ከዚህ ቀደም የፍትህ ሳምንት በመባል ሲከበር የነበረው እና በተያዘው አመት የተራዘመው የፍትህ ወር ጳግሜ 5 ቀን በሚሊኒየም አዳራሽ በሚካሄድ ዝግጅት ይጠናቀቃል ሲል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ፡፡
በእለቱ ለፍትህ ስርአት መጠናከር አስተዋፅኦ ላበረከቱ ምሁራን እውቅና በመስጠትና በባለሞያዎች በሚደረጉ አነቃቂ ንግግሮች የሚከበር ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስቴሩም ይገኙበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ የጠበቆች ማህበር እና ፌደራል ፖሊስ በጋራ የሚያከብት ይህ ወር ‹‹እኔ የህግ ተገዥ ነኝ በሚል መርህ ›› ሲያከብሩት ቆይቷል፡፡
ከዚህ አመት ጀምሮ በቋሚነት በየአመቱ ጳጉሜ 5 ቀን የፍትህ ቀን ሆኖ የሚከበር ሲሆን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ብርሃኑ ፀጋዬ እንደሚመራም የጠቅላይ አቃቤ ህግ የኮሚኒኬሽን ሃላፊ ዝናቡ ቱኑ ገልፀዋል፡፡
በእለቱም የጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጽህፈት ቤት ባዘጋጀው ጳጉሜን በመደመር በሚል በተዘጋጀው የስድስት ቀን መርሃ ግብር ላይ የፍትህ ቀን ተብሎ የተሰየመ ሲሆን ከፍትህ ወር መስዝጊያ ጋር አብሮ እንደሚከበር ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከጠቅላይ አቃቤ ህግ ውጪም የተለያዩ የመንግስት አካላት ስድስቱን ቀናት የተከፋፈሉ ሲሆን ጷጉሜ 1 የብልጽግና ቀን በሚል የጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት ይመራዋል፡፡ ጷጉሜ 2 የሰላም ቀን በሚል የሰላም ሚንስትር ሙፈሪያት ካሚል፣ ጷጉሜ 3 የሀገራዊ ኩራት ቀን በሚል የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ፣ ጷጉሜ 4 የዴሞክራሲ ቀን በሚል የትራንስፖርት ሚንስትር ዳግማዊት ሞገስ ይመሩታልም ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ጷጉሜ 6 የብሄራዊ አንድነት ቀን በሚል ስያሜ በጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት የሚመራ ይሆናል፡፡
ቅጽ 1 ቁጥር 42 ነሐሴ 18 2011



