ቀርከሃን በጥበብ

0
714

አብሮ አደግ ናቸው፤ ፍቅርተ ገብሬ እና ወይንሸት አጨራምቶ። አሁን ላይ በጋራ ሆነው እየሠሩ ካሉት ፍቅርተ እና ጓደኞቻቸው የቀርከሃ ሥራ ኅብረት ሽርክና ማኅበር በሚል ሥያሜ ከሚጠራው የቀርከሃ ሥራቸው በፊት የተጋሩት ሕይወት ነበር፤ ስደት። ፍቅርተ በስደት ከዐሥር ዓመት በላይ ቆይታለች። አካሔዳቸው ሕጋዊ ነበርና ምንም እንኳ ኹለቱም እጅግ የከፋ የገጠማቸው ነገር ባይኖርም፤ ስደት ትምህርት ቤት ነው በሚለው የፍቅርተ አባባል ይስማማሉ።

ፍቅርተ “በስደት ሰው አገር ዝቅ ብለን ስንሠራ ቆይተን፥ አገራችን ሥራን መናቅና ዝቅ ብሎ መሥራትንም መጥላት የለብንም” ትላለች። ወይንሸትም በበኩሏ አራት የሚጠጉ ዓመታትና በስደት ቆይታለች፤ እርሷም ስደት አስቀያሚ መሆኑን ሳትጠቅስ አላለፈችም።

ይህን የተሻገሩት እነዚህ ሴቶች አገራቸው ከተመለሱ በኋላ አንድ ጥሩ ዕድል ገጠማቸው። በሚኖሩበት ቀበሌ የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ ያመጣው በተለያዩ ሙያዎች የሚሰጥ ሥልጠና ነበር። ዋይዝ የተባለ ራስ አገዛ ቡድን እንዲሁም ቻዲቲ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ከወጣት ሴቶች መቋቋሚያ ማኅበር ጋር ተባብረው ያደረጉላቸውን ድጋፍ ኹለቱም አይረሱም። በተለይም በቀርከሃ ሥራ የተሰጣቸውን ሥልጠና እንዳጠናቀቁ፤ “የሥራ ቦታ እስክታገኙ ድረስ በተማራችሁበት ስፍራና በሰለጠናችሁባቸው መሣሪያዎች እየሠራችሁ መቆየት ትችላላችሁ” ሲባሉ በጊዜው ከነበሩ ሠልጣኞች መካከል በብቸኛነት አጋጣሚውን ለመጠቀም አላንገራገሩም።

ወደ ሥራው ከገቡ በኋላ ታድያ “ከውጪ መጥተው እዚህ አቧራ ያቦናሉ!” እያለ የሚተቻቸው ብዙ ነበር። ይሔኔ ነው በሰው አገር ዝቅ ብለን ስንሠራ ቆይተን በአገራችን ሲሆን ግን ዝቅ ብሎ መሥራትን መጥላት የለብንም በሚለው ሐሳባቸው የጸኑት። ድርጅቶቹ ከሰጧቸው ድጋፍ ላይ የራሳቸው ብርታት ሲደመር፤ በኤግዚቢሽን እና ባዛሮች ላይ ለመሳተፍና ምርቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁ አገዛቸው። ዳዴ በሚመስል አካሔድ ጀምረውም በእግራቸው ቆመው መሔድ ላይ ደረሱ።

አዲስ ማለዳ በቀርከሃ ሙያ ከተሰማሩት ከእነዚህ ወጣቶች ጋር ባደረገችው ቆይታ ሴቶች አብረው ተስማምተው መሥራት አይችሉም የሚለውን የተለመደ ብሂል ውድቅ ማድረጋቸውን ታዝባለች። ፍቅርተ “አብሮ መሥራት በጣም ከባድ ነው፤ ነገር ግን ደግሞ አብሮ መሥራት ያሳድጋል” ስትል ያላትን ተመክሮ አካፍላለች።

ወይንሸትም ከፍቅርተ ሐሳብ ጋር ትስማማለች። አብሮ በመሥራት ውስጥ የሚገኘውን ዕድገት በማሰብ መከባበርና መቻቻል፤ መተጋገዝና መረዳዳት ያስፈልጋል ትላለች። በእነርሱም በኩል ሴት በመሆናቸው ሳይሆን በሥራ ሁኔታዎች የማይስማሙበት፤ ነገር ግን መልሰው የሚግባቡበት አጋጣሚ ብዙ እንደሆነ አውስታለች።

