በመቀሌ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሰራተኞች የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ

0
322

በመቀሌ ከተማ በኩዊሃ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ዲቢኤል ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የሚሠሩ ሠራተኞች፣ ባሳለፍነው ሐሙስ፣ ነሐሴ 2 ከደሞዛቸው የትራንስፖርት 300 ብር ይቆረጣል መባሉን ተከትሎ፣ ሰልፍ መውጣታቸውን አዲስ ማለዳ ከስፍራው ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

ሠራተኞቹ ሰልፍ በወጡበት ዕለት፣ ባለሥልጣናት ምላሽ ይሰጣችኋል ተብለው ለ4 ሰዓታት ያህል ቢጠብቁም፣ ምላሽ ሊሰጣቸው የመጣ አንድም የመንግሥት አካል ባለመኖሩ መበተናቸውን አስታውቀዋል። ከጎናችሁ ነን የሚል የመንግሥት አካል በማጣታቸው ማዘናቸውንም አውስተዋል። ነሐሴ 1 እና 2 በዚህ ምክንያት ሥራ አለመግባታቸውን ሠራተኞቹ ገልጸዋል።

የኩዊሃ ክፍለ ከተማ አስተዳዳሪ አዳነ ወልደጊዮርጊስ የሠራተኞቹ ጥያቄ አግባብ ቢሆንም፣ የቀረበበት መንገድ ግን ስህተት ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ከመንግሥት መልስ አላገኘንም መባሉ እንዳሳዘናቸ ያስታወቁት ኀላፊው፣ ሠራተኛው ሰልፍ በወጣበት ወቅት ሰብስበው እንዳናገሯቸውም አውስተዋል።

ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንዲት የፋብሪካው ሠራተኛ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ የሠራተኞቹ ደመወዝ ከ800 ብር እስከ 1 ሺሕ 500 ብር ነው። በደሞዙም ኑሯቸውን በአግባቡ መግፋት መቸገራቸውን እና ባለው የኑሮ ውድነት በቀን የሚያገኙት ከ27 ብር እስከ 50 ብር ሕይወታቸውን ባግባቡ ለመምራት አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው ተናግረዋል።

ይህ ባለበት ሁኔታ ድርጅቱ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማቅረብ ከወር ደሞዛችሁ ላይ 300 ብር እቆርጣለሁ ማለቱ ሠራተኛውን እንዳስቆጣው ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፣ 800 ብር የሚከፈለው ሠራተኛ 300 ብር ሲቆረጥበት በ500 ብር ደሞዝ ወሩን እንዲገፋ ተፈርዶበታል ማለት ነው በማለት ተናግረዋል። ይህ ሰብአዊነት ከሚሰማው አካል የማይጠበቅ ነው ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

ሠራተኞቹ ከደሞዛቸው ውጪ የትራንስፖርት የተመደበላቸው 350 ብር መኖሩን የነገሩን አዳነ፣ በርካታ ሠራተኞች ትራንስፖርት ይመደብልን ብለው በመጠየቃቸው፣ ተቋሙ “ትራንስፖርት እመድብላችኋለሁ፤ ነገር ግን የምከፍላችሁን የትራንስፖርት አበል አልከፍልም” አለ እንጂ፣ ከደሞዛቸው አልተቆረጠም፤ በድርጅቱ 800 ብር የሚከፈለው ሠራተኛም የለም፤ ዝቅተኛ ደሞዝ የሚያገኙት 1 ሺሕ 50 ብር ነው ሲሉ፣ የሠራተኛው አቤቱታ እውነትን መሰረት ያላደረገ መሆኑን አሳውቀዋል።

አዳነ ሲገልጹ፣ ድርጅቱ የመንግሥት አይደለም፤ የውጪ ባለሀብት ያቋቋሙት የግል ድርጅት ነው። መንግሥት ጣልቃ ገብቶ “ይህን ያህል ደሞዝ ክፈል ሊል አይችልም” ይሁን እንጂ እሳቸውን ጨምሮ የክፍለ ከተማ አመራሮች ከሠራተኛው ጋር መምከራቸውን ይናገራሉ።

የሠራተኛው ጥያቄ አራት መሆኑን የሚያወሱት አዳነ፣ ከደሞዛቸው ውጪ የሚከፈላቸው የትራንስፖርት አበል 350 ብር፣ የምግብ 250 ብር መኖሩን አስታውቀው፣ ይህ በቂ አለመሆኑን በመረዳት ለምግብ የሚሰጣቸው 250 ብር ቀርቶ፣ በምትኩ በቀላል ዋጋ እዛው ፋብሪካ ውስጥ እንዲዘጋጅላቸው ምክረ ሐሳብ ማቅረባቸውን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ሌሎች ጥቅማ ጥቅማቸውን አስመለክተው ከባለሀብቶቹ ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ባለሀብቶቹ “ገና ግንባታውን ጨርሰን ሙሉ በሙሉ ማምረት ባልጀመርንበትና በኪሳራ እየሠራን ባለንበት ወቅት ደሞዝ አንጨምርም” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ሠራተኛው ተደራጅቶ ጥያቄውን እንዲያቀርብና መብቱን እንዲጠይቅ አድርገናል የሚሉት አዳነ፣ ሠራተኛው በዚህ ደሞዝ የቤት ኪራይ ከፍሎ፣ መሰረታዊ ነገሩን አሟልቶ መኖር እንደማይችል ስለተገነዘብን ቢያንስ ምግባቸው እዛው እንዲዘጋጅና ሌሎቹም ጥያቄዎቻቸው በሒደት እንዲስተካከሉ እየሠራን ነው ብለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 40 ነሐሴ 4 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here