የወርቅ ንግድ ከ430 ሚሊዮን ወደ 32 ሚሊዮን ዶላር አሽቆለቆለ

0
678

በ2006 አካባቢ ከወጪ ንግድ ከቡና ንግድ ቀጥሎ 430 ሚሊዮን ዶላር ይገኝበት የነበረው የወርቅ ንግድ ባለፈው ዓመት ወደ 32 ሚሊዮን ዶላር ማሽቆልቆሉ ታወቀ።

ወርቅ፣ ኦፓል፣ ሳፋየር፣ ታንታለም፣ እምነበረድ እና የመሳሰሉትን ለውጭ አገር የምታቀርበው ኢትዮጵያ ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚሆኑ ሌሎችንም ማዕድናት ታመርታለች። አገሪቱ ሰፊ የማዕድን ሀብት ክምችት እንዳላት ቢነገርም በስፋት ጥቅም ላይ ሲውል ግን አይስተዋልም። ለገበያ የሚቀርቡትም ቢሆን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ማሽቆልቆላቸው ሥጋትን አጭሯል።

የኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ ልማት ታሪክ እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ይነገርለታል። የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት አጭር ጊዜ ያለው ከመሆኑም ባሻገር በትክክልም አገሪቱ ካላት ገጸ በረከት ይልቅ ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻለች ነው የሚወሱት። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ አገሪቱ እያስተናገደች ያለችው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳው እና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችም ማሽቆልቆል እየታየባቸው ስለመሆኑ ሲነገር ይሰማል።

ያለፉትን ስድስት ወራት የአገሪቱን የኢኮኖሚ ሁኔታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት የብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ወርቅን በተመለከተ ያቀረቡት መረጃ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ይሆናል። “ወርቅን በተመለከተ በ2006 አካባቢ ወደ ከወጪ ንግድ አኳያ ከቡና ንግድ ቀጥሎ 430 ሚሊዮን ዶላር ይገኝ ነበር። ባለፈው ዓመት ይሔ ወርዶ ወርዶ ወደ 32 ሚሊዮን ዶላር ነው የሆነው። አሁን ባለው ሁኔታ የኮንትሮባንድ ሰለባ ሆኗል። በዚሁ ከቀጠለ ከወርቅ የምናገኘው የውጭ ምንዛሬ ከጊዜ በኋላ ይኖራል ብሎ መገመት ያስቸግራል” ሲሉ ይናገር የሁኔታውን አሳሳቢነት ጠቁመው ነበር።

ቅጽ 1 ቁጥር 39 ሐምሌ 27 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here