የጠቅላይ ሚኒስትሩ የወላይታ ሶዶ ጉብኝት በቂ ምላሽ የሰጠ አይደለም ተባለ

0
486

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐምሌ 22/2011 ወደ ደቡብ ክልል ወላይታ ከተማ በመገኘት ከነዋሪዎች ጋር ያደረጉት ውይይት ምክረ ሐሳብ ከመለገስ ባሻገር መንግሥታዊ ውሳኔዎችን ማስተላለፍ ያልተቻለበት ነው ሲል የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ(ወብን) አስታወቀ።

የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ተከተል ላቤና ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት በዛው መድረክ ላይ የወላይታን የክልልነት ጥያቄ ይፈታሉ ብለን ባናስብም፤ ነገር ግን ለስምንት ወራት በደኢሕዴን ምክር ቤት ውሳኔ ሳይሰጠው የቆየውን የወላይታን ጥያቄ ግን ዕልባት መስጠት ይችሉ ነበር።

ለስምንት ወራት የተያዘው የክልልነት ጥያቄ የክልሉ ምክር ቤት ወደ ምርጫ ቦርድ መምራት ቢኖርበትም ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እያደረገ እንዳልሆነ ለማወቅ ተችሏል። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በሕዝባዊ ውይይት መድረኩ ላይ የክልልነት ጥያቄን በተመለከተ የተቆረጠ ነገር ባይናገሩም ወላይታ ትግል ፍፁም ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ እንደሆነ መጠቆማቸውን ተከተል ጠቅሰው የክልልነት ጥያቄ የመጠየቅ ያልተገደበ መብት እንዳላቸውም እንደተናገሩ አስታውቀዋል።

“የክልልነት ጥያቄያችሁን ማቅረብ ትችላላችሁ ተገቢም ነው፤ እንደ እኔ ግን አንድ ላይ ብትሆኑ የተሸለ ነው” ሲሉ የተደመጡት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ፤ በሕዝቡ በኩል የተጠበቀውን ምላሽ መስጠት እንዳልቻሉ መጠቆሙን በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህሩ ተከተል ላቤና ይናገራሉ።

ይህም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የግል ሐሳባቸው እንጂ ለወላይታ ሕዝብ ዘለቄታዊ መፍትሔ የሚስጥ ባለመሆኑ አሁንም የሕዝቡን የክልልነት ጥያቄ ማቅረባቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ወብን አስታውቋል። የንቅናቄውን አካሔድም ፍፁም ሰላማዊ እንደሆነና በቅርብ ጊዜያት በሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ በክልሉ ውስጥ የተነሳውን አለመረጋጋት እንዲደገም ምንም ዓይነት ፍላጎት እንደሌለው ተከተል አስረግጠዋል። “ወላይታ ዞን ፍፁም ሰላማዊ የሆነ አካባቢ ነው” የሚሉት ተከተል ከአካባቢው ሰላም የተነሳ ወላይታ ዩኒቨርስቲ በተከታታይ ዓመታት ሰላማዊ ዩኒቨርስቲ በመባል ሽልማቶችን መሸለሙን አውስተዋል።

ወብን ለአዲስ ማለዳ ጨምሮ እንደገለፀው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የወላይታ ሕዝብን ጉዳይ እና ጥያቄ በጥልቀት ገብተው ተረድተውታል የሚል እምነት እንደሌላቸው ጠቁሞ በዕለቱ የነበረው የሕዝብ ውይይትም በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቃውሞ የተሰማበት እንደነበር አስረድተዋል። በዚሁ የሕዝባዊ መድረክም ላይ የወላይታ ሕዝብ ሕገ መንግሥታዊ መብቱን ማራመድ እየቻለ እንዳልሆነ እና የክልሉ መንግሥትም ጥያቄውን በአግባቡ ማስተናገድ ባለመቻሉ ከሕዝቡ ጥያቄ እንዳስነሳ ፓርቲው ለአዲስ ማለዳ አስረድቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 39 ሐምሌ 27 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here