የዋልያዎች ቁጥር በመቶዎች እድገት አሳየ

0
1919

በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እና በራስ ዳሽን ተራራ ላይ ብቻ የሚገኘው ብርቅዬው የዱር እንስሳ ዋልያ ከመጥፋት ስጋት በመውጣት ወደ ዘጠኝ መቶ ከፍ አለ።
የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ ከ 15 ዓመት በፊት የዋልያዎቹ ቁጥር ወደ 150 ማሽቆልቆሉን ተከትሎ በአደጋ መዝገብ ውስጥ እንዲገባ አድርጎ የነበረ ቢሆንም በ2010 ከፍተኛ የሚባል የቁጥር እድገት በመታየቱ በድጋሚ የቋሚ ቅርስ መዝገብ ውስጥ እንዲገባ ማድረጉ ይታወሳል።

ፓርኩ በዓለም ቅርስነት ከተመዘገበበት ጊዜ አንስቶ በፓርኩ ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር በማድረግ የዋልያዎቹን ቁጥር ከፍ ለማድረግ ተችሏል ሲሉ በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ባለስልጣን የብሔራዊ ፓርኮች መጠለያና ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ገብረመስቀል ግዛው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ዳይሬከተሩ ጨምረው እንደተናገሩት በ1980ዎቹ መጀመሪያ በሰሜኑ የአገሪቱ አካባቢ በነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት አማካኝነት የዋልያ ቁጥር አሽቆልቆሎ የነበረ ሲሆን ፓርኩን የሚጠብቀው አካልም እንዳልነበረም ተናግረዋል።

በፓርኩ ውስጥ ህገ ወጥ የመሬት ወረራ፤ አደን፣ የቤት እንስሳት ግጦሽ፣ ሽፍታዎች፣ በሰሜን ጎንደር ደባርቅ ወረዳ ውስጥ የሚኖሩ የግጭ መንደር በፓርኩ ውስጥ መኖሪያቸውን ማድረጋቸው ለብርቅዬ እንስሳቱ መመናመን ምክንያት ነው ብለዋል።

ፓርኩ ይዞ ከነበረው 136 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ቦታ ውስጥ መንገድ እና የኤሌክትሪክ ፖሎች በመኖራቸው በፓርኩ ውስጥ ያሉ እንስሳት እንዲመናመኑ አድርጓል። ይህንንም ለመቅረፍ የፓርኩን ስፋት በመጨመር 412 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የተደረገ ሲሆን በውስጡ ያለው መንገድ በውጪ በኩል በተሰራው የአስፓልት መንገድ እና እርሱን ተከትሎም በተተከሉት የኤሌክትሪክ ፖሎች እንዲቀር የተሰራ ሲሆን ይህም መንገድ በቅርቡ ተመርቆ በፓርኩ ውስጥ ያለው መተላለፊያ እንደሚዘጋ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በፓርኩ ውስጥ የሚኖሩ 418 የሚሆኑ የግጭ መንደር ነዋሪዎቹም መንግስት 162 ሚሊየን ብር መድቦ ካሳ እንዲከፈላቸው በማድረግ እንዲወጡ መደረጉን ጨምረው ገልፀዋል። በፓርኩ ውስጥም ብርቅዬ ከሚባሉት እንስሳት ውስጥ ከዋልያ በተጨማሪ 130 ቀይ ቀበሮ፣ 26 ሺህ ጭላዳ ዥንጀሮ እና የሚኒሊክ ድኩላ ይገኙበታል።
‹‹ፓርኩን ከሰው ንክኪ ነጻ ለማድረግም በፓርኩ ጥግ የሰፈሩ ነዋሪዎችን ወደ ሌላ ቦታ ማሸጋገር እና ሙሉ በሙሉ ፓርኩን ከግጦሽ ነፃ የምናደርግ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ከሄኒከን ቢራ ፋብሪካ ጋር ባደረግነው ውል መሰረት የዋልያን ቁጥር ለማሳደግ ሥራ እንሰራለን›› ያሉት ገብረመስቀል ‹‹ሎጎውን የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች ላይም እየሰራን ነው›› ብለዋል።

እ.አ.አ በ1978 ዓ.ም በዩኔስኮ ቋሚ መዝገብ ውስጥ በዓለም ቅርስነት ተመዝግቦ የነበረው የሰሜን ብሔራዊ ፓርክ በውስጡ የተለያዩ ብርቅዬ እንስሳዎችን የያዘ ቢሆንም በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው ዋልያ ብቻ እንደሆነ ይታወቃል። ከጊዜ ወደ ጊዜ የዋልያዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ተመናምኖ ወደ 150 በመውረዱ በ2010 በድጋሚ በቋሚ ቅርስነት ከመመዝቡ በፊት በ1988 ፓርኩ በዩኔስኮ አደጋ መዝገብ ውስጥ እንዲገባ ተደርጎ እንደነበር ይታወሳል።

በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ከደባርቅ ከተማ 32 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኘው የስሜን ብሔራዊ ፓርክ እ..አ.አ በ1966 የተቋቋመ ሲሆን በ1978 በዩኔስኮ ዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል። ፓርኩ ከባህር ወለል በላይ ከ1900-3926 ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል።

ቅጽ 1 ቁጥር 43 ነሐሴ 25 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here