በየመን 15 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሞቱ

0
491

ከጅቡቲ ወደ የመን በጀልባ በመጓዝ ላይ የነበሩ 15 ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸው እንዳለፈ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት (IOM) አስታወቀ። ከሞቱት ኢትዮጵያውያን አንዳንዶቹ በረሃብ እና በውሃ ጥም፣ የተቀሩት ደግሞ በውሃ ውስጥ ሰጥመው ሕይወታቸው ማለፉን ከአደጋው የተረፉት እንደተናገሩ ድርጅቱ ረቡዕ፣ ሐምሌ 24 ማታ በትዊተር ገጹ ላይ አስታውቋል።

የመን መድረስ ከቻሉት የተወሰኑትም የሕክምና እርዳታ ከማግኘታቸው በፊት ሕይወታቸው ማለፉን ያስታወቀው መሥሪያ ቤቱ፣ ስደተኞቹ አደጋው የደረሰባቸው ጀልባቸው መንገድ ላይ ከተሰበረ በኋላ መሆኑን ገልጿል። 90 ኢትዮጵያውያንን አሳፍሮ ከጅቡቲ የተነሳው ጀልባም ረቡዕ በየመን ደቡባዊ የወደብ ከተማ ኤደን መድረሱንም ተናግሯል።

ከአደጋው ከተረፉት አብዛኛዎቹ የት እንዳሉ አይታወቅም። እንደ የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት በኤደን እና በአጎራባቿ በላህጅ በሚገኙ ኹለት የስደተኞች ማጎሪያ ማዕከላት የሚገኙ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን የሆኑ ከ3 ሺሕ በላይ ስደተኞች ሰብኣዊነት በጎደለው አያያዝ እየተሰቃዩ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል። የመን ከ4 ዓመታት በላይ በጦርነት እየታመሰች ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ስደተኛ ዜጎችንም በውስጧ ይዛለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 39 ሐምሌ 27 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here