“የምድራችን ጀግና” አዲሱ የዘነበ ወላ በረከት

0
1162

“አስተዋይ፣ ትሁት አንዳንዴ ይሉኝታ የሚያበዛ ሰው ነው” ሲሉ ሽብሩ ተድላ (ፕሮፌሰር) ብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ ለተገኘው ታዳሚ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ምስክርነት ሰጡ። ፕሮፌሰሩ ይህን ምስክርነት የሰጡት ለረጅም ዓመታት ወዳጃቸውና ጓደኛቸው ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር) ነው። ስለዶክተር ተወልደ ብርሃን ይልቁንም ስለ መልካም ስብዕናቸው ብዙዎች ደጋግመው ተናገረውላቸዋል። ተፈጥሮም ብትሆን አንደበትን ብትታደል ዝም ልትል እንደማትችል ያደረጉላት ሥራ ሁሉ ያሳብቃል። ለተፈጥሮ ተቆርቋሪ፤ ለአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች ናቸውና።

በሕይወት ካሉ ባለውለታዎች ይልቅ በሕይወት የሌሉ ክብርና ሞገስ በሚያገኙበት ጊዜ ላይ፤ ተመራማሪው ተወልደ ብርሃን በሕይወት እያሉ ደጋግመን እናስባቸውና እናመሰግናቸው ዘንድ ምክንያት እነሆ ተገኘ። ይህም ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ የመጽሐፍ ሥራዎችን የሚያቀርበው ደራሲ ዘነበ ወላ የተወልደ ብርሃንን ግለ ታሪክ ለአንባቢ ማድረሱ ነው። ባሳለፍነው ማክሰኞ፤ ሐምሌ 16 “የምድራችን ጀግና” እንዲሁም “ኢትዮጵያዊው ሳይንቲስት” የተሰኙ ኹለት መጻሕፍት በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ በድምቀት ተመርቀዋል።

አዲስ ማለዳ ከመጽሐፉ ምርቃት ቀደም ብላ ከኹለቱ መጻሕፍት ደራሲ ዘነበ ወላ ጋር ባደረገችው አጠር ያለ ቆይታ፤ የደራሲ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ወንድም ሰለሆኑት ስለ ተወልደ ብርሃን ግለ ታሪክ መጽሐፍ ማዘጋጀቱ እንደምን ሆነ ስትል ጠይቃዋለች (አስቀድሞ የስብሐት ገብረእግዚአብሔር ሕይወትና ሥራዎች ላይ የሚያተኩር መጽሐፍ ለአንባቢ አድርሷልና)። አንደበተ ርቱዕ ደራሲ በምላሹም “ተወልደ ብርሃን እና ስብሐት የአንድ እናትና የአንድ አባት ልጆች ናቸው። ግን ፍጹም የተለያዩ ሰዎች፤ አንዱ በሥነ ጽሑፍ ሌላው በአካባቢ ጥበቃና ተፈጥሮ ላይ ሠርተዋል። ኹለቱም ግን ለኢትዮጵያ ማዋጣት ግባቸው የነበረ ሰዎች ናቸው” ብሏል።
ዘነበ ወላ “የምድራችን ጀግና” የተባሉትንና የተገባቸውን የተወልደብርሃን የሕይወት ጉዞ እንዲያስቃኝና ሥራቸውንም እንዲመለከት መነሻ ምክንያት የሆነው የራሱ ጥያቄ ነበር። ይህም የአየር መበከል፣ ሰደድ እሳት፣ አውሎ ነፋስና መሰል ተፈጥሯዊ አደጋዎችን የተመለከተ ሲሆን፤ በየዘመኑ ረሃብ ባልተላቀቃት ኢትዮጵያ “ይህ ችግር ይቀጥላል ወይስ የቱ ጋር ነው የሚገታው?” የሚል ነበር።

የመርከብ ላይ ሕይወትን ጠንቅቆ የሚያውቀው የቀድሞው የኢትዮጵያ ባሕር ኀይል ባልደረባ የነበረው ደራሲ ዘነበ፤ ተፈጥሮን ለማስተዋልና ለማዳመጥ ቅርብ መሆኑን እርሱም ዘግይቶ ነው ልብ ያለው። ደግሞም ሐሳብና ጆሮ የሰጠውን ተፈጥሯዊ አደጋና ችግር ታዝቦ አላለፈም፤ አርቆ መመልከት ጸጋው እንደሆነ ደራሲ በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ አካባቢንና አካባቢያዊ ጉዳዮችን ለማሳየት መረጠ።

