ገበሬዎች ሰፋፊ እርሻ አልሚ የሚሆኑበት ህግ ሊዘጋጅ ነው

0
1207

መንግሥት በትናንሽ መሬት ላይ የሚያርሱ ገበሬዎች ሰፋፊ እርሻዎች ከመንግሥት በሊዝ ወስደው ባለድርሻ የሚሆኑበት አዲስ ሕግ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት መወሰኑን ሃገር በቀል ኢኮኖሚ አጀንዳ ይፋ በሆነበት ወቅት አስታወቀ።

ከ 20 ዓመታት ጀምሮ ሲሠራበት በነበረው ግብርና መር የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሰረት፣ በትንንሽ የእረሻ መሬቶች ላይ የማምረት አሠራር የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አለማስቻሉን ተከትሎ ይፋ የሆነው ማዕቀፉ፣ ገበሬዎች ከመንግሥት ብድር ወስደው ሰፋፊ እርሻዎችን ማስተዳደር የሚችሉበትን መንገድ እንደሚያመቻች ተነግሯል።
‹‹ገበሬዎች ሰፋፊ እርሻዎች ይዘው የሚሰሩበት የሕግ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅ የተያዘው አቅጣጫ ከተተገበረ በኋላ የግብርናው ዘርፍ ላይ ትልቅ ለውጥ ሊመጣ ይችላል›› ሲሉ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ እና የኢኮኖሚ ሪፎርሙ አስተባባሪ እዮብ ተካልኝ በሸራተን አዲስ ሆቴል አዲሱን ኢኮኖሚ አጀንዳ ይፋ ባደረጉበት ወቅት ተናግረዋል።

በተለይም ከዚህ ቀደም በልማት ባንክ በተፈቀዱ ብድሮች የተቋቋሙ ሰፋፊ እርሻዎች የታሰበላቸውን ውጤት ባለማምጣታቸው አዲሱ ሕግ ማዕቀፍ ማስፈለጉን ኢዮብ ተናግረዋል።

ከአምስት ዓመታት በፊት መንግሥት ለግል ዘርፍ አልሚዎች በርካታ ብድሮች መስጠቱን ተከትሎ በርካታ ኢንቨስተሮች መሬት ተከራይተው ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር ቢወስዱም ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ሳይመለስ ቀርቷል።

በተጨማሪም ከ36 በላይ የግል አልሚዎች ብድር ከወሰዱ በኋላ የገቡበት አልታወቀም ሲል በፓርላማ የበጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ አስታውቆ ነበር። በኢትዮጵያ ከ5000 በላይ ሰፋፊ እርሻዎችን የያዙ የግል አልሚዎች ያሉ ሲሆን በአጠቃላይ በአገሪቷ በእርሻ ከተሸፈነው 13 ሚሊዮን ሄክታር ውስጥ አምስት በመቶውን ብቻ ይዘዋል። በተያያዘ 14 ሚሊዮን በላይ ትናንሽ እርሻዎች ላይ የሚሠሩ ገበሬዎች ያሉ ሲሆን የግብርናው ዘርፍ ከአገሪቷ አጠቃላይ ምርት ውስጥ 34 በመቶ ድርሻ አለው።

ቅጽ 1 ቁጥር 43 ነሐሴ 25 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here