ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የቀቧቸው” የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች

0
701

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ሥራ አስፈጻሚ ሐምሌ 8 ተመስገን ጥሩነህን የክልሉ እጩ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ መምረጡ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኗል። ይነገር ጌታቸው “የፌደራል መንግሥቱ በርዕሰ መስተዳድሩ ምርጫ ላይ እጁን አስገብቶ ይሆን” ሲሉ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቀደምት ንግግሮችና ከሌሎች ክልሎች ርዕሰ መስተዳድር አሿሿም ጋር በማያያዝ ሐሳባቸውን አጋርተዋል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሐቲት የውዝግብን ወዝ የለመደ ነው፤ እዚህም እዛም ያሉ ጉዳዮች ያነታርኩናል። የግለሰቦችን ሹመት በጥርጣሬ ዓይን ማየት ተለምዷዊ ሆኗል። ነገርዬው እርግማን አይመስለኝም። ታሪካችን ጥሎ ማለፍ ነው። ፖለቲከኞቻችን በሴራ እንጅ በሕዝብ ድምፅ ሥልጣን ተረክበው አያውቁም። ሰሞነኛው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ሹመት ላይ የሚቀርቡ ትችቶችም የትናንት ተቀጥያዎች እንጅ አዲስ የተፈበረኩ አይደሉም። አዴፓ ተመስገን ጥሩነህን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር እንዲሆኑ በእጩነት ማቅረቡን ተከትሎ ጥያቄ የሚያነሳው ወገን ተበራክቷል።

ሥራ አስፈፃሚ ውስጥ ያልነበረ ሰው በድንገት ሥራ አስፈፃሚ ውስጥ እንዲገባ ተደርጎ ለዚህ ሹመት መታጨቱስ ጤነኛ አካሔድ ነው ወይ? ይላል። ለዚህ የሚሆን ምላሽ ፍለጋም አራት ኪሎ ድርስ ይጓዛል። የቀድሞው ሻለቃ ለአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድርነት መታጨትም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፍላጎት የወለደው እንደሆነ ይደመድማል። እዚህ ላይ የፖለቲካ ልኂቁን ሐሳብ ገታ አድርጌ የራሴን ጥያቄ ላንሳ። “የተመስገን ለክልል ፕሬዘዳንትነት መታጨት ለምን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ይተሳሰራል?”

ከአራት ኪሎ “መቀባት”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሕግ ባለሙያዎች ጋር በነበራቸው ውይይት የክልል ርዕሰ መስተዳደር ለመሆን ከአራት ኪሎ “መቀባት”ን እንደሚጠይቅ በገደምዳሜ ነግረውናል። የኢሕአዴጉ ሊቀ መንበር ስለጉዳዩ ሲያብራሩ በዚህ ወቅት ከትግራይና ቤንሻንጉል ጉምዝ ውጭ በሁሉም ክልሎች ርዕሰ መሰተዳድሮችንም ሆነ ካቢኔው እንዲቀየሩ አድርገናል ብለዋል። እንዲህ ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ንግግር የአፍ ወለምታ አይደለም። የመንግሥታቸውን የ2011 አፈፃፀም ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅትም አዳዲስ የክልልነት ጥያቄዎችን ጊዜ ወስደን ለመፍታት እየሞከርን ነው ከዚህ በተቃራኒው ለመሔድ የሚሞክር ኀይል ካለ ግን በሱማሌ ክልል ላይ የወሰድነውን እርምጃ እንደግመዋለን ሲሉ አስጠንቅቀዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 8 የተቀመጠውን የብሔር ብሔረሰቦችን ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት መሆን መዘንጋት የቃላት ጨዋታ ብቻ አይመስልም።

