ኃይሌ ገብረሥላሴ ፋውንዴሽን ተቋቋመ

0
525

በረጅም ርቀት ሩጫ የኦሎምፒክ ባለድል የሆኑት አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ (ሻለቃ) ከባለቤታቸው ጋር በመሆን በትምህርት ላይ የሚሠራ ፋውንዴሽን በስማቸው አቋቋሙ።

በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ላይ የተሰማራው ኃይሌ፤ በፋውንዴሽኑ ከመዋዕለ ሕጻናት እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ላሉ የትምህርት ተቋማት የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ ላይ እንደሚያተኩር ገልጾአል። አያይዘው በአውሮፓ የሚገኙ የትምህርት ተቋማትም በፋውንዴሽኑ አማካኝነት እርዳታ ለማቅረብ ጥያቄ እንዳቀረቡላቸው ተናግረዋል።

ለቀጣዩ ትውልድ የአስተሳሳብ ግንባታ ያግዛል በማለት ፋውንዴሽኑን እንዳቋቋሙ የሚናገረው ኃይሌ፤ ነፃ የትምህርት እድል በመስጠት እንዲሁም ከተለያዩ የወጪ ሀገራት የሚመጡ የመማርያ መጽሐፍትና ኮምፕዩተሮችን በመለገስ፤ ማዕከሉ የትምህርት ጥራትን ለማስፋፋት የሚያስችል ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ ዓላማ አለን ብሏል።

የፋውንዴሽኑ ቦርድ የአትሌቱን ባለቤት ዓለም ጥላሁንን ጨምሮ የኃይሌ ሪዞርት ዳይሬክተር መልካሙ መኮንን፣ የማራቶን ሞተር ሥራ አስኪያጅ መልካሙ አሰፋ እና ሌሎች ሦስት አባላትን አካቷል።

ፈውንዴሽኑ እውቅና ከማግኘቱ ቀደም ብሎ አራት ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት በአትሌቱ የተገነባው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከሰቆጣ ከተማ 55ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ጣግቢ ወረዳ ላይ ባሳለፍነው አርብ ነሀሴ 17/2011 መመረቁ ይታወሳል። በእለቱም አንድ ግለሰብ ከ5 አስከ 8ኛ ክፍል ለሚሆኑ ተማሪዎች የ8 ሺህ መጽሐፍት ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፤ የፋውንዴሽኑ መሥራች ኃይሌ በእለቱ ለጌዲኦ ተፈናቃዮች ለምግብ እና አልባሳት የሚውል 1.2 ሚሊዮን ብር በፋውንዴሽኑ ስም ድጋፍ ማድረጋቸውን ጨምረው ጠቅሰዋል።

የፋውንዴሽኑ መሥራች አትሌት ኃይሌ ከዚህ በፊት በተለያዩ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ውስጥ በአምባሳደርነት እንዳገለገለ አስታውሶ፤ በባህር ዳር እና በአሰላ ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች አስገንብተው መስጠቱን ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።

‹‹እነዚህ ትምህርት ቤቶች ከመዋዕለ ህፃናት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ግን ድጋፍ የምናደርገው ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎችም መሆን አለበት በሚል ነው ፋውንዴሽኑን ያቋቋምነው›› ሲልም አስታውቆአል።

የበጎ አድራጎት ማሕበራት ኤጀንሲ አዋጅ ከተሻሻለ በኋላ አራት መቶ አዳዲስ በጎ አድራጎት ድርጅቶች መመዝባቸውን የገለጹት የኤጀንሲው ምክትለ ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው፤ በተመሳሳይ የቀድሞው አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ በልጃቸው ስም ዲቦራ የበጎ አድራጎት ድርጅት መመሥረታቸውንና በኤጀንሲው መመዝገቡን ገልጸዋል። ታዋቂና ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች እንዲህ ባሉ ተግባራት መሰማራቸው ይበል የሚያሰኝ መሆኑንም ነው ምክትል ዳይሬክተሩ አያይዘው ያነሱት።

ቅጽ 1 ቁጥር 42 ነሐሴ 18 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here