የኮማድ ፖስቱ ጉዳይ በደቡብ ክልል

0
364

ከሰኞ፣ ሐምሌ 15 ጀምሮ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሁሉም ዞኖች፣ የሐዋሳ አስተዳደርና ልዩ ወረዳዎች የጸጥታ ሥራው በፌደራል ጸጥታ ኀይል ቁጥጥር ሥር ሆኖ በጊዜያዊ ኮማድ ፖስት እንዲመራ መወሰኑ ክልሉ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ ይታወቃል።

ደቡብ ክልልን በኮማንድ ፖስት ስር እንዲሆን የዳረገው ከሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ መሆኑ ተጠቅሶ በተከሰቱት የጸጥታ ችግሮች፣ የሕግ የበላይነት በአግባቡ እንዳይከበር እንቅፋት መሆኑና የዜጎች ደኅንነት ጥያቄ ላይ እንዲወድቅ ማድረጉ እንደ ገፊ ምክንያት ተጠቅሷል።

‘ሲዳማ 11/11/11’ በተባለ የኅቡዕ የሲዳማን ክልልነት ለማወጅ በተዘጋጁ ወይም ዘመቻውን እንደ ጥሩ አጋጣሚ የተጠቀሙት የተቀናጁ ወጣቶች ስብስብ በሐዋሳና በዙሪያዋ በሚገኙ ወረዳዎች ላይ የሰላምና መረጋጋት መታጣት፣ ግድያዎች፣ የተደራጀ ዘረፋ፣ የአብያተ ክርስቲያናት ቃጠሎ እንዲሁም በመንግሥት ተቋማት፣ በሱቆችና በግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች ላይ ውድመት እንደተካሔዱ በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ተዘግቧል። ቁጥሩ ላይ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም በበርካታ ዐሥርታት የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል፤ ቁስለኞች ደግሞ የሟቾች እጥፍ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ ተገምቷል።

ኮማድ ፖስቱን በተመለከተ የተለያ ሰዎች የተለያ አመለካከቶችን አራምደዋል። አንዳንዶች መደገፍ ነገር ግን የዘገየ ሲሉ ተችተውታል። በክልሉ የታየው አለመረጋጋትና ኹከት ብዙዎች የገመቱት ይሁንና በመንግሥት ዳተኝነት ምክንያት የብዙ ሰዎች ሕይወት ቀጥፏል። ኢዜማ ማክሰኞ፣ ሐምሌ 16 በሰጠው መግለጫም በሐዋሳ እንደዚህ ዓይነት ኹከትና ጥፋት ሊፈጠር እንደሚችል አስቀድመን እናውቅ፤ ይህንንም ለሚመለከተው የመንግሥት አካላት በከፍተኛ አመራሮቻችን በኩል እንዲደርስ አድርገናል ሲል የመንግሥትን ዳተኝነት ኮንኗል።

በዚህም አንዳንዶች “መከላከያው መግባቱ ካልቀረ፣ ከማንድ ፖስት መቋቋሙ ካልቀረ” ከቀናት በፊት ቢሆን ሲሉ የመንግሥትን ዘገምተኛ አካሔድ ወርፈዋል፤ የዘገየ እርምጃ አወሳሰድ ዜጎችን በማማረር በመንግሥት ላይ ያላቸው የደኅንነት ዋስትና እና መተማመን በከፍተኛ ደረጃ አዳክሞታል የሚሉም ታዛቢዎች አሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ሕጋዊነትን በተዳጋጋሚ በማንሳት መንግሥት ለሕጋዊ ጥያቄ የሰጠው ምላሽ ከሕግ ውጪ ነው ሲሉ ከዚህ ቀደም እንደነበረው የኀይል አማራጭን መውሰዱ ተገቢ እንዳልሆነ የገለጹ አሉ። መንግሥት ወደ ራሱ ተመልክቶ ጥያቄን በሕግ አግባብ መፍታት ሲገባው ለማንም ያልበጀውን ኀይል መጠቀሙ ያስተዛዝባል ያሉም ይገኙበታል። እነዚህኞቹ ጠንከር ያለ አስተያየታቸውን ያሰሙት የሲዳማን ክልልነት በሕግ ካልተሳካ በኀይል እሳካዋለን ሲሉ ዛቻና ማስፈራሪያ አሰምተዋል። አንዳንዶች ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜው ‘ከኑግ ጋር የተገኘኽ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ’ እንዲሉ የጸጥው ችግር በዋናነት ሐዋሳና በዙሪያዋ በሚገኙ ወረዳዎች ሆኖ ሳለ በአጠቃላይ ክልሉን በኮማንድ ፖስት ቁጥጥር ሥር ማድረጉ ተገቢነት ላይ ጥያቄ አንስቷል።

የአስቸኳይ ጊዜው አቀባበል ጉራማይሌነት የመንግሥት ሰላምና ጸጥታን የማስጠበቅ እንዲሁም አስቀድሞ የመከላከል ብቃት ጥያቄ ላይ በብዙዎች ዘንድ ጥያቄ እያስነሳ ይገኛል።

አዲስ ማለዳ ሐምሌ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here