ካልተረዳዱ አብሮ ማደግ አይታሰብም የምትለው ወይንሸት፤ በወሊድ ጊዜ እንኳን ሥራዎችን እየተሸፋፈኑና እየተጋገዙ መቆየታቸውን ዋቢ አድርጋለች፤ ከሙያ ፍቅር ውጪ አብሮነታቸውን የሚፈታተን የባሕሪ ለውጥ እንዳልገጠማቸው የሦስት ዓመታት ጉዟቸውን ለማስረጃነት ጠቅሳለች።

ቀርከሃ
ኹለቱ ወጣቶች ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በቀርከሃ የተለያዩ ጌጣጌጦችን ያዘጋጃሉ። የብዙዎችን ትኩረት መሳብ የቻሉት እነዚህን የቤት ውስጥ ማስዋቢያና የተለያዩ ጌጣጌጦችን ስለሚያዘጋጁ መሆኑንም ይናገራሉ። ፍቅርተ “በብዛት የምናተኩረው ጌጣጌጥ ላይ ነው፤ ብዙውን ጊዜ በቀርከሃ መሥራት የተለመደው የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች [እንደ] ሶፋና ወንበር [ያሉት] ናቸው። ነገር ግን ቀርከሃን ለብዙ ነገሮች [ለመሥሪያነት ያገለግላል] በተለያየ መንገድ መጠቀም ይቻላል፤ ድስት ሆኖ እሳት ላይ ብቻ ነው የማይጣደው” ብላለች።

በየጊዜውም አዳዲስ ፈጠራዎችን በማቅረብና በብረት እንዲሁም በእንጨት ተሠርተው ያዩትን በቀርከሃ በመሥራት፤ ቀርከሃ ላይ ጥበብን አክለው ፈጠራውን ያሳድጋሉ። እንዲያም ሆኖ ግን ብዙ ይቀረናል ባይ ናቸው። ወይንሸት እንዳለችው ቀርከሃ የመተጣጠፍ ጸባይ አለው ወይም ይታዘዛል። እነርሱም ይህን ታዛዥነቱን እየተጠቀሙበት ነው። ይሁንና ውጪ አገራት ከተሠሩት አንጻር ሲታይ ግን ብዙ እንደሚቀራቸውና፤ ያለጥርጥር ደግሞ ትልቅ ደረጃ ላይ እንደሚደርሱ በአንድ ቃል ተናግረዋል።

በአገራችን ለቀርከሃ ያለውን ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑን ሳያነሱ አልቀሩም። በተለይም ፍቅርተ ሸንበቆና ቀርከሃ መካከል ያለውን ልዩነት አጥርተው ያላወቁና ተመሳሳይ የሚመስላቸው እንዳሉ ጠቅሳለች። ከዛም ባሻገር ቀርከሃን ለዋና አከፋፋዮች የሚያቀርቡ አርሶ አደሮችም ጋር በተመሳሳይ በቂ ግንዛቤ እንደሌለ ነው ፍቅርተ የምታነሳው።

“ገበሬው ጋር በቂ ግንዛቤ የለም። ቀርከሃ ወደ ሥራ ሲቀየር ቶሎ ይነቅዛል የሚባለው ችግር የሚመጣው ከአሠራር አይደለም፤ ከአቆራጥ ጋር የተያያዘ ነው። ከሳር ዝርያ የሚመደበው ቀርከሃ በሦስት ወር ውስጥ ረጅም ይሆናል፤ ለመቁረጥ ግን ሦስት ዓመት ሊጠበቅ ያስፈልጋል። ይሁንና ለመቆረጥ ዝግጁ ነው ወይ የሚለው ትኩረት ሳይሰጠው ስለረዘመ ብቻ የሚቆርጡት አሉ” ስትል ያብራራችው ፍቅርተ፤ ቀርከሃ ጊዜውን ጠብቆ በአግባቡ በወቅቱ ቢቆረጥ የመንቀዝ ሁኔታውን ጨርሶ እንደሚወጣ ገልጻለች።