“ይህን ጥያቄ የሚመልሰው ማን ነው ስል ዶክተር ተወልደን አገኘሁ፤ እርሱም ከዕጽዋት ሳይንስ ጋር በተያያዘ ነው ሙያው። መጽሐፉን ማዘጋጀት ከመጀመሬ በፊትም ጉዳዩ እስከሚገባኝ 5 ዓመታት ፈጅቶብኛል” ሲል ዘነበ ለአዲስ ማለዳ ገለጿል። መጽሐፉን ለማዘጋጀትም በደምሩ ኻያ ዓመታት እንደፈጀበት ዘነበ ተናግሯል።
“ተወልደ ብርሃን የገበሬ ልጅ ሲሆን አስተዳደጉም ከዕጽዋት ጋር ነው። እርሱም የገባው በኋላ ነው። እኔም ይህንን ነው መሠረት ያደረግኩት” አለ ዘነበ፤ የተወልደ ብርሃንን ለሐሳቡ ልከኛ ሰው እንደሆኑት ሲገልጽ። በእርግጥም ተወልደ ብርሃን የተፈጥሮንና የአካባቢ ጥበቃን ጉዳዬ ብለው ከወጣትነት ዘመናቸው ጀምሮ ዕድሜና ጊዜያቸውን ለዘርፉ የሰጡ ሰው ናቸው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የ2008 የዓመቱ በጎ ሰው ሽልማት ‘መንግሥታዊ የሥራ ኀላፊነትን በብቃት መወጣት’ በሚል ዘርፍ፤ “የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንን ለብዙ ዓመታት በስኬት የመሩ የአካባቢ ሳይንስ ሊቅ” ብሎ ተሸላሚ ሲያደርጋቸውና አሸናፊ ሲሆኑ በአጭሩ በተነበበ ታሪካቸው ተከታዩን እናገኛለን፤
“ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር በአገራችን የአካባቢ ሥነ ሕይወትና ብዝኀ ሕይወት ጥበቃ ጉዳይ ሲነሳ ከማንም በላይ በታላቅ ክብር ሥማቸው የሚነሳ የተከበሩ ሳይንቲስት ናቸው። በዓለም ዐቀፍ ደረጃም በብዙ የምርምርና የትምህርት ተቋማት፣ ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶችና ታዋቂ ሰዎች ዘንድ የከበረ ሥም አትርፈዋል።

በተሰማሩበት መስክ የአገርንና የሕዝብን ጥቅም በማስቀደም በተለይም የአርሶ አደሮችና የአርብቶ አደሮች ጥቅም እንዲጠበቅ በቁርጠኝነት ጠንክረው ሠርተዋል።
…በተዳቀሉ እህሎች በእርዳታ ሰበብ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡና ትውልድ እንዳይበላሽ በዓለም ዐቀፍ መድረኮች ጭምር ተከራክረዋል። በአጭር መግለጫ ተገልጾ በማያበቃው ሥራቸው በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተለያዩ የክብር ሽልማቶችን አግኝተዋል። ከዚህም ውስጥ በ2006 የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የአካባቢ ጥበቃ ሽልማት ‹‹የምድር ሻምፒዮን›› ተብለው ተሸልመዋል።” ይላል።

ደራሲ ዘነበ ወላ የእኚህን ታላቅ ሰው በተለይ የሙያ ሕይወት በማስቃኘቱ ለትውልዱ አርዓያ ከማስተዋወቁም ባሻገር መጽሐፉ ከዘመን ታሻጋሪዎቹ ቀደምት ሥራዎቹን ተርታ እንዲሰለፍ አድርጎታል። ደራሲው ለአዲስ ማለዳ እንደገለጸው፤ መጽሐፉ በዋናነት “ለምን ረሃብ ይበረታብናል?” እንዲሁም “ኢትዮጵያ ትልቅ ችግር የሆነባትን ረሃብ በዘለቄታው ለምን መቅረፍ አልተቻለም?” ለሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ እንዳለው ጠቁሟል።

