አምስት መቶ ቤተሰቦች የኢትዮ- ጅቡቲ የባቡር መስመርን ለመጠበቅ ሊሰማሩ ነው

0
2117
  • በ15 ኪሎ ሜትር ውስጥ 25 ሺሕ ማያያዣ ብሎኖች ተፈተው ተወስደዋል

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር ሐዲድ ላይ እየተበራከተ የመጣውን የስርቆት ወንጀል ለመከላከል ይረዳል የተባለውን አዲስ የጥበቃ ስርዓት አምስት መቶ ቤተሰቦችን በየአንድ ኪሎሜትር ርቀት በሐዲዱ ዙሪያ ጥበቃ እንዲያደርጉ ማቀዱን የባቡር ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

ድርጅቱ የባቡር ሐዲዱ በሚያቋርጥባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ማኅበረሰቦችን በማወያየት ከሰበታ እስከ ዶራሌ ጣቢያ ድረስ የተዘረጋው 751 ኪሎ ሜትር ውስጥ በኢትዮጵያ ያለውን አምስት መቶ ኪሎ ሜትር ለሚጠብቁት የአካባቢው ማኅበረሰብ መንግሥት መሰረተ ልማትን በማቅረብ ድጋፍ እንደሚያደርገ ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ምክትል ዳይሬክተር የኑስ ናስር ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ድርጅቱ የባቡር ሐዲዱን በሚመለከት ሲደረግ የነበረው ጥበቃ ለውጥ ካለማምጣቱም በላይ በጥበቃ ሥራ ላይ ለተሰማሩ ግለሰቦችም በሕይወታቸው ላይ አደጋ እየተጋረጠ እንዳለ ጠቁመዋል። አያይዘውም የባቡር ሐዲዱ በበቂ እና በተገቢው ሁኔታ ካለመጠበቁ ተነሳ ዐሥራ አምስት ኪሎ ሜትር የሚሆን ሐዲድ ማያያዣ ብሎኖች ተፈተው መወሰዳቸውን ተቁመዋል።

ማያያዣ ብሎኖች በየስልሳ ሴንቲ ሜትር ልዩነት የሚገኙ እንደነበሩ የተጠቀሰ ሲሆን በ15 ኪሎ ሜትር ውስጥ 25 ሺሕ ማያያዣ ብሎኖች ተፈተው መወሰዳቸው እና በባቡር አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። ጅቡቲ ድረስ የሚዘልቀውን የባቡር መስመር በጠቅላላ ግራና ቀኝ ማጠር እጅግ ከባድ በመሆኑ በቀደመው ጊዜ ከነበረው ምድር ባቡር አሠራር ልምድ በመቅሰም አዲሱ አሠራር ዓይነተኛ አማራጭ ነው ሲሉም ኀላፊው ገልፀዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች የባቡር እንቅስቃሴው በአንዳንድ ግለሰቦች ዕገታ ተፈፅሞበት እንደነበርና የሚመለከተው አካል ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የባቡሩን ግንባታ ያከናወነው እና አሁንም በማስተዳደር ላይ የሚገኘው የቻይና የባቡር ሐዲድ ግንባታ ድርጅት (ሲአርኢሲሲ) እና ቻይና ሲቪል ምሕንድስና ግንባታ ኩባንያ (ሲሲኢሲሲ) ዋና ሥራ አስኪያጅ ዚሀንግ ዜንሃይ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል። አያይዘውም የባቡር መስመሩ በዋናነት ከእንስሳትና ከሰው እንቅስቃሴ የፀዳ መሆን እንዳለበት ቢቀመጥም እንደታሰበው ባለመሆኑ ባቡሩ በሚፈለገው የፍጥነት መጠን እየተንቀሳቀሰ እንዳልሆነ እና ኩባንያቸው መንግሥት መፍትሔ ሊያበጅ ይገባል ብሎ እንደሚያምን ተናግረዋል።

ኹለቱ የቻይና ግዙፍ የባቡር ግንባታ ድርጅቶች በ2010 ላይ የሽርክና ውል አስረው የኢትዮ ጅቡቲ የምድር ባቡርን ማስተዳደር መጀመራቸው የሚታወስ ሲሆን የውሉ የቆይታ ጊዜም ለስድስት ዓመታትን እንደሚቆይ የሚታወስ ነው።

አዲስ ማለዳ ከቻይናው ኩባንያ ያገኘችው መረጃ እንደሚያመለክተው በ2010 አንድ መቶ ኻያ ስምንት ሺሕ 722 መንገደኞች እና ጭነቶች በኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር መጓጓዛቸው እና ከዚህም 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ከጭነት 30 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱም ታውቋል።

ይህ አኀዝ በ2011 በከፍተኛ መጠን በማሽቆልቆል ከመንገደኞች 537 ሺሕ 4 መቶ የአሜሪካን ዶላር ብቻ መሰብሰቡን እንደተቻለና ከጭነትም 19 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ብቻ እንደተሰበሰበ የታወቀ ሲሆን ይህም መንግሥት ለምድር ባቡር የደኅንነት ሥጋቶች መፍትሔ ካለመስጠቱ ጋር የተያያዘ ነው ሲሉ የሲሲኢሲሲ እና ሲአርሲሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 43 ነሐሴ 25 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here