የከተማ አስተዳደሩ የምግብ ዋጋ የሚያንሩት ላይ እርምጃ ወስዳለሁ አለ

0
366

በአዲስ አበባ ከተማ በመሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ተከትሎ የከተማው አስተዳደር ጥናት በማድረግ እርምጃ ሊወስድ መዘጋጀቱን ገለፀ።

በተለይም በአትክልት ምርቶች ላይ የታየው ጭማሪ አሳሳቢ እንደሆነ በአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ የንግድ ቁጥጥርና ክትትል የሥራ ሒደት መሪ ካሳሁን በየነ ገልጸዋል።

በአገሪቱ በነበረው የሰላም መደፍረስ ምክንያት የአትክልት አቅራቢዎች በበልግ ወቅት በሙሉ አቅማቸው ያለማምረታቸው በክረምት ወቅት የሚያጋጥመውን የምርት እጥረት አባብሶታል ብለዋል። በተለይም መቂ ከተማን ጨምሮ በመስኖ ምርት የከተማዋን የአትክልት አቅርቦት በሚሸፍኑ አካባቢዎች ላይ የተፈጠረው ጫና የተወሰነ የምርት እጥረት አምጥቷል ቢባልም ላለፉት ኹለት ሳምንታት የታየው ጭማሪ ግን ሰው ሰራሽ ሊሆን እንደሚችል ካሳሁን ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ አዲስ አባበ በአራዳ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ በሚገኘው በአትክልት ተራ ባካሔደችው ዳሰሳም አንድ ኪሎ ነጭ ሽንኩርት ከ150 እስከ 180 ብር የሚሸጥ ሲሆን በተለይ ከረመዳን ጾም ወር ጀምሮ ሲታይ ከነበረው ጭማሪ ላይ ባለፉት ኹለት ሳምንታት የ50 ብር ጭማሬ አሳይቷል። ቀይ ሽንኩርት በኪሎ ከ23 ብር ጀምሮ የማከፋፈያ ዋጋው ሲሆን በችርቻሮ ደግሞ እስከ 30 ብር ተሽጧል። እንዲሁም አንድ ኪሎ ቲማቲም በኪሎ ከ16 ብር እስከ 18 ብር ቢከፋፈልም በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ግን እስከ 20 ብር ድረስ እየተሸጠ ይገኛል።

በሌሎች የጥራጥሬ ምርቶች ላይም እስከ 15 ብር ድረስ ጭማሬ የታየ ሲሆን የዘይት ዋጋ በአንድ ሊትር ከ6 ብር እስከ 10 ብር ድረስ ጭማሪ አሳይቷል። በሸማች ማኅበራት በኩል የሚሸጡ ሸቀጦች ላይ ጭማሪ ባይታይም ስኳር አለመቅረቡን ተከትሎ በሐምሌ ወር ውስጥ በቸርቻሪ ሱቆች ውስጥ ከ35 እስከ 40 ብር በመሸጥ ላይ ነው።

የፆም ወቅት መግቢያ መድረሱን ተከትሎ የተለያዩ የአትክልት ምርቶች ላይ ጭማሪ መታየቱ የተለመደ ቢሆንም የሰሞኑ ጭማሪ ግን መጋነኑን መለየታቸውን ካሳሁን ተናግረዋል። ከትንሳኤ በዓል ጀምሮ ሲታይ ነበረውን የዋጋ ጭማሪ በተለይ የምርት አቅርቦት መስተጓጎሎችን በመቀነስ እና የተወሰኑትንም በሸማች ማኅበራት በኩል እንዲቀርቡ በማድረግ ለማረጋጋት እየሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል።

“መንግሥት የገበያ ዋጋን ለማውጣት እና ለማስገደድ ሕጉ አይፈቅድለትም፣ ነገር ግን የሕዝብ ኑሮ ላይ ጫና ለመፍጠር እና ያለአግባብ ለመበልፀግ የሚደረግ አሻጥር ላይ ግን ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ጥናታችን አጠናቀናል” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የምርቶቹ ዋጋ መጨመር ምክንያት ግልፅ አይደለም የሚሉት የአዲስ አበባ አትክልት እና ፍራፍሬ ነጋዴዎች በበኩላቸው የዋጋ ጭማሪው ምክንያት የምርት አቅርቦት እጥረት ሳይሆን ምርቶቹ ከሚገቡባቸው አካባቢዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ ስላለ መሆኑን ይናገራሉ። በመቂ፣ ዝዋይ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የመስኖ እና የበልግ አምራች አካባቢዎች ምክንያታዊ ባልሆነ መልኩ ዋጋ እንደጨመሩ እና ይህም የበዓል፣ የምርቃት፣ የሰርግ እንዲሁም የፆም ወቅት ላይ የሚደረግ የተለመደ ጭማሪ ነው ይላሉ።

በፒያሳ አትክልት ተራ አትክልት ሲገበያዩ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ስመኝሽ አድማሱ የሽንኩርት እና የቲማቲም ዋጋ በእጥፍ መጨመሩን ተናግረው በትንሹም ቢሆን በማከፋፈያ ቦታው ላይ የተወሰነ ቅናሽ ለማግኘት መምጣታቸውን ይናገራሉ።

“አማራጭ ስለሌለን እና ግዴታ ስለሆነብን ያለንን አብቃቅተን እንገዛለን” ያሉት ስመኝ “መንግሥት ጫናችንን ይመልከተልን፣ አፋጣኝ እርምጃም ሊወሰድ ይገባል” ሲሉ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 39 ሐምሌ 27 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here