የመሬት ይዞታ ካሳ በወቅታዊ ዋጋ ተሰልቶ እንዲከፈል ተወሰነ

0
467

ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትና ካሳ የሚከፈልበትን ሁኔታ ለመወሰን በወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ የካሳ አከፋፈሉ በወቅታዊ ዋጋ ተሰልቶ መከፈል እንደሚኖርበት በመጥቀስ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።

ባለ ይዞታዎች መሬቱን ከመልቀቃቸው በፊት ሦስት ዓመታት ውስጥ በየዓመቱ ከመሬቱ ሲያገኙ ከነበረው ከፍተኛውን የአንድ ዓመት ገቢ ብቻ ድጋፍ እንደሚሰጣቸው ለውይይት ቀርቦ የነበርና ካሣ ሲከፈልም ከረጅም ጊዜ በፊት በተገመተ ዋጋ መሆኑ ቅሬታ የፈጠረ ስለ መሆኑ በጥናት ተረጋግጦ እንደነበር ታውቋል። ይሁን እንጂ በውሳኔ ሐሳቡ ላይ በወቅታዊ ዋጋ ተሰልቶ የሚል ሐሳብ ተጨምሮበት እንዲፀድቅ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል። በተለይ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ የአንድ ዓመት ዓመታዊ ገቢ በ10 ተባዝቶ የሚለው ሕግ በ15 ተባዝቶ እንዲከፈል በአዲሱ አዋጅ ላይ ተካቷል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኹለተኛ አስቸኳይ ስብሰባውን ረቡዕ፣ በሐምሌ 24/2011 ባደረገበት ወቅት በከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ያፀደቀ ሲሆን አዳዲስ ሐሳቦችንም አካቷል። ከእነዚህም ውስጥ በገጠርም ሆነ በከተማ የልማት ተነሺ በሽርክና ለመጠቀም ፍላጎት ኖሮት ባለሀብቱ ይህን ለማድረግ የማያስችለው ሁኔታ ካለ ለተነሽዎች በኑሮ ራሳቸውን የሚችሉበት ተለዋጭ መፍትሔ በተነሽው፣ በባለሀብቱ እና በአስተዳደሩ መሰጠት እንዳለበት በአዲሱ አዋጅ ውስጥ ተካቷል።

ከላይ የተጠቀሱትን የሕግ ማዕቀፍ የሚተገብር እና የሚመራ ራሱን የቻለ ቡድን እንደሚቋቋም የተገለፀ ሲሆን ወይም ደግሞ ካሉት ተቋሞች ይህንን ኀላፊነት የሚወጣ አካል እንደሚሰየም ለማወቅ ተችሏል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም የሚቋቋመው ቡድን በልማት ምክንያት የተነሱ አካላት ያሉበት የኑሮ ሁኔታን ጥናት በማካሔድ በጥናቱ ለተለያዩ ችግሮች መፍትሔ እንደሚሰጥም ታውቋል።

አዲሱ አዋጅ ከዚህ ቀደም በሥራ ላይ የነበረውን የካሳ አዋጅ በሥራ ላይ ከዋለ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ እና ወቅታዊነቱ ላይ ክፍተት ስለታየበት ከፍተቱን ለመሙላት የተዘጋጀ እንደሆነ በከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የሕግ፣ ፍትሕና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተገልጿል።

ልማት ተነሽዎች ቦታው ለልማት ተፈልጎ እንዲነሱ በሚጠየቁበት ጊዜ እና ጉዳዩ የፍርድ ቤት ክርክር አስነስቶ ውሳኔ ከተሰጠበት በኋላ ይግባኝ ማለት የሚፈልጉ ከሆነ ልማቱ እንዳይጓተት ቦታውን አስረክበው ክርክሩን የመቀጠል መብት እንዳላቸው ተደንግጓል። የልማት ተነሽዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስፈልገውን በጀትና በጀቱ በማን እንደሚሸፈን መወሰን እንዳለበት በአዲሱ አዋጅ ላይ ሰፍሯል። በመሆኑም በኹለቱ ቋሚ ኮሚቴዎች በጋራ የቀረበው አዲሱ የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትና ካሣ የሚከፈልበትን ለመወሰን የወጣው አዋጅ በአምስት ተቃውሞ እና በአምስት ድምፅ ታዕቅቦ በአብላቻ ድምፅ ፀድቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 39 ሐምሌ 27 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here