አዲስ የውርጃ በሽታ ከብቶችን እያጠቃ መሆኑ ታወቀ

0
390
  • በሽታው ለአገራችን አዲስ ነው ተብሏል

በደቡብ ክልል እና በአዲስ አበባ ዙሪያ የተከሰተው እና የወተት ላሞችን የሚያጠቃው የውርጃ በሽታ መለየቱን የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ። ለመውለድ የደረሱ ላሞችን የሚያጨነግፈው ይህ በሽታ በዩኒቨርሲቲ የወተት ላሞችን የእርባታ ሒደት ለማስተጓጎል ምክንያት መሆኑን ተከትሎ፣ በተደረገ ምርመራ አዲስ ሦስት የበሽታ አምጪ ተህዋሲያን ዓይነቶችን መለየት መቻሉ ታውቋል።

የዩኒቨርሲቲው የእንስሣት ትምህርት ክፍል አስተባባሪ ካሳሁን አስማረ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት በሽታው ለአገራችን አዲስ እንደመሆኑ ዩኒቨርሲቲያቸውን ጨምሮ በርካታ ጥናቶች እየተደረጉ መሆኑን አክለው ገልጸዋል። በሌሎች አገራት እንደሚገኝ የሚታወቀው ይህ በሽታ፥ በፍጥነት እልባት ካልተበጀለት በእንስሣት ሀብት ላይ ከፍተኛ አደጋ ማምጣቱ እንደማይቀርም ካሳሁን ተናግረዋል።

የበሽታ አምጪ ተህዋስያኑ የሕይወት ዑደታቸውን የሚያካሒዱት በእንስሳቱ ውስጥ ብቻ ሳይሆን፣ ውሻና ድመትን ከመሳሰሉ ሌሎች የቤት እንስሳት ጋር ከፍተኛ ተዛምዶ እንዳላቸው በምርምር ሥራው ለማረጋገጥ መቻሉን ካሳሁን አውስተዋል። ይህም የመተላለፊያ መንገዶቹን በማስፋት እና እንስሳቱን ለከፍተኛ ጉዳት በመዳረግ የምርት መጠኑ እንዲቀንስ ምክንያት መሆኑን ያብራራሉ።

በምርምር ሥራው የእንስሳቱ የመራባት ሒደት ለማጨናገፍ ምክንያት የሆኑ የበሽታ አምጪ ተህዋስያኑ ያላቸው ባሕሪ ላይ ጥናት ተደርጓል። እነኝህ የበሽታ አምጪ ተህዋሲያን የእንስሳቱን የውልደት ሒደት በማስተጓጎል ለምርቱ አለማደግ ምክንያት መሆናቸውን ያብራሩት ባለሞያው፣ የበሽታ አምጪ ተህዋሲያኑ የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ የግብርና ሚኒሰቴርን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት ጋር እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከእነዚህ ተዋህስያን በተጨማሪ ለኢትዮጵያ ከብቶች ሥጋት ሆኖ በመጠቀስ ላይ የሚገኘውና የከብቶችን ሞት በማፋጠን ላይ ያለው የቆላ ዝንብ በሽታ መሆኑን ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። በሽታው ከሰሃራ በታች ባሉ 37 የአፍሪካ አገሮች ተሰራጭቶ የሚገኝ ሲሆን፣ 23 ያህል ዝርያዎች ተለይተው የታወቁ መሆኑም ተገልጿል።

በኢትዮጵያም የቆላ ዝንብ ባለበት አካባቢ ሰፍረው የሚኖሩ ሕዝቦችም በዚሁ በቆላ ዝንብ በሚተላለፈው የገንዲ በሽታ ምክንያት የቀንድ ከብቶቻቸውና ሌሎች የቤት እንስሳቶቻቸው ምርታማ ሊሆኑ አለመቻላቸው ታውቋል። ያላቸው የእንስሳት ሀብት ሊኖራቸው ከሚችለው ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ከመሆኑም በላይ ከእንስሳት ሀብት የሚያገኙት ውጤትም እንደዚሁ ከሚጠበቀው በታች መሆኑ በጥናት ሰነዶች ተመልክቷል። በተጨማሪም የቀንድ ከብቶችን በመጠቀም በአካባቢው የእርሻ ልማት ለማካሔድ የሚደረገውን ጥረት በሽታውን የሚያስተላልፈው የቆላ ዝንብ መኖሩ የእርሻ ከብቶች ለገንዲ በሽታ መጋለጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ አድርሶበታል።

የገንዲ በሽታን ለመቆጣጠር በአገሪቱ የተለያየ ጥረት ሲደረግ የቆየ ቢሆንም፤ ጥረቶቹ በአብዛኛው ያተኮሩት ለበሽታው መፈወሻ የሚሆን መድኀኒት በመጠቀም እንደነበር የሚያወሳው ጥናቱ፣ በዚህም ምክንያት መድኀኒቶቹ ለረጅም ጊዜ በጥቅም ላይ በመዋላቸውና አልፎ አልፎ በአግባቡ በጥቅም ላይ ባለመዋላቸው በአንዳንድ አካባቢዎች በሽታው መድኀኒቶቹን የመላመድና የመቋቋም ሁኔታ በማሳየት ላይ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ በቀንድ ከብት ሀብት ብዛት ከአፍሪካ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ላይ ብትሰለፍም፣ የአረባብ ሒደቱ ለረጅም ዓመታት በሳይንሳዊ ምርምሮች ያልተደገፈ እና በተለምዶ የሚከናወን በመሆኑ፣ አገሪቱ ከዘርፉ የታሰበውን ጥቅም እንዳታገኝ እያደረጋት ይገኛል ሲሉም ካሳሁን ያብራራሉ። ይህ ችግር ባለበት ሁኔታ፣ አዲሱ በሽታ መከሰቱ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ያደርገዋልም ብለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 39 ሐምሌ 27 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here