ወታደራዊ አስተዳደር በደቡብ፣ ‘የእናት አገር ጥሪ’ በትግራይ!

0
386

የፌደራል መንግሥቱ ሐምሌ 11 ከሲዳማ ክልልነት ጋር በተያያዘ የተከሰተውን ኹከት ሌሎች የክልልነት ጥያቄዎችን ጸጥ ለማሰኘት ተጠቅሞበታል፤ የትግራይ ክልል መንግሥት በበኩሉ ባለፈው ሳምንት የንግዱ ማኅበረሰብ አስተባበረው የተባለውን ‘ቴሌቶን’ሕወሓት ሕዝባዊ ድጋፍ ለማሰባሰብ ተጠቅሞበታል በማለት ግዛቸው አበበ ያትታሉ።

ለውጥ መጣ ከተባለ በኋላ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ጨምሮ የለውጥ መሪ የሚባሉት ሰዎች በየአጋጣሚው ኢሕአዴግ አለ፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲ መመሪያችን ነው፣ አሁን ያለው የፌደራል አወቃቀር ይቀጥላል፣ ሕገ መንግሥቱ ብዙ ደም የፈሰሰለት ስለሆነ ይከበራል ወዘተ…. እያሉ ግራ ሲያጋቡን ከርመዋል። የሲዳማ ሕዝብ የሚያነሳውን የመሰለ ጥያቄ ሲነሳ ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ሳይሻሻል መመለስ የለበትም ሲባል ይሰማል። ያለ ፍኖተ ካርታ የሚመራው ለውጥ ግራ ማጋባቱን ቀጥሎ፣ አሁን ደግሞ የለውጡ መሪዎች ከሕወሓት ኢሕአዴጋዊ ባሕሪቸውም ጋር በቀድሞ ቦታቸው እንዳሉ ለማወቅ የተገደድንበት ጊዜ በመምጣት ላይ ያለ ይመስላል።

ሰው ተቃውሞ በማሰማቱ ብቻ በአሸባሪነት ተፈርጆ እየታሰረ ነው፣ ድሮ ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን መናድ እየተባለ ሲካሔድ የነበረው ውንጀላ ዛሬ መፈንቅለ መንግሥት ለማካሔድ አሲረዋል በሚል ብዙ ሰዎች እየታሰሩ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አመራር በትዕግስተኛት ሥም በርካታ ሕገወጥ ድርጊቶች በመላ አገሪቱ ሲፈጸሙ ዝም ማለቱ አንድ ትልቅ ስህተት መሆኑ እየታወቀ አሁን ደግሞ ትዕግስታችን አልቋል ወይም ሕግን እናስከብራለን በሚል ሽፋን ወደ አምባገነንነት የተመለሰ በሚያስመስል መፍገምገም ውስጥ መዘፈቁ ሌላ ስህተት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሐምሌ 11/2011 ወደ አስመራ በረራ ሲያደርጉ፣ የፌደራል ታጣቂ ኀይሎች ወደ ጦርነት እንደሚገባ ኀይል ተዘጋጅተው ወደ ሲዳማ፣ በተለይም ወደ ሐዋሳ ከተማ አምርተዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጦር ወደ ከተማዋ ገብቶ ዋዜማው ላይ ማሳሰቢያና ማስጠንቀቂ ከመስጠት ይልቅ ወደ ጎዳናዎችና ወደ አደባባዮች የሚወጣን ሕዝብ ጠመንጃውን አቀባብሎ መጠባበቁን መርጧል። ከዚያም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአስመራ ጎዳናዎች ላይ ሲንሸራሸሩ በሲዳማ ጎዳናዎች መልአከ ሞት የደም ሱሱን ለማርካት ተንጎራድዷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከፕሬዘደንት ኢሳያስ ጋር ሲሳሳቁ ሲዳማ ውስጥ መትረየሶችና ክላሽንኮቮች ያሽካኩ ነበረ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ አስመራ አውሮፕላን ማረፊያ በሚወስደው መንገድ ላይ ችግኝ ሲተክሉ ሲዳማ ውስጥ በየቦታው ለጋ ወጣቶች ይቀጠፉ ነበር።

