በባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ የ10 ሰው እና የ10 ዝሆኖች ህይወት አለፈ

0
907

በባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ በህገ-ወጥ እርሻና ሰፈራ መስፋፋት እንዲሁም ህገ ወጥ አደን ሳቢያ የተቆጡ ዝሆኖች በ2011 14 ሰዎችን ያጠቁ ሲሆን ስድስቱ ወዲያውኑ ህይወታቸው አልፏል። ሌሎች አራት ሰዎችም በተለያየ ጊዜ በደረሰባቸው ጥቃት ህይወታቸው ሲያልፍ በተመሳሳይም አራት ግለሰቦች ከባድ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል።

አስር ዝሆኖች በአንድ ዓመት ውስጥ ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ሦስቱ ግልገሎች መሆናቸውን የመጠለያው ኃላፊ አደም ሞሐመድ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ሰባቱ አዋቂ ዝሆኖችም በህገወጥ አደን ምክንያት ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፣ ግልገሎቹ በአካባቢው በሰፈሩት ሰዎች በመረበሻቸውና ለጭንቀት በመዳረጋቸው መሞታቸውን ገልጸዋል።

አደም ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት የዝሆን መኖሪያ በሆኑ አካባቢዎች ላይ እየተስፋፋ የመጣው የእርሻ ሥራም ዝሆኖቹ መኖሪያቸውን ለመከላከል ሲሉ ጥቃት እንዲጀምሩ አድርጓል።

በመጠለያው ያለውን ህገ ወጥ ሰፈራ፣ እርሻና አደን ለመቆጣጠር ጥረት ቢደረግም፣ በበጀት ዓመቱ በመጠለያው ውስጥ የሚፈጸሙ ህገወጥ ድርጊቶችን ከመከላከል አንጻር አፈጻጸሙ ከ30 በመቶ በታች መሆኑን ያስታወቀው የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ነው።

ከሶማሌ ክልል በኩል የሚገቡ ህገወጥ አዳኞችም ለዝሆኖቹ መመናመን የበኩላቸውን ድርሻ ተወጥተዋል ይላሉ ኃላፊው።የባቢሌ መጠለያ ዓላማውን ለማሳካት የያዘው ስትራቴጂ ደካማ በመሆኑና መጠለያው ትኩረት አጥቶ በመሰንበቱ፣ በ2010 አስራ አንድ ዝሆኖች፣ በ2011 ደግሞ 10 ዝሆኖች እንዲሞቱ ምክንያት መሆኑንም ይናገራሉ።

‹‹በ30 ዓመት ውስጥ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ዝሆኖች ውስጥ 90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሞተዋል፣ ወደ ጎረቤት አገር ተሰድደዋል፣ የደረሱበት አይታወቅም›› ሲሉ የመጠለያው ኃላፊ አክለው ገልጸዋል።

ባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ከአዲስ አበባ በስተምስራቅ 550 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ይህ መጠለያ 6982 ካሬ-ሜትር የቆዳ ስፋት ያለው ሲሆን፣ ከጠቅላላ ስፋቱም ውስጥ 72 ከመቶ ያህሉ በሱማሌ ክልል ስር ሲካለል፤ ቀሪው 23 ከመቶ ያህሉ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ስር ይገኛል።

የአካባቢው የኦሮሚያ ብሔር ተወላጆች ‹‹ወረ-ሃርባ›› (ባለዝሆኖቹ) በማለት የሚጠሩትና በፌዴራል የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ስር የሚተዳደረው የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ፣ በዓፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ-መንግሥት በ1962 ነበር የተመሰረተው።

የምሥረታውም ዋነኛ ዓላማ የነበረው በምሥራቅ አፍሪካ ብቻ የሚገኙትን “ሎክሶዳንታ አፍሪካና ኦርሊያንሲ” የተባሉትን ንዑስ የዝሆን ዝርያ ለማልማትና ለመጠበቅ መሆኑን ያስታወቁት አደም፣ በአሁኑ ጊዜ መጠለያው ከ30 በላይ ጡት አጥቢ የዱር እንስሳት፣ ከ250 በላይ የአዕዋፍ ዝርያዎች፣ 3 መቶ ያህል የዕፅዋት ዝርያዎች የሚገኙበት መሆኑን ተናግረዋል።

ከምድረ ገፅ የመጥፋት አደጋ ላይ ያለው ”የሳልቫዶሪ ዘረ-መል” (Serinus xantholaema) ወፍ እና ባለጥቁር ጎፈር አንበሳ በዚህ መጠለያ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል።

ቅጽ 1 ቁጥር 43 ነሐሴ 25 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here