ይህ መጽሐፍ በጸሐፊው ችሎታ ብቻ ሳይሆን ከባለታሪኩ ክቡድነትም የተነሳ ትልቅ ዋጋ ያለው ነው። ዘነበም እንዳለው፤ የሥራው ውበትና መሰል አስተያየቶች ለአንባቢ የሚተው ቢሆንም “ማንም ሰው አንብቦ መደርደሪያው ላይ የሚያስቀምጠውና ለልጁ የሚሰጠውን መጽሐፍ እንዳበረከትኩ ነው የሚሰማኝ” ሲል ተናገሯል።

ዘነበ አሁን ለንባብ ያበቃው በስፋት የተነሳው “የምድራችን ጀግና” የተሰኘው መጽሐፉ ይሁን እንጂ ተያይዞ ለንባብ የበቃና በተወልደ ብርሃን ላይ ያተኮረ “ኢትዮጵያዊው ሳይንቲስት” የተሰኘ መጽሐፍም አለ። “ኹለት መጻሕፍት ነው የጻፍኩት፤ አንደኛው ‘’የምድራችን ጀግና’’ የሚለው ሲሆን ይህም ዶክተር ተወልደ ስለራሱ የተናገረው፤ የሕይወት ታሪኩና ሥራው ላይ ያተኮረው ነው። ኹለተኛው ደግሞ ዶክተር ተወልደ ስለራሱ ያለውን ጨምሮ የ18 ሰዎችን ቃለ መጠይቅ ይዟል።

ይህም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች የሆኑና የእርሱ ተማሪዎች የነበሩ ይገኙበታል። በተጨማሪም በዓለም እንዲሁም በአገር ዐቀፍ መድረኮች ያደረጋቸውን ንግግሮችና አራት ጥናታዊ ሥራዎች የተካተቱበት ነው።” ብሏል።

ከዚህ መጽሐፍ ሻገር ስንል፤ ከዚህ በኋላም አንባቢ “እጅህ ከምን?” ለሚለው ምላሹ ምን እንደሆነ አዲስ ማለዳ ላቀረበችለት ጥያቄ ዘነበ፤ “‹‹ልጅነትን›› ካነበባችሁ፤ እንግዲህ ደግሞ ቀስ ብዬ ወጣትነትን መሞከሬ አይቀርም” በማለት መልስ ሰጥቷል። ወጣት ተስፋ እንዳይቆርጥ፣ ሩቅ እንዲመለከት፤ በመንፈስም በሥጋም እንዲታገል የሚያደርግ መጽሐፍ ለማበርከት እንደሚሞክርም ተስፋውን ገልጿል። ረጅም ጊዜንና ብዙ ሐሳቡን ከፍሎ ይዞ የቆየው ይህ ለንባብ ያበቃው መጽሐፍ ግን የተወሰነ እረፍት ሳይጠይቀው አይቀርም።

ከ1961 ጀምሮ በከፍተኛ የትምህርት ተቋም በመምህርነትና በከፍተኛ የኀላፊነት ደረጃዎች፤ እንደውም አስመራ ዩኒቨርትሲቲ በፕሬዝዳንትነት ለስምንት ዓመታት ያገለገሉት፤ ከ1983 የመንግሥት ለውጥ በኋላም የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ስትራቴጂ ሴክሬታርያት ዳይሬክተርና ቀጥሎ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን ብዙ ያገለገሉት ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር፤ የደራሲ ዘነበ ወላን ጥያቄ ለመመለስ ትክክለኛ ሰው ሆነው ተገኝተዋል። የእርሱን ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ለአንባቢም መልስ የያዘው መጽሐፍ የመጻሕፍት ገበያውን ተቀላቅሎ አንባቢን መጠባበቅ ጀምሯል።

ዘነበ ወላ ከዚህ ቀደም ‹‹ማስታወሻ›› በሚል ርዕስ የደራሲ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔርን ሕይወትና ሥራዎች በተመለከተ አንድ ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ለአንባቢ ያደረሰ ሲሆን፤ ‹‹ሕይወት በባሕር ውስጥ››፣ ‹‹ልጅነት›› እና ‹‹መልህቅ›› የተሰኙ መጻሕፍትንም ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል። በአሁኑ ሰዓትም በጄቲቪ ኢትዮጵያ ‘ከፀሐይ በታች’ የተሰኘ ሳምንታዊ ዝግጅት እያቀረበ ይገኛል።

አዲስ ማለዳ ሐምሌ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here