ደኢሕዴን ከፍተኛ ባለሥልጣኖቹን አገደ

0
561

የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ገዢ ፓርቲ የሆነው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) የሲዳማ ዞን አመራሮችን ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ከኀላፊነታቸው አገደ። በከፍተኛ ማስጠንቀቂያ የታለፉ የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት መኖራቸውንም አዲስ ማለዳ ከክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣን ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

ከታገዱት ባለስልጣናት መካከል፣ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር፣ የሲዳማ ዞንና የሐድያ ዞን አስተዳደር፣ ምክትል አስተዳዳሪዎች፣ የድርጅት ጉዳይ ኀላፊዎች፣ የጸጥታ ጉዳይ ኀላፊዎችና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይገኙበታል። በከባድ ማስጠንቀቂያ ከታለፉት ባለሥልጣናት መካከል ደግሞ የወላይታና የከፋ አመራሮች እንደሚገኙበት አዲስ ማለዳ ከክልሉ ጽሕፈት ቤት ያገኘችው መረጃ ያመለክታል። ድርጅቱ ለከፍተኛ አመራሮቹ መታገድ እንደ ምክንያት የጠቀሰው በክልሉ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይ ደግሞ በሐዋሳ ከተማና በሌሎች የሲዳማ አካባቢዎች ሰሞኑን ያጋጠሙትን ቀውሶች ሲሆን፤ የሐድያ ዞን ከፍተኛ አመራሮችም በዞኑ ውስጥ ታይተዋል በተባሉ የጸጥታ ችግሮች ውስጥ ሚና አላቸው ተብለው በመጠርጠራቸው መሆኑ ተገልጿል።

ከሐምሌ 11 ጀምሮ በሐዋሳ፣ በአለታ ወንዶ፣ በሀገረ ሰላም፣ በወንዶ ገነትና ሌሎች የሲዳማ ዞን ወረዳዎች በተፈጠረ ግጭት እስካሁን ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ሲሞቱ በግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች፣ በንግድ ተቋማትና በአብያተ ክርስትያናት ላይ በተፈጸመ ጥቃት ውድመት አጋጥሟል።

ደኢሕዴን ከተጠቀሱት አካባቢ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተጨማሪ በተመሳሳይ ድርጊቶች ውስጥ ተሳትፈው ተገኝተዋል የተባሉ በክልሉ ሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ባለስልጣናት ላይም ውስዷል።

አዲስ ማለዳ ሐምሌ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here