የፖለቲካ ልዩነታችን ለውጪ ሃይሎች እንዳያስከነዳን

0
377

የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ገዱ አንዳርጋቸው ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ ግብፅ ካመሩበት ሃምሌ 19/2011 በኋላ የግብፁ አቻቸው ኢትዮጵያን እና ሱዳንን በአንድ ቀን ርቀት ጎብኝተው ነበር። ሞሃመድ አብደል. ላቲ ሁለቱን አገራት የጎበኙበት ምክኒያትም ከተለመደው ውጪ አንድ አዲስ ጥናት በመያዝ በህዳሴው ግድብ ላይ ለማግባባት ነበር፡፡

የግብጹ የውሃና የመስኖና ሚኒስትር ለኢትዮጵያው አቻቸው ኢንጂነር ስለሺ የሰጡት ይህ የጥናት ሰነድ አዲስ ማለዳ አግኝታ በዝርዝር መመልከት ባትችልም፣ ከኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አባላት መካከል ባገኘችው መረጃ ‹‹የግድቡን የማመንጨት መጠን የሚቀንስ ከመሆኑ በላይ ግብጽ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የማይጠበቅ እና ከቅኝ ግዛት የማይተናነስ ጥያቄ ይዛ መጥታለች›› ሲሉ ይናገራሉ።

ባለሞያው እንደሚሉት የግብፅ ባለስልጣኖች ኢትዮጵያ በቋፍ ላይ ያለች ሀገር ሆና ታይታቸዋለች፤ ይህም እንዲህ አይነት ‹‹የቀኝ ግዛት የሚመስል›› ሰነድ ይዘው እንዲመጡ አድርጓል።

የግድቡ የውሃ አሞላል እና አለቃቀቅ ጉዳይም የሶስቱ አገራት የውሃ ሚኒስቴሮች በአዲስ አበባ ለመጨረሻ ግዜ ባደረጉት ስብሰባ ተደራድረው በቃል ከተስማሙ በኋላ፣ ቃለ ጉባኤውን ከመፈረማቸው በፊት የግብፁ የውሃ ሚኒስቴር አገሬን ላማክር በማለታቸው ሳይፈረም ቀርቷል፡፡ በኋላም ሱዳን ባጋጠማት ህዝባዊ አመጽ እና የመሪ ለውጥ ድርድሩ ሳይደረግ ለወራት እንዲቆይ ሆኗል።

ግብፅ አዲስ ጥናት ይዛ የመምጣቷ ምስጢር፣ የሱዳን የውስጥ አመፅ እና ኢትዮጵያውያንም ያለንበትን ሁኔታ በመመልከት ይመስላል፡፡ ላለፉት ተከታታይ ዓመታት ኢትዮጵያ የነበረችበት የፖለቲካ ለውጥ ሳይቋጭ በተደጋጋሚ በተነሱ ብሄር ተኮር ግጭቶች ሚሊዮኖች ሲፈናቀሉ እና ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ኢትዮጵያዊያን በገዛ ወገኖቻቸው መገደላቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡

አገሪቱ ያለችበት የፀጥታ ሁኔታ በአማራ ክልል እና በአዲስ አበባ በሰኔ ወር አጋማሽ በተከሰተ የአመራሮች ግድያ ጥግ በመርገጥ፣ ዜጎችን ከማሸበር ባለፈም በመላው ዓለም የፖለቲካ ትኩሳታችን መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡

እነዚህን የውስጥ ችግሮች በፍጥነት በመፍታት ጠንካራ አንድነትን ማምጣት ካልተቻለ፣ ቢሊዮኖች የፈሰሱበት እና የሃገሪቱን ኢኮኖሚ አንድ እርምጃ ያራምዳል የተባለውን ይህ ግድብ ማገባደድ የማይታሰብ መሆኑ እሙን ነው። ይህንንም ከግምት በማስገባት፣ ያጋጠሙ ችግሮችን በሰከነ መልኩ መፍታት ካልተቻለ የግድብ ብቻ ሳይሆን የሉአላዊነት ጉዳይ መሆኑ አይቀርም፡፡

