ለፍርድ ቤቶች የሚቀርቡ ሐሰተኛ ምስክሮችና ሰነዶች የወልና የግለሰብ መሬቶችን በማይገባቸው ሰዎች እጅ እንዲያዙ እያደረጉ ነው ሲሉ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት አስታወቁ። የ2011 በጀት ዓመት የ11 ወራት ዕቅድ አፈፃፀሙን ለክልሉ ምክር ቤት 13ኛ መደበኛ ጉባኤ ያቀረበው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ሐሰተኛ ምስክሮችና ሰነዶችን እያደራጁ ለፍርድ ቤት በማቅረብ የፍርድ ውሳኔን እንዲዛባ እየተደረገ ነው ብለዋል። በዚህም አላግባብ የሕፃናት፣ የሴቶች፣ የአቅመ ደካሞችና የሞተ-ከዳ መሬቶችን ለግለሰቦች ጥቅም እየዋሉ መሆኑን ተናግረዋል።
በሐሰተኛ ማስረጃ ምክንያት ፍርድ ቤቶች ትክክለኛ ያልሆነ ውሳኔ እንዲያስተላልፉና መተማመን እንዲጠፋ እያደረገ ነው ያሉት የምክር ቤት አባላት፥ ፍርድ ቤቶች የመንግሥትን የሥራ ሰዓት ጠብቀው አገልግሎት እየሰጡ ባለመሆኑም ራቅ ካሉ አካባቢዎች የሚመጡ ተገልጋዮች ጉዳያቸውን ሳይሰሙ ተለዋጭ ቀጠሮ ስለሚሰጣቸው ማማረራቸውን ገልጸዋል።
ሐሰተኛ ማስረጃ የሚያቀርቡና በሐሰት የምስክርነት ቃላቸውን የሚሰጡ አካላት በሕግ አግባብ አስተማሪ እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባም የምክር ቤቱ አባላት አሳስበዋል።
የምክር ቤቱ የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አማረ ሰጤ በበኩላቸው የቀበሌ መሬቶችን በተደራጀ የሐሰት ምስክርነት ወደ ግለሰቦች የማስተላለፍ አደገኛ ተግባር እንዲስተካከል አቅጣጫ ተቀምጦ የነበረ ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ ችግሩ አልተፈታም ብለዋል።
በአንዳንድ የወረዳ ፍርድ ቤቶች ባለጉዳዮችን በትህትና የማስተናገድ ችግር እንደሚስተዋል ቋሚ ኮሚቴው ባደረገው የመስክ ክትትል ወቅት ኅብረተሰቡ ካነሳው ቅሬታ ለመረዳት እንደተቻለ ተናግረዋል። የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የኔነህ ስመኝ በበኩላቸው ተከታታይ ሥራዎች ቢሠሩም ለፍርድ ጥራት መጓደል ዋነኛ መንስኤ የሐሰት ምስክርና በገጠር መሬት ክርክሮች ላይ የሚሰጡ ያልተጣሩ ማስረጃዎች አሁንም ፈተና ሆነው ቀጥለዋል።
አዲስ ማለዳ ሐምሌ 20 ቀን 2011