ፍቅርተና ወይንሸት እንዲሁም ሥራውን አብረዋቸው የጀመሩት ጓደኞቻቸው ድርጅታቸውን አሁን ካለበት ደረጃ ለማድረስ ብዙ መሰናክሎችን አልፈዋል። ገቢያቸውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መሔዱን እንዲሁም ድርጅታቸውንም እንዲያሳድጉ እንደረዳቸው ኹለቱም ይናገራሉ።

ፍቅርተ “አሁን ያለንበት ቀበሌ የሰጥን ቦታ ላይ በነበረን የስድስት ወር ቆይታ ብዙ ሥራዎችን ማከናወን ችለናል። በዚህ አካሔዳችን [የበለጠ] እየጨመርን ነው የምንሔደው” ስትል፤ ጓደኛዋ ወይንሸትም በበኩሏ “ሥራውን መሥራቴ በራሱ እርካታን የሚያስገኘኝ ገቢዬ ነው” ስትል በልበ ሙሉነት ትናገራለች። ሥራው አሁን ላይ ጥሩ ገቢ እንዳለውና ወደ ፊት ትልቅ ገቢ የሚያገኙበት እንደሚሆን ኹለቱም በሚገባ እርግጠኛ መሆናቸውን አዲስ ማለዳ ታዝባለች።

በሥራው የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ሰዎችም አሉ። እንደ ፍቅርተ ገለጻ፤ በትዕዛዙ ልክና እንደ ሥራው ሁኔታ በቁጥር እስከ ዐሥር የሚደርሱ ሠራተኞች የሚያስፈልግበት ጊዜ ሲኖር እነዚህም በጊዜያዊ ቅጥር የሚካተቱ ናቸው። አዲስ ማለዳ ረቡዕ፣ ሐምሌ 24 ከመገናኛ ወደ ካዛንችስ በሚወስደው መንገድ መለስ ፋውንዴሽን ፊት ለፊት ከሚገኘው የማምረቻና መሸጫ ስፍራ በአካል ተገኝታ አራት ተጨማሪ ባለሙያዎች በሥራ ገበታቸው ላይ መኖራቸውን ታዝባለች።

እንደሚቀበሉት ትዕዛዝ ብዛት የአጋዥ ሠራተኞች ቁጥር ከፍም ዝቅም ሊል እንደሚችል፤ አንዳንዴም ፍቅርተና ወይንሸት ብቻቸውን ያለአጋዥ የሚሠሩበት አጋጣሚ እንዳለም በተጨማሪም ለመረዳት ችላለች።

ኹለቱ ብረቱ ሴቶች የየራሳቸውን ቤተሰብም መሥርተዋል፤ ወይንሸት የኹለት ዓመት ልጅ እናት ስትሆን፤ ፍቅርተ ደግሞ አንዲት የሦስት ዓመትና አንድ የስምንት ወር ልጆች አሏት። ቤተሰቦቻቸው በሚችሉት ሁሉ በማበረታታትና በሐሳብ እንደሚደግፏቸውም ገልጸዋል። በተለይም ስለ ሥራ ወዳድነታቸው ሲናገሩ፥ ፍቅርተ የእናቷን ታታሪነት ስታነሳ ወይንሸትም ደግሞ በሕይወት ባይኖሩም የአባቷን ምክር ትጠቅሳለች። ቤተሰቦቻቸው የፍሬያቸውን ውጤት እያዩ ሲሔዱ ደስታ እንደሚሰማቸውም ይገልጻሉ።

ወጣቶቹ መልዕክታቸው በአንድ በኩል የሥራ ሐሳብና አቅም ላላቸው ወጣቶች፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሥራ በመጀመር ሒደት ውስጥ “ኑ ተደራጁ!” ብለው ጠርተው መልሰው ብዙ ፈተናን ለሚያስቀምጡ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ነው። ወጣቶች የፈለጉት ደረጃ ለመድረስ ችግሮችን መጋፈጥ ዋናው መንገድ ነው የሚሉት ወይንሸትና ፍቅርተ፥ የመንግሥት ኀላፊዎችን በተመለከተ ደግሞ ተቀምጦ ከመወሰን ወረድ ብሎ መሬት ላይ የሚሠራውን በማየት አቅምና ችሎታ ላላቸው ከዛም አልፎ ህልመኞች ስኬታማ እንዲሆኑ መርዳት አለባቸው ሲሉ ሰሚ ካለ በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 39 ሐምሌ 27 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here