ከሐረሪ እስከ ጋምቤላ፣ ከሐዋሳ እስከ ጅግጅጋ የተደረጉ የአመራር ለውጦች ሕዝባዊ ጥያቄ የወለዳቸው ብቻ ናቸው ብሎ የሚከራከር ያለ አይመስለኝም። ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአመራር ለውጥ እንዲመጣ አድርገናል እያሉም “ዓይኔን ግንባር ያድረገው ነገሩ ውሸት ነው” የሚል ክርክር አሁን ቦታ የለውም። በእኔ ግምት አሁን ያለው ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምን መንገድ ነው የክልል ፖለቲካን እየተቆጣጠሩ ያሉት የሚለው ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በተለያዩ መንገዶች የክልሎችን ፖለቲካ ወደ ራሳቸው ለመጎትት ሲሞክሩ ተስተውለዋል። ለዚህ ደግሞ ሦስት ዐብይት አቅጣጫዎችን ተከትለዋል። የመጀመሪያው የክልል ገዥ ፓርቲዎችን አራት ኪሎ በሚገኘው አዳራሻቸው በመሰብሰብ የአመራር ለውጥ እንዲያደርጉ ግፊት አድርገዋል። ከሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶዴፓ) እስከ የጋምቤላ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋሕዴን) ያለው የአመራር መተካካትም በዚህ ዓይነቱ አቅጣጫ የተወለደ ይመስላል። ኹለተኛው የፓርቲ ኀላፊዎችን አዲስ አበባ በማድረግ የክልል ፖለቲካውን ከሰዶ ማሳደድ ለማንፃት ጥረዋል። በዚህ በኩል የሶማሌም ሆነ የአፋር፤ የደቡብ ሕዝብም ሆነ የአማራ ፓርቲ መሪዎች መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላይ አድረገዋል። ሦስተኛው መንገድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው የነገሩን በኀይል ከሥልጣን ማስወገድ ነው። ይህ መንገድ በተለይ በቀድሞው የሱማሌ አመራር ላይ ተተግብሮ ውጤታማ ሆኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚታሙበት የራስን ሰው የመሾም፣ ወደ ፊት የማምጣት አባዜ ኦሮሚያ ላይም ተግባራዊ እንደተደረገ የሚከራከሩ ብዙዎች ናቸው። የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲፒ) ሊቀ መንበር ዐቢይ አሕመድ የለማን ስንብት ተከትሎ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ጦይባ ሀሰንን ወደ ጎን በመግፋት የአራት ኪሎ ወዳጃቸው የሆኑትን ሽመልስ አብዲሳን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እንዲሆን አድርገዋል በሚል በሰፊው ታምተዋል። ሽመልስ የክልሉ ምክር ቤት አባል ሆነው በምክትልነት መሾምም ብዙ አወዛግቧል። የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር በቅርቡ ከአንድ መገናኛ ብዙኀን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት በፌደራል ደረጃ ያለውን ለውጥ ወደ ክልሎች ማውረድ በሚል ፕሮጀክት የተነሳ ሥልጣናቸውን ለቀዋል። ይህ በአራት ኪሎ የሚዘወር ፕሮጀክት ከትግራይ ክልል ውጭ በበርካታ አካባቢዎች ተስተውሏል። በባሕር ዳር በቅርቡ የተፈፀመው የአመራሮች ግድያም ራስን ትክክለኛ ተወካይ ሌሎችን ተላላኪ አድርጎ ከመወንጀል የመነጨ እንደነበር ተስተውሏል።

አዴፓ በሕይወት በሌሉት ምክትል ሊቀ መንበሩና የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ምትክ ማንን ሊሾም ይችላል በሚል የተለያዩ መላምቶች ሲሰነዘሩ ቆይተዋል። በጊዜው ይሰነዘሩ ከነበሩ አስተያየቶች አንጻር የዮሃንስ ቧያለው የአዴፓ ምክትል ሊቀ መንበር መሆን የሚያስገርም አይደለም። ይሁን እንጅ የእሳቸው ሹመት ሰምና ወርቅን ያዘለ ነው። የክልሉ ገዥ ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር ለመሆን ከቻሉ ለምን የርዕሰ መስተዳድርነቱን ቦታ ተነፈጉ የሚለው ሐሳብም አንድምታው ብዙ ነው።ለዚህ ጥያቄ አውንታዊም አሉታዊም ምላሾችን መስጠት የሚቻል ይመስለኛል።

የመጀመሪያው አዴፓ የድርጅት ጉዳይን የሚመራ ሰው የመንግሥት ቁንጮ መሆን የለበትም የሚል ቅን አስተሳሰብን በማንገቡ ሊሆን ይችላል። ይህ አመለካከት በአዴፓ ሥራ አስፈፃሚም ሆነ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ውስጥ ተፈጥሮ ከሆነ እጅጉን የሚያሰወድስ ነው። ነገር ግን ሴራ በተጠናወተው የአገራችን ፖለቲካ ውስጥ የዮሃንስ ሥልጣን በፓርቲ ብቻ መገደቡ ጥርጣሬን ያጭራል። ይህ ጥርጣሪያችን ይበልጥ ጉልበት የሚያገኘው ደግሞ ለክልል ርዕሰ መስተዳድርነት ቦታ የታጩትን ሰው ማንነት ስንረዳ ነው።

