የጎፋ ዞን ነዋሪዎች የኀይል ጥቃት እየደረሰብን ነው ሲሉ ቅሬታቸውን አሰሙ

0
432

በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ጎፋ ዞን ልዩ ሥሙ መለኮዛ በተባለ ቦታ የቤተ ክርስቲያን ይዞታ አይነካም በማለታችን የክልሉ የታጠቁ ኀይሎች ጥቃት አድርሰውብናል ሲሉ ነዋሪዎች አስታወቁ። ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ከ1964 ጀምሮ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባለቤትነት ሥር የነበረው ቦታ ከመንግሥት ሳይሆን ከዞኑ የተወሰኑ አመራሮች በመነጨ ፍላጎት ለመውሰድ እንቅስቃሴ በሚደረግበት ወቅት ምዕመኑ ተቃውሞ በማሰማቱ በክልሉ ልዩ ኀይልና በዞኑ የፀጥታ ኀይሎች ጥቃት ደርሶብናል ሲሉ አስረድተዋል።

ቅሬታ አቅራቢዎች ጨምረው እንደገለፁት ቦታው በአርባ ምንጭ አገረ ስብከት ላሃ ድብረ ሳኤል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሥር ለረጅም ዓመታት ይተዳደር የነበረ መሆኑን ገልፀው፤ አያይዘውም በየዓመቱ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል (ጥምቀት ባሕር) የሚከናወንበት ሥፍራ እንደሆነም ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ ቅሬታ አቅራቢዎች ለአዲስ ማለዳ እንደሚናገሩት የአካባቢው ተወላጅ የሆኑትና በፌደራል መንግሥት የኀላፊነት ሥፍራ የሚገኙት ተስፋዬ ቤልጅጌ የዞኑን የሥራ ኀላፊዎች በማስተባበር ለባለ ሀብት እንዲሰጥ በማሰብ የቤተ ክርስቲያኗን መሬት ለመንጠቅ ተንቀሳቅሰዋል ሲሉም ጨምረው ገልፀዋል። በዚህም መሰረት ደመላሽ አስራት የተባሉ ባለሀብት የቤተ ክርስቲያን ይዞታ ነው በተባለው ቦታ ላይ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ‹ዴፖ› መትከል መጀመራቸውንም ለማወቅ ተችሏል።

በሌላ በኩል ደግሞ የዞኑ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ድንበሩ ድሪባ ስለ ጉዳዩ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ማብራሪያ ከመጀመሪያውም ቦታው የማንም ሳይሆን የመንግስት እንሆነና ቦታው ለመነሐሪያ ግንባታ ስለታሰበ ተለዋጭ ቦታ ተሰቷቸዋል ሲሉ አብራርተዋል። ጨምረውም የኃይል እርምጃ ተወሰደ የተባለውም የተሳሳተ መረጃ ነው ሲሉ አክለዋል።

የዞኑ አስተዳዳሪዎች እየሠሩ ያሉትን ተግባር ሕገ ወጥ ነው በሚል ተቃውሟቸውን ያሰሙ ግለሰቦት ክፉኛ እንደተደበደቡና ሃምሳ አንድ ያህል የሚሆኑት ደግሞ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ምንጮች ከጎፋ ዞን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

በጥምቀተ ባሕር የመጠመቂያ ሥፍራ ላይ የነበረውን የመስቀል ምልክትም በመሰባበር እንዲፈራርስ እንዳደረጉትም ታውቋል። የድብደባ ጥቃት ከተፈፀመባቸው ውስጥ አራት የቤተ ክርስቲያኗ ካህናት ከፍተኛ ጉዳት ስላጋጠማቸው በጤና ተቋም ዕርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኙና አንድ ወጣትም በዱላ ተደብድቦ እጁ እና ወገቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳጋጠመው ለአዲስ ማለዳ ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአካባቢው ሰዎች ተናግረዋል። በተጨማሪም በሐምሌ 11/2011 ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ላይ የክልሉ የፀጥታ ኀይሎች በቤተ ክርስቲያኗ ላይ የተኩስ ጥቃት ማድረሳቸውንም ተጨምሮ ተገልጿል።

የአዲስ ማለዳ ምንጮች ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ቅሬታቸውን ለማቅረብ ከክልል እስከ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ድረስ መመላለሳቸውን እና አሁንም ዕልባት እንዳላገኙ ገልፀው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያሪክ ብጹዕ አቡነ ማቲያስ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉት እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል።

አዲስ ማለዳ የጎፋ ዞን አስተዳዳሪዎችን ያደራጃሉ የተባሉትን ተስፋዬ ቤልጅጌን ስለ ጉዳዩ ያነጋገረች ሲሆን “ጉዳዩን አውቀዋለሁ ግን ከረጅም ጊዜ በፊት ዕልባት እንደተሰጠው እና ቦታው እንዳይነካ የሚል ውሳኔ ላይ እንደተደረሰም አውቃለሁ። ነገር ግን አሁን እኔ በፌደራል ደረጃ እየሠራሁ ስለሆነ ምንም የማውቀው ነገር የለም” ያሉ ሲሆን ሥማቸው ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ መነሳቱም ትክክል እንዳልሆነና መሰረተ ቢስ ሥም የማጥፋት ዘመቻ ነው ሲሉም አክለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 37 ሐምሌ 13 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here