የ1959ኙ የሱዳን እና የግብፅ ስምምነት በ1929 የሱዳን ቅኝ ገዢ የነበረቸው እንግሊዝ እና ግብፅ የፈረሙትን ስምምነት የሚያፀና ስምምነት ነበር፡፡ በዚህ ስምምነትም ግብፅ ከናይል ወንዝ በየአመቱ የምታገኘውን 48 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ ወደ 55.5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ የሚያሳድግ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ሱዳንም በየአመቱ ከምታገከኘው አራት ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ ወደ 18.5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ከፍ በማድረግ የላይኛውን ተፋሰስ ሀገራት በማግለል ለሁለቱ ሃገራት የድርሻ ማረጋጋጫ የተሰጠበት ነበር፡፡

እንደ ዋዜማ ራዲዮ ዘገባ፣ ግብፅ የህዳሴው ግድብ ሲገነባ በየዓመቱ ልታገኝ ይገባል ከተባለው አምስት ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ በ35 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ከፍ በማድረግ 40 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ ላገኝ ይገባኛል የሚል አዲስ ሀሳብ ይዛ ብቅ ማለቷን የ1959ኙን የቅኝ ግዛት ውል ለመጫን በማሰብ የቀረበ ሀሳብ መሆኑን ባለሙያዎች ይሞግታሉ።

ሱዳን እና ኢትዮጵያ በውስጥ ችግሮቻቸው በተናጡበት እና በደከሙበት ግዜ ላይ አዲስ የድርድር መነሻ ሃሳብ ይዛ ብቅ ያለቸው ግብፅ፣ ለሱዳናዊያን ያቀረበቸው ከቀድሞ የድርድር ግዜአት መጠኑ ከፍ ያለው ውሃም ሱዳናዊያንን ከማማለል ይልቅ የውስጥ የቤት ስራቸውን በወቅቱ እንዲያጠናቅቁም ያሳሰበ ሆኗል ሲሉ ምንጫችን አክለዋል፡፡

የግብፅ መንግስት የኢትዮጵያ እና የሱዳንን ወቅታዊ ፖለቲካ ሁኔታ ተጠቅሞ በአባይ ግድብ ላይ ያለውን ድርድር እንዳዲስ ለመጀመር እና በግድቡ የሃይል ማመንጨት አቅም ላይም ባሳየው አዲስ አቋም ምክኒያትም ሁለቱ አገራት ፊታቸውን አዙረውባታል እስካሁንም መልስ አልሰጡም ሲሉ ምንጫችን ይናገራሉ፡፡
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ገዱ አንዳርጋቸው በግብፅ በነበራቸው ቆይታ ይህን ሃሳብ አንፀባርቀዋል የተባለ ሲሆን ‹‹ካቆምንበት ነው የምንቀጥለው›› የሚል ምላሽ ሰጥተው መመለሳቸውን የአዲስ ማለዳ ምንጭ ገልጸዋል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ በኩል ያሉት ተደራዳሪዎችም፣ ከባለሞያ እስከ ከፍተኛ የመንግስት ባለስጣኖች፣ ከፍተኛ ብስጭት ውስጥ ገብተዋል›› ያሉት ምንጫችን ‹‹ይዘውት ስለመጡት ሰነድ ዝርዝር መናገር ባልችልም ባጭሩ ቅኝ እንግዛችሁ ከማለት አይተናነስም፣ በዚህ ዘመን ዘመን ይደረጋል ተብሎ የማይጠበቅ ነገር ነው ያደረጉት›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የሱዳን ሽግግር መንግስት ያልተረጋጋበትን ግዜ በመጠበቅ የቀረበ ሃሳብ ነው በማለት በሱዳናዊያን ባለስልጣኖች ዘንድም ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል ሲሉ ምንጫችን አክለው ገልፀዋል፡፡ የሃይል መጠኑ ግብፅ በምትፈልገው ልክ ለማድረግ እና በግድቡ ላይም የባለቤትነት ስሜት በማሳየት ሰነዱ ቁጣን አጭሯል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ግድቡን በተመለከተ ከህዝቡ የወር ደመወዝ ሳይቀር ገንዘብ የሚሰበስብ ሲሆን፣ ህዝቡ የግድቡ ባለቤት ነው በማለት በተደጋጋሚ ሲገልፅ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ታዲያ እንዲህ ባለ የግድቡን ህልውና አደጋ ውስጥ በሚከትበት ወቅት ለህዝቡ አስፈላጊውን እና በቂ መረጃ መስጠት እንደሚኖርበት አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች፡፡

የድርድር ሂደቶቹም ከፖለቲካ ሹመኞች ይልቅ በባለሞያዎች የሚመራ ድርድር ማድረግ አማራጭ የለውም ብላ ጋዜጣችን ታምናለች፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 43 ነሐሴ 25 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here