ተስመስገን ጥሩነህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫ ይሆኑ?
አዴፓ ተመስገን ጥሩነህን ቀጣዩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዲሆኑ እጩ አድርጎ መርጧል። ተመስገን ከየትኛውም የአዴፓ አመራሮች ቀድመው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወዳጅ እንደነበሩ የአደባባይ ምስጢር ነው። የዛሬው ጠቅላይ ሚኒስትር ቀድሞ ይሰሩ በት ከነበረው የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የራስን ኔትወርክ በማደራጀት ተገምግመው ከኀላፊነት ሲነሱ አብረዋቸው ከተሰናበቱት መካከል ተመስገን ጥሩነህና አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ተጠቃሽ ናቸው። ኹለቱ ግለሰቦች በዐቢይ አሕመድና (ዶ/ር) በሜጄር ጄነራል ተክለብርሃን ወልደ አርጋይ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ለዛሬው ጠቅላይ ሚኒስትር ወግነው ብዙ ችግሮችን ተጋፍጠዋል። በመጨረሻም የጄነራሉ ቡድን አሸናፊ ሲሆን ከኀላፊነታቸው በግምገማ እንዲነሱ ተደርገዋል። የእነሱ ተቀናቃኝ የሚባሉት ሲሳይ ቶላና ዛሬ በእሥር ላይ የሚገኙት ቢኒያምም በድርጅቱ ውስጥ የተሻለ ተደማጭ ወደ መሆን ተሸጋግረዋል።

ተመስገን በኢንሳ የተፈጠረውን የኹለት ወገኖች ግብግብ ተከትሎ ተሸናፊ በነበረው አንጃ ውስጥ እንደመገኘታቸው መጠን በተቋሙ ሊቀጥሉ አልቻሉም። በዚህም የመሰረቱትን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ለቀው ወደ ክልላቸው አምርተዋል። የቅርብ ወዳጃቸው ዐቢይ ኢንሳን ተሰናብተው የሳይንስና ቴክኖሎጅ ማዕከልን ተቀላቅለዋል። የኹለቱ ተሰናባቾች ግንኙኝነት በዚህ ዓይነት ሁኔታ የተጠናቀቀ ቢመስልም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ግን ትንሳዔን አልነፈገውም። ባለፈው ዓመት የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ዐቢይ ሳይጠበቁጠቅ ላይ ሚኒስትር አደረገ። የእሳቸው መምጣትም ብዙ ነገሮችን ቀየረ።ከዓመታት በፊት ድል ቀናኝ ያሉት ሜጄር ጄነራል ተክለ ብርሃን የቀድሞ ባላንጣቸውን መሾም ሲሰሙ ከኀላፊነታቸው ለመልቀቅ ጥያቄ አቀረቡ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዓይናቸውን ሳያሹ ሰውዬውን አሰናበቱ። በምትካቸውም ከዓመታት በፊት እሳቸወን በመደገፋቸው ከኢንሳ አመራርነት የታገዱትን ተመስገን ጥሩነህን ሾሙ። ሌላኛውን ወዳጃቸውን አብርሃም በላይም (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አደረጉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ መንገድ የቀድሞ ወዳጆቻቸውን ለመካስ ቢሞክሩም ከመርህ አንጻር ግን ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም። በተለይም የፓርቲ አባል የሆነሰው በመንግሥት ደኅንነት ተቋማት ውስጥ አይመደብም የሚለው ቃላቸው መልሶ ራሳቸውን መፈናፈኛ አሳጣቸው። በመሆኑም ዐቢይ ተመስገንን ከኢንሳ አንስተው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ደኅንነት አማካሪ አድርገው ሾሟቸው። በውትድርና ሕይወት እሰከ ሻለቃነት የደረሱት ተመስገን ሀገር ባለመረጋጋት ከድጡ ወደ ማጡ ስታመራ ያቀረቡት መፍትሔ ምን እንደነበረ ባይታወቅም በኀላፊነት መዝለቃቸው ግን እውነት ነበር።

