ከሴቶች ብቻ ከ 4ቢሊዮን ብር በላይ ቁጠባ ተሰበሰበ

0
695
  • 579 ሺሕ የሚሆኑ ሴቶችም ብድር አግኝተዋል

ባሳለፍነው 2011 የበጀት ዓመት ስድስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን በጥቃቅን እና አነስተኛ የተደራጁ ሴቶች አራት ነጥብ ኹለት ቢሊዮን ብር ቆጥበዋል ሲል የሴቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር አስታወቀ። በተጨማሪም 579 ሺሕ ለሚሆኑ ሴቶች ሦስት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር የሚሆን በረጅምና በአጭር ጊዜ የሚከፈል ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ ብድር አግኝተዋል።

ተቋሙ የሴቶችን የቁጠባ ባሕል በማዳበር እና በብድር አጠቃቀም ዙሪያ በተሠራው የግንዛቤ ማስጨበጫ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም ማጎልበት መቻሉን የተቋሙ የኮሚንኬሽን ባለሙያ መላኩ ባዩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ከተባበሩት መንግሥታት የሴቶች ጉዳይ (UN Women) ጋር በመተባበርም የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማጎልበት የኹለት ዓመት ፕሮግራም በግማሽ ሚሊዮን ብር መተግበሩንም ገልጸዋል።

የሴቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር ከፌደራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በተለያዩ ዘርፎች በጥቃቅን እና አነስተኛ ለተሰማሩ ሴቶች፣ የንግድ ባንክ የቁጠባ ደብተር በማዘጋጀት እንዲቆጥቡ መደረጉን ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት መላኩ፣ በቆጠቡት ልክ ገንዘብ በማበደርና፣ በግብርና እና እንስሳት እርባታ ላይ ለተሰማሩት መሬት እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከአውሮፓ ኅብረት በተገኘ የስድስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍም በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ተመርቀው ሥራ ያላገኙ ሴቶችን፣ በተለያዩ የሙያ መስኮች ሠልጥነው በገቢ ማስገኛ መስኮች ላይ እንዲሳተፉ መደረጉ ለውጥ ማምጣት ችሏል ሲል የሚኒስቴሩ ዓመታዊ ሪፖርት ያሳያል። በአራት ክልሎች እና በስድስት ከተሞች ላይ በድምሩ ሦስት ሺሕ ሴቶች እያንዳንዳቸው በሚያቀርቡት የቢዝነስ ዕቅድ መሰረት በ20 ሺሕ ብር መነሻ በመመደብ ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ከቴክኒክና ሙያ ክህሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በተደረገ ዉል መሰረት ሥልጠናውን እንዲወስዱ የተደረገ ሲሆን፣ የመረጃ ማጣራትና የክትትል ሥራዎች በመሥራት በአምቦ፣ ጅማ፣ አሶሳ፣ ዲላ እና ጋምቤላ ከተሞች ለኹለት ሺሕ አራት መቶ ሴቶች 48 ሚሊዮን ብር እንዲለቀቅ ተደርጓል ሲሉ መላኩ ተናግረዋል።

በሙከራ ደረጃ ኦሮሚያ እና አፋር ክልሎች ላይ ኹለት ሺሕ ሴቶችን በማኅበራት በማደራጀት፤ በማሰልጠን እና መነሻ ብር በማቅረብ አዋጭ በሆኑ የሥራ ዘርፎች እንዲሰማሩ በማድረግ፣ ሴቶችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች ተሰርቷል ሲል ሚኒሰቴሩ ለአዲስ ማለዳ የላከው የአፈጻጸም ሪፖርት ያሳያል።

ቅጽ 1 ቁጥር 41 ነሐሴ 11 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here