በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዐሥሩም ክፍለ ከተሞች ቁጥራቸው የበዛ የመሥሪያ ቦታ ሕንፃዎችና ሼዶች ተገንብተው ቢያልቁም ለተጠቃሚዎች እንዳልተላለፉ ታወቀ። ተጠቃሚዎች ከአንድ ዓመት በላይ ተደራጅተው ቢጠብቁም የመሥሪያ ቦታ እንሰጣችኋለን ከሚል ተስፋ በስተቀር እስካሁን ምንም ዓይነት መሥሪያ ቦታ እንዳልተቀበሉ አዲስ ማለዳ በተወሰኑ አካባቢዎች ተዘዋውራ ያነጋገረቻቸው ሰዎች ገልፀዋል።
ሰፋፊ መሬት ላይ ከተገነቡት ቀላል ሼዶች ጀምሮ አራት ፎቅ እስካላቸው የመሥሪያ ቦታ ሕንፃዎች ድረስ ለተጠቃሚዎች ያልተላለፉት መሥሪያ ቦታዎች ተደራጅተው በሚጠብቁ ተጠቃሚዎች ላይም ከፍተኛ ለማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮች እንደዳረጋቸው ለማወቅ ተችሏል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ቅሬታ አቅራቢዎች ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት መንግሥት ወጣቱ በሥራ ፈጠራ ላይ እንዲሰማራ እና ራሱን ጠቅሞ አገሩንም እንዲጠቅም በአንድ በኩል እያበረታታ በሌላኛው በኩል ደግሞ የምንሠራበትን ቦታ ሳያከፋፍለን በማዘግየት እያጉላላን ነው በማለት ቅሬታቸውን አስተጋብተዋል።
የቀረበውን ቅሬታ በሚመለከት የፌደራል ከተሞች ሥራ ፈጠራ እና ምግብ ዋስትና ማረጋገጫ ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገረው፤ ችግሩ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በኹሉም የኢትዮጵያ ክልሎች እና ከተሞች ላይ የሚታይ ሲሆን ተገንብተው ለተጠቃሚዎች የማይተላለፉበት ምክንያም ተመሳሳይ እንደሆነ ተናግሯል። ኤጀንሲው እንደምክንያት ያስቀመጣቸውም የመሰረተ ልማት አለመሟላትን በግንባር ቀደምነት ይጠቅሱታል ። ኤጀንሲው ይህን ይበል እንጂ፤ ሌሎች ተጨማሪ ቅሬታ አቅራቢዎች ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት ደግሞ በአምራች ዘርፍ ተደራጅተው ባለ አራት ፎቅ ሕንፃ እንደተሰጣቸው እና ለመብራት ‘ትራንፎርመር‘ እና ‘ስሪ ፌዝ ቆጣሪ’ ለማስገባት ከ7 መቶ ሺሕ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ድረስ ቢከፍሉም ከአንድ ዓመት በላይ ምላሽ ሳያገኙ መቅረታቸውን አስታውቀዋል።
የፌደራል ከተሞች ሥራ ፈጠራ እና ምግብ ዋስትና ማረጋገጫ ኤጀንሲ ሕዝብ ግንኙነት አቦዘነች ነጋሽ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፤ ይህን ሥራ በዋናነት የሚመለከተው ክልሎችንና የከተማ አስተዳደሮችን ሲሆን በጀቱም ከክልሎች የሚመደብ እንደሆነ ጠቁመው ኤጀንሲው ግን በበላይነት እንደሚቆጣጠር ገልፀው የውሃ አገልግሎት፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ችግር እንዲሁም የኀይል እጥረት ለርክክቡ መዘግየት ዋነኛ ችግር ነው ሲሉ ተናግረዋል። ኤጀንሲው እስካሁን ሲሠራ ከነበረው በላቀ ሁኔታ የሼዶችንና የመሥሪያ ቦታ ሕንፃዎችን በተገቢው ሁኔታ ለተጠቃሚው ተሸጋግረዋል ወይ የሚለውን በጥንቃቄ እንደሚሠሩም ተያይዞ ተገልጿል።
ከዚህ በተቃራኒ ግን ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በቦሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ቅሬታ አቅራቢ እንደሚናገሩት ተደራጅተው ወደ ክፍለ ከተማ እና ወረዳዎች ጉዳያቸውን ለማቅረብ በሚሔዱበት ጊዜ በየጊዜው የተለያዩ የሥራ ኀላፊዎች መቀያየር ምክንያት የተፈለገውን ለውጥ ማምጣት ካለመቻሉም በላይ ችግራቸውንም ሊፈታ የሚችል የሥራ ኀላፊ እንዳጡ ተናግረዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 40 ነሐሴ 4 2011



