥም እየማሉና እየተገዘቱ፣ በትግራይ ሕዝብ ሥም እየነገዱ ከሦስት ሺሕ ዓመታት በላይ የዘለቀውን የአብሮነት ታሪካችንን በአራት ዐሥርት ዓመታት የበሬ ወለደ ትርክቶች ለመሸርሸርና ሕዝባዊ አንድነታችንን አደጋ ላይ ለመጣል የሚያደርጉት ሴራ መሆኑን አውቃችሁ ከአማራ ሕዝብ ጋር ያላችሁ ወንድማዊና ቤተሰባዊ ግንኙነታችሁ ሳይቋረጥ ኹለቱን ሕዝቦች የሚያለያዩ ሙከራዎችን በጽናት እንድትታገሉ ሲል ለትግራይ ሕዝብ ጥሪውን አቅርቧል።

ቅጽ 1 ቁጥር 36 ሐምሌ 6 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here