የሲዳማን ሕዝብ ጥያቄ አሁን በሥራ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥት ተከትሎ መልስ መስጠት ሲገባ ከረዥም ጊዜ ዝምታ በኋላ ‘እንዳያማህ ጥራው…….’ ዓይነት ሥራ መሥራት ተመረጠ። መልስ መስጠቱ ቢቀር ችግር እንዳይከሰት የጥንቃቄ እርምጃዎች ለመውሰድ የሞከረ የለም። የፌደራሉም ሆነ የክልሉ መንግሥት እስከ ሐምሌ 10/2011 ምሸት ባለው ጊዜ አንዳች የእንቅስቃሴ ወይም የስብሰባ ወይም የሰልፍ ገደብ መጣልና እልቂት ለማስቀረት መዘጋጀት ሲገባቸው፣ የወዳጅነት እግር ኳስ ጨዋታ የሚካሔድበት ጊዜ ይመስል ጠመንጃዎች እየተወለወሉ ዕለቱ እንዲደርስ አድርገውታል።

አንድ የአገር መሪ በአገሩ ውስጥ ያንዣበበ ወይም የተከሰተ ችግር ወይም አደጋ ሲኖር ወደ ጉብኝት መሔድ ቀርቶ ጉብኝት ላይ ከሆነ እንኳን አቋርጦ ወደ አገሩ መመለስ ይጠበቅበታል። በሲዳማ የተከሰተው ውጥረት በውጭ ያለ መሪን ወደ አገር እንዲመጣ የሚያስገድድ ቢሆንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀኑን ጠብቀው ከአገር ወጥተዋል፤ የሚደግሱትን ደግሰው ወደ አስመራ በርረዋል ማለት ይቻላል። የእልቂት ዛቻውን ወደ ተግባር ለመቀየር የእልቂት ድግስ ላዘጋጁት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከአስመራ ውጭ ሌላ ምቹ ቦታ የለምና ወደ አስመራ ተጉዘው በሲዳማ ዞን የሚሆኑ ነገሮችን ተከታትለዋል። እዚያው ሆነው ተጨማሪ መመሪያና ትዕዛዝ ሰጥተውም ሊሆን ይችላል።

ከሰኞ፣ ሐምሌ 15/2011 ጀምሮ ደቡብ ኢትዮጵያ የሚባለው ክልል በሙሉ በወታደራዊ ዕዝ ሥር ገብቷል ወይም ወታደራዊ አስተዳደር ሰፍኖበታል። በደቡብ ኢትዮጵያ በየትኛውም ዞን ሰልፍ፣ ስብሰባና ማንኛውንም ዓይነት ሕዝባዊ እንቅስቀሴ ማካሔድ አገደኛ ጨዋታ እንደመጫወት ሆኗል። ይህን የተመለከቱ አንዳንድ ወገኖች የሲዳማው ግጭት ሆነ ተብሎ የተጠበቀው ለዚህ ነው፣ ሲዳማዎችን ብቻ ሳይሆን የክልልነት ጥያቄ የሚያነሱ ሌሎች ሕዝቦችንም ጸጥ ለማሰኘት መንግሥት የሐምሌ 11/2011 የኹከት ቀን እንዲሆን አድፍጦ ተጠባብቋል ይላሉ።

በሌላ በኩል በ2010 ሕወሓት ወደ መቀሌ መፈርጠጡን ተከትሎ፣ በተካሔደ አንድ ስብሰባ ላይ ትግራይ ዙሪያዋን በጠላት ስለተከበበች ትግራይን ለመከላከል ዘብ መቆም አለብን የሚል ሽብር ነዥ ወሬ ተስተጋብቶበት ነበር። በዚያ ወቅት ሸፈንፈን ተደርጎ ቢሆንም ትግራይን ከበዋታል የተባሉት ጠላቶች ኤርትራና አማራ መሆናቸውን ይነገር ነበረ። በዚህ ስብሰባ ትግራይን ለመከላከል የትግራይ ሕዝብ መዋጮ ያደርግ ዘንድ መወትወትም ትኩረት ተሰጥቶት ነበረ። ነገር ግን ከስብሰባው ተካፋዮች አንዱ የሕወሓት ዋና ዋና ሰዎችን በመጥቀስ ራሳችሁን ለማዳን ወደ ትግራይ የሸሻችሁት እናንተ ናችሁና የትግራይ ሕዝብ ጠላት የለውም የሚል ተቃውሞ ሲያሰማ ሌሎች ደግሞ ይህ ትግራይን ለመከላከል በሚል ሥም የሚካሔድ የመዋጮ ጥሪ የሌለ ጠላትን እንደ መጥራት ነው በሚል ተቃውሞ ስላሰሙ ነገሩ በዚያው ተዘግቶ ቆይቷል።

