ኒው ዮርክ ካፌ ሶስት ሚሊዮን ብር ተፈረደበት

0
633
  • ትምህርት ቤቱ ባወጣው አዲስ ጨረታ የካፍቴሪያ ቦታውን ካልዲስ ካፌ ተከራይቶታል

ላለፉት ሦስት ዓመታት በክስ ሒደት ላይ የቆየው የአሳይ የሕዝብ ትምህርት ቤት እና የኒው ዮርክ ካፌ ክርክር በሐምሌ ወር 2011 የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አምስተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ለአሳይ ትምህርት ቤት በተሰጠው ፍርድ ተጠናቀቀ።

ካፌውን የሚያስተዳድረው ኮስሞ ትሬዲንግ ከአሳይ ትምህርት ቤት ጋር የፈፀመው የኪራይ ውል በቀደሞ ዋጋው እንዲቀጥል የቀረበውም ጥያቄ ውድቅ እንዲሆን ተደርጓል። ካፍቴርያውም ክርክሩ በቆየበት ግዜ ለተከታታይ 15 ወራት በሥራ ላይ ነበር። ይህንንም አስመልክቶ ትምህርት ቤቱ ሊያገኝ የሚገባውን የ15 ወራት ያልተከፈለ ኹለት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር እንዲከፍል ፍርድ ቤቱ ወስኗል።

ፍርድ ቤቱ የኒው ዮርክ ካፌን አቤቱታ የእድሳት ስራው የተከናወነው ስራን ለማሳለጥ ሲባል በመሆኑ እፎይታ አያሰጥም ሲል ወስኗል።
ኮስሞም ኒዮርክ ካፌ ያረፈበትን ጨምሮ በአሳይ ትምህርት ቤት ባለቤትነት ሥር ያሉ ሌሎች ስድስት ሱቆችን ለዓመታት በኪራይ ውል ተቀብሎ ሲያስተዳድር የቆየ ሲሆን፥ በ2006 መጨረሻ ላይ በተገባው የመጨረሻ ውል ላይ ነበር ክርክር የተነሳው። በወር በ175 ሺሕ ብር ለመክፈል የተዋዋለው ኒው ዮርክ ካፌ በአፍሪካ ጎዳና ላይ በተደረገው የመንገድ ግንባታ ምክንያት እና በካፍቴሪያው ተነስቶ በነበረው እሳት አማካኝነት መሥራት የሚገባኝን ባለመሥራቴ ውሉ ለ26 ወራት ይራዘምልኝ ሲል ሲከራከር መቆየቱ ይታወሳል።

ካፌው አክሎም በተከራየው ዓመት መጠቀም እንዳልቻለ እና በተነሳው እሳት ምክንያት በሚሊዮኖችን የሚቆጠር ገንዘብ ለእድሳት ማውጣቱን ለመከራከሪያ ሲያነሳ ቆይቷል። ትምህርት ቤቱ በበኩሉ የእሳቱ መነሻ ካፌው እንደመሆኑ ይህንን ለማስተካከል የወጡ ወጪዎች ውሉን ለማራዘም ምክንያት እንደማይሆኑ እና የአፍሪካ ጎዳና ማስፋፊያ በሚገነባበት ወቅትም ኒው ዮርክ ለቆ ለመሔድ ይችል እንደበር ገልጾ ሲከራከር ቆይቷል።

በዋናነት የተለያዩ መዋቢያዎችን እና ሽቶ በማስመጣት ላይ የተሠማራው ኮስሞ የኪ ራይ ውሉን ማቋረጥ አይገባኝም በሚል በጥር ወር 2009 በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመሠረተው ክስም ተጠናቆ ትምህርት ቤቱ ባወጣው አዲስ ጨረታ የካፍቴሪያ ቦታውን ለካልዲስ ካፌ እንዳከራየው የትምህርት ቤቱ ባልደረባ ወንድሙ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አሳይ የሕዝብ የመጀመሪያ እና የኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ1956 የተቋቋመ ትምህርት ቤት ሲሆን በአዲስ አበባ ውስጥም ብቸኛው የሕዝብ ትምህርት ቤት እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ። ትምህርት ቤቱ ወጪዎቹን በቋሚነት የሚሸፍን ገቢ ለማግኘት በማሰብ በ2004 የንግድ ሥራውን ለማስጀመር በሕዝብ ተገንብቶ ባቋቋመው ገንዘብ ሕንፃዎቹን ገንብቶ እያከራየ ይገኛል።

ቅጽ 1 ቁጥር 41 ነሐሴ 11 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here