በዚህም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ለመሆን እስከ ታጩበት ጊዜ ድረስ አራት ኪሎው ለው አድረዋል። በሒደትም እንደሌላው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የቀድሞ ባልደረባቸው ሽመልስ አብዲሳ ክልል ለመምራት ተቃርበዋል።የተመስገን ለርዕሰ መስተዳድርነት መታጨት የአዴፓ ብቻ ፍላጎት አይመስልም። ለዚህ ኹለት ነገሮችን መከራከሪያ አድርጎ ማቅረብ ይቻላል። የመጀመሪያው ተመስገን አዴፓ በተደጋጋሚ ባካሔዳቸው የሥራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫ ላይ አባል ሆነው አለማወቃቸው ነው። መረጋጋት በተሳነው አዴፓ ውስጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በርካቶች የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል በመሆን ወጣ ገባ ብለዋል። ከብሔራዊ ባንክ ገዥው ይናገር ደሴ (ዶ/ር) እስከ ተፈራ ደርበው ድረስ ብዙዎች የሥራ አስፈጻሚነት ፀበል ደርሷቸዋል።

ተመስገን ጥሩነህ ግን ለዚህ አልታደሉም። እንዲህ ከሆነ ታዲያ ዛሬ ምን ተገኝቶ በአንድ ጊዜ የሥራ አስፈፃሚ አባልነትና የክልል መሪነት ድርሻ ተሰጣቸው? ያስብላል። ምላሹ የቀድሞው ሻለቃ በድንገት ተዓምራዊ ለውጥ አምጥተው የአዴፓን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ቀልብ ስለሳቡ አይመስልም። እንደውም ከሥራ አፈፃፀም አንፃር ከተመለከትነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚተቹበት የአገሪቱን ዜጎች ደኅንነት አለማስጠበቅ ጉዳይ ከእኒህ ሰው ኀላፊነት ጋር የሚተሳሰር ነው። ዐብይ የሚወቀሱበት አገራዊ አለመረጋጋትን አስቀድሞ አለመተንበይና ከተፈጠረ በኋላም በፍጥነት አለመፍታትም በዋናነት ተመስገንን የሚመለከት ነው። እውነታው እንዲህ ከሆነ የቀድሞው የኢንሳ አመራር ለርዕሰ መስተዳድርነት መታጨት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፍላጎት የወለደው ሊሆን ይችላል ማለቱ እንደ “ሀራም” ሊታይ አይገባም ።

በርግጥም የአዴፓ ኹለተኛ ሰው ዮሃንስ ቧያለው ኹለት ሚሊዮን የማይሞላ ካድሬ እንዲያስተዳደር ተደርጎ በፓርቲ ውስጥ ከእሱ ያነሰ ሚና ያለው ሰው ከ30 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እንዲመራ ማድረግ ፖለቲካዊ እንቆቅልሽ ነው። ነገሩን በውሉ ከተመለከትነውም የማኅበራዊ ሚዲያውን ተፅዕኖና የጠቅላይ ሚኒሰትሩን ፍላጎት ለማጣጣም የተዘየደ ይመስላል። የአማራ አክቲቪስቶች ከሞላ ጎደል ዮሃንስ ቧያለው የአዴፓ ምክትል ሊቀ መንበርና የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር እንዲሆኑ መፈለጋቸው እርግጥ ነበር። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ያለውን የክልሉን ብሔርተኝነትና ፖለቲካዊ ጡዘት የሚያረግብ ከተቻለም እምነት የሚጥሉበት ሰው ወደ ፊት እንዲመጣ መፈለጋቸው አያከራክርም።

ይህ ደግሞ የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴን ኹለቱን ኹለቱንም ጎራ ጎራ አሸናፊ ያደረገ ውሳኔ እንዲያስተላልፍ አድርጎት ሊሆን ይችላል። የአዴፓ የኹለቱን ወገኖች ፍላጎት በዚህ መንገድ ለማስታረቅ ቢሞክርም መሰረታዊውን ጥያቄ ግን የተሻገረው አይመስልም። ከሕወሓት ጋር በነበረው ግንኙነት ተላላኪ ተደርጎ ሲገለፅ የነበረው አዴፓ ዛሬም በኦዲፒ መታማት ይዟል። በዚህ ውጥንቅጥ መካከል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወዳጅ የሆኑት ተመስገን ጥሩነህ ወደ ርዕሰ መስተዳድርነት መምጣትም ነገሩን ይብለጥ እንዳያንርው ያሰጋል። ጉዳዩን ከአዲስ አበባና ባሕር ዳር ፖለቲካ ከፍ አድርገን ከተመለከትነውም የአራት ኪሎ ቡራኬን የተቀበሉ ሰዎች ወደ ክልል ቤተመንግሥታት መትመም ለውጡን የሰፌድ ላይ ሩጫ እንዳያደርገው ያስፈራል።

