የርዕሰ መስተዳድሩ መታጨት ጉዳይ

0
684

በአማራ ብሔራዊ ክልል ሰኔ 15 የተካሔደውን “መፈንቅለ መንግሥት” ተከትሎ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥትና የፓርቲው የአመራር ቦታዎች ክፍተት መፈጠራቸው ይታወቃል። ይህንን ክፍተት ለመሙላት የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ አካሒዶ ሰኞ፣ ሐምሌ 8 ተመስገን ጥሩነህን ዕጩ ርዕሰ መስተዳድር እንዲሁም ዩሐንስ ቧያለውን ደግሞ የአዴፓ ምክትል ሊቀ መንበር አድርጎ መርጧል።

በተለይ የተመስገን ዕጩ ርዕሰ መስተዳድር ሆኖ መመረጥ በከፍተኛ ደረጃ የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች የመነጋገሪያ ጉዳይ ሆኖ ጎልቶ ወጥቷል። ሥማቸው ብዙም የማይታወቀው ተመስገን ክልሉንም ሆነ የፌደራል መንግሥቱን በተለያዩ ኀላፊነቶች አገልግለዋል።

የተመስገን ዕጩ ርዕሰ መስተዳድር ሆኖ መመረጥ ቅር ያሰኛቸው ወገኖች በርካታ የመከራከሪያ ጭብጦችን ያነሳሉ። የመጀመሪያውና ዋናው ከዚህ በፊት የሚሾሙት የነበሩት አመራር የሕወሓትን ተልዕኮ የሚያስፈጽሙ ነበሩ የሚሉት ወቃሾች ዛሬ ይሔ በአዴፓ ላለመደገሙ ዋስትና የለንም በማለት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ረጃጅም እጆች ምርጫው ውስጥ አሉበት ሲሉ ይከራከራሉ። የጠቅላዩን ሥልጣን የሚያራዝም “ሲጠሩት አቤት ሲልኩት ወዴት” የሚል ባለሟል ነው የተሾመው ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ ሆነው ማገልገላቸው ይጠቅሳሉ። በርግጥ የጠቅላዩን ግለጽ ጣልቃ ገብነት በመረጃም ሆነ ማስረጃ አላስደገፉትም።

በተጨማሪም የተመስገን ለርዕሰ መስተዳድር ቦታ መታጨት በአማራ ብሔርተኞች ዘንድ እምብዛም የተወደደ አይመስልም። እንደምክንያትነት የጠቀሰው ሹመቱ ሆን ተብሎ የአማራ ብሔርተኝነትትን ለማዳከም ብሎም ለማጥፋት የተጎነጎነ ሴራ ነው ሲሉ ድምፃቸው ተሰምቷል። ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉትም ቦታው የዩሐንስ ቧያለው መሆን ነበረበት ሲሉም ተደምጠዋል። ሐሳባቸውን በአመክንዮ ሲያስቀምጡ ከዚህ በፊት በነበረው አሠራር መሰረት የፓርቲው ምክትል ሊቀ መንበር የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር መሆኑን በመጥቃስ ነው።

አንዳንዶች በበኩላቸው የተመስገን ዕጩ ርዕሰ መስተዳድር ሆኖ መቅረብ ከካበተ ልምዳቸው አንጻር በተለይ በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ከመስራችነት እስከ ዋና ዳይሬክተርነት እንዲሁም በመከላለያ ሠራዊት ውስጥ የመረጃ ዋና ኀላፊ ሆነው ማገልገላቸው በተለይ በክልሉ የሚስተዋለውን ስርዓት አልበኝነት አደብ ለማስያዝ ኹነኛ ሰው ናቸው ሲሉ ሹመቱን ከወዲሁ ያጸደቁላቸው አልታጡም፤ የክልሉ የፀጥታና ሁኔታ ትኩረት ተሰጥቶት መሠራት ከሚል ማሳሰቢያ ጋር።

ሌላው እንደሌሎች አንዳንድ ክልሎች ሕገ መንግሥታዊውን ርዕሰ መስተዳድር ኀላፊነት ሙሉ በሙሉ ሰጥቶ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማስቀመጥ ሕጋዊም ሕገ መንግሥታዊ ተገቢነት የለውም በማለት አዴፓ ይህንን ችግር ተሸግሮታል በማለት የተመስገንን መታጨት ደግፈዋል። ይሁንና ከዚህ በፊት ከነበረው አሠራር አንጻር ግን ዕጩው ርዕሰ መስተዳድር የፓርቲው ምክትል ሊቀ መንበር አለመሆናቸው ውሳኔ በመስጠት አቅማቸው ላይ ችግር ይኖረው ይሆን በሚል ጥርጣሬጣቸውን አንጸባርቀዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 37 ሐምሌ 13 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here