ሰኔ 15/2011 የተከሰተውን ነገር ተከትሎ ግን የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በይደር የቆየውን የመከበብ ወሬ እንደገና አንስተውታል። እሳቸው ‘ትምክህተኛ ኀይሎች’ ያሏቸው ወገኖች፣ በትግራይ ላይ ብቻ ሳይሆን በፌደራላዊ ስርዓቱና በሕገ መንግሥቱ ላይ ተነስተዋል። የትግራይን ሕዝብ ወደ ባርነት ቀንበር ለመመለስ አሲረዋልም ብለዋል። ሕወሓት ከ1967 ጀምሮ ትምክህተኛ ብሎ በጠላትነት የፈረጀው የአማራን ሕዝብ መሆኑ ይታወቃል። እንዲያውም በማንፌስቶ-68 ላይ ‘ጨቋኝ ብሔር’ ብሎ አማራውን በጅምላ ፈርጆታልና የሰኔ 15ቱን ክስተት ተከትሎ የትምክህት ኀይሎች በትግራይ ሕዝብ ላይ ተነስተዋል ብለው ሲቀሰቅሱ አማራው ሕዝብ በትግራይ ሕዝብ ላይ በጠላትነት ለመዝመት ተዘጋጅቷል እንደማለት ነው። በዚህም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ሕዝብን ግጭት ውስጥ ለመሞጀር እያሴሩ መሆኑ ማንም ሊዘነጋው አይገባም፤ በተለይም የአማራ ሕዝብ እና አዴፓ።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የትግራይ የንግድ ማኅበረሰብ አስተባበረው በተባለው የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ላይ 250 ሚሊዮን ብር ለመሰበሰብ ታቅዶ ወደ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ (519 ሚሊዮን ብር) ለማዋጣት ቃል መገባቱን ከተለያዩ የዜና ምንጮች ሰምተናል። እነ ኢቲቪ መዋጮው ለልማትና የሥራ አጥነት ችግርን ለማቃለል ሲባል የሚደረግ መሆኑን ቢናገሩም ዶቼቨለ የአማርኛው ክፍል ላይ መዋጮው “የትግራይን ደኅንነነት ለመጠበቅ” በሚል አርዕስት ጭምር መካሔዱን አሳውቋል። ዶቸቨለ ያነጋገራቸው የትግራይ ኮሚውኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ ትግራይ በተለየ ሁኔታ ውስጥ እንዳለች፣ ጊዜው የሰላምና የደኅንነቱ ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ የገባበት አስቸጋሪ ወቅት መሆኑን፣ የገንዘብ መዋጮው ከተጀመረ 3ኛ ወሩን መያዙንና ቀጣይ መሆኑንም ጭምር ገልጸዋል። በትግራይ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ካለፈው ወር ጀምሮ ከደሞዛቸው 10 በመቶ እስከ 100 በመቶ እያዋጡ ወደ 41 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡ ተነግሯል።

ይህን በመሰለው የ‘ቶሌቶን’ ዘመቻ ከሚሰበሰበው ገንዘብ በተጨማሪ ፕሮፓጋንዳ ለመሥራትና ሕዝባዊ ድጋፍ ለማሰባሰብ የሚጠቅም መሆኑ ግልጽ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የትግራይ ሕዝብ እና ባለሀብቶች ከሕወሓት ጎን መቆማቸውን ለማሳየት ወይም ከትግራይ መንግሥት ጎን የቆሙ የሚያስመስል ድራማ ለመሥራት ጭምር የሚደረግ ነው ማለት ይቻላል።
ግዛቸው አበበ መምህር ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው gizachewabe@gmail.com ይገኛሉ።

አዲስ ማለዳ ሐምሌ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here