ለፌደራል መንግሥቱ ሎሌ የሆኑ የክልል መሪዎችን መሾም ትናንት ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለን ይታወቃል። በሥም ፌደራላዊ ስርዓት እንከተላለን እያልንም በተግባር የአኀዳዊ ተቀጥላ ስርዓትን እንድናራምድ አድርጎናል። በዚህም ሕዝብ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት የሚሆንበት መንገድ ተዘንግቶ ዴሞክራሲያዊ ማዕከለዊነት ከላይ እስከታች አገርን መላወሻ አሳጥቶ ኑሯል። እንዲህ ያለው ፀረ ዴሞክራሲያዊ አካሔድም በጊዜ ሒደት ስርዓቱን አቆርቁዞታል። የደካማ የክልል መንግሥታት መፈጠር አገራዊ ቁልቁለትን አፋጥኗል። በየአከባቢው ያለው ሕዝብም መሪዎቹን እንደ መሪ ከማየት ይልቅ ተላላኪዎች ናቸው ብሎ እንዲያምን አድርጓል።

በርካታ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ሲገመግሙ አንዱ የመፍትሔ ሐሳብ ጠንካራ የክልል መንግሥታትን መፍጠር ነው ይላሉ። የክልሎች መጠናከር ድምር ውጤትም አገርን ወደ ተሸለ ደረጃ ያሸጋግራል ሲሉ ይሞግታሉ። በርግጥም ኢትዮጵያ ጠንካራ አገር መንግሥትን እንድትገነባ ክልሎች በሕገ መንገሥቱ የተሰጣቸው ሉዓላዊ ሥልጣን ሊከበር ይገባል። ትናንት ብአዴን፣ ኦሕዴድና ደኢሕዴን በሚመሩት ሕዝብ ሲፈተኑ የነበሩት የእኛ ሳይሆን የሕወሓት ተወካዮች ናችሁ በሚል ነበር። ይህን ታሪክ የተሻገርነው አድርገን ልናስበው አይገባም። የነገው የፖለቲካ ፍኖታችን ክልሎችን ሉዓላዊ የሥልጣን ባላቤት ከማድረግ አንጻር ከሀሜት የሚድን መሆን አለበት።

የተመስገን ጥሩነህ ለአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድርነት መታጨት ከአራት ኪሎ ቡራኬን የተቀባለ ሰው ፍለጋ ያመጣው ቢመስልም የነገ ተግባራቸው ግን የጉዳዩን እውነትነት አልያም ሐሰትነት የምናረጋግጥብት ብቸኛ ማስረጃችን ይሆናል። አዲሱ ዕጩ ርዕሰ መስተዳደር በፀጥታና ደኅንነት በኩል ረጅም ልምድ ያካበቱት እንደመሆናቸው መጠን ሰላም የራቀውን ክልል ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲመጣ ሊያግዙት ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪም በገጠር መንገዶች ባለሥልጣን ውስጥ በኀላፊነት እንደመቆየታቸው መጠን በዚህ በኩል ያላቸውን ልምድ መጠቀም ከቻሉ በመንገድ ትስስር ኋላቀር የሚባለውን ክልል ለውጥ እንዲያመጣ ይረዳሉ። ተመስገን ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ያላቸው ግኑኝነት በመርህ ላይ የሚመሰረት ከሆነም የአማራን ሕዝብ ጥቅም በሰላማዊ መንገድ ለማስከበር ሌላ ጉልበት እንደሚሆኑ አያጠራጥርም።

ይነገር ጌታቸው ተለያዩ መገናኛ ብዙኀን በማገልገል ላይ የሚገኙ ባለሙያ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው mar.getachew@gmail.com ሊገኘኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 37 ሐምሌ 13 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here