ሰርከስ አዳማ ለ 5 ዓመታት ኪራይ ባለመክፈሉ ታሸገ

0
805

በአዳማ ከተማ የሚገኘው ሰርከስ አዳማ የወጣቶች ቡድን ለተከታታይ አምስት ዓመታት የቤት ኪራይ ባለመክፈሉ ምክንያት አርብ፣ ሐምሌ 5/2011 መታሸጉን ቡድኑ አስታወቀ። ከ25 ዓመታት በፊት 45 አባላትን በመያዝ የተመሰረተው ስፖርት ቡድን ከከተማ አስተዳደሩ በ350 ብር ኪራይ ያገኘውን ቤት ኪራይ ለመክፈል ባለመቻሉ በከተማው ንግድ ቢሮ አማካኝነት መታሸጉም ታውቋል።

የስፖርት ቡድኑ ዳይሬክተር አላምረው ዳኜ ለአዲስ ማለዳ እንደገጹት ሰርከስ አደማ እስከ አሁን ከተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ድጋፍ እያገኘ ኅብረተሰቡን ሲያገለግል የቆየ ቢሆንም ከዚህ ቀደም በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ላይ የወጣውን አዋጅ አስመልክቶ ድጋፍ የሚያደርጉ ድርጅቶች በሙሉ ድጋፋቸውን አቋርጠዋል። ሆኖም ግን ይህ ድጋፍ ከተቋረጠ በኋላ ለተከታታይ 2 ዓመታት 350 ብር ከማኅበሩ አባላት በመሰብሰብ መዋጮ ሲከፍሉ መቆየታቸውን የተናገሩት አላምረው ላለፉት አምስት ዓመታት ክራይ መክፈል ባለመቻቸው የቡድኑ ጽሕፈት ቤት ሊታሸግ ችሏል ብለዋል።

በአዳማ ከተማ የሚገኙ እና የዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ልጆችን ድጋፍ ለመስጠት በሚል በትምህርት፣ በሰርከስ ጥበብ እና በሥነ ምግባር የተሻሉ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ ከአዳማ ዩንቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር በመሆን በበጎ ፍቃደኝነት መሰረታዊ የኮምፒውተር ትምርቶችን እንዲሁም የተለያዩ ሥልጠናዎችን እና የላብረሪ አገልግሎቶችን ሲሰጥ ነበር። ሆኖም ጽሕፈት ቤቱ በመታሸጉ ይህ አገልግሎት ተቋርጧል።

“የሰርከስ አዳማ ክለብ ልጆች በመላው ኦሮምያ ጨዋታዎች አዳማን በመወከል እየተወዳደሩ ለመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች የወርቅ ሜዳልያዎች እና የዋንጫ ሽልማቶችን ሲያስመዘግቡ የቆዩ ልጆች ናቸው” ሲሉ አላምረው ተናግረዋል። “ከዚህም አልፎ በዓለም ክብረ ወሰን መዝገብ ላይ የተመዘገቡ ልጆችን እሰከማፍራት የደረሰ እና የከተማዋን መልካም ገጽታ ከማበርከት አኳያ ትልቅ ሚና ነበረው።”

በ200 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው የሰርከስ አዳማ 85 ልጆችን ይዞ የተለያዩ ሥልጠናዎችን እየሰጠ የሚገኝ እና በበጎ ፍቃደኛነት የተመሰረተ ክለብ ነበር። ክለቡ ሲመሰረት ቦታው የተገኘው በወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ አማካኝነት መሆኑን እና በወቅቱ በባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊዎችም ከፍተኛ ድጋፍ ሲደረግለት እንደነበርም ታውቋል።

“ሆኖም ግን የቡድኑ ጽሕፈት ቤት መታሸግ ቢኖርበት እንኳን ሊታሸግ የሚገባው በቤቶች ልማት አማካኝነት ቢሆንም የታሸገው ግን በከተማዋ ንግድ ቢሮ አማካኝነት ነው” ያሉት ሰርከስ አዳማ ቡድን ዳይሬክተር “ይሁንና የወጣቶች ስፖርት ክለብ ክራይ መክፈል የምንችልበት ምንም ዓይነት ገቢ እንደሌለን በጻፈው ደብዳቤ መሰረት ለሚመለከተው ሁሉ ብናሳውቅም እስከአሁን ምላሽ ማግኘት አልቻልንም” ሲሉ ጨምረው ገልፀዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 37 ሐምሌ 13 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here