የሲአን አመራሮች ለኹለት ተከፈሉ

0
301
  • ምርጫ ቦርድ ጉዳዩን እየመረመርኩ ነው ብሏል

የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) አመራሮች መካከል በተከሰተው አለመግባባት፣ ንቅናቄው ለኹለት ተከፍሎ ግጭት ውስጥ መግባቱን አዲስ ማለዳ ከፓርቲው አመራሮች ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

በሚሊዮን ቱማቶ (ዶ/ር) የሚመራው ወገን “የሲአን ሕጋዊ አመራር እኔ ነኝ” ያለ ሲሆን፣ ባሳለፍነው ሳምንት መጀመሪያ ነሐሴ 20/2011 የንቅናቄውን የማዕከላዊ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ አካሒዷል። የተካሔደው ስብሰባ ዕውቅና የሌለው ነው በማለት ያወገዘው በዱካሌ ላሚሶ የሚመራው ቡድን በበኩሉ፣ ማዕከላዊ ኮሚቴውን ያካሔዱት አመራሮች በከባድ የሥነ ምግባር ጉድለት ያሰናበትናቸው በመሆናቸው ተቀባይነት የሌለው ሲሉ ስብሰባውን ተቃውመውታል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገረቻቸው የሲአን የድርጅት ጉዳይ ኀላፊና ዋና ጸሐፊ ለገሰ ላንቃሞ፣ በሚሊዮን የተመራው ስብሰባ ሕገወጥ መሆኑን ገልጸዋል። በፓርቲው 104 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ባሉበት ሁኔታ 35 ሰዎች ተሰብስበው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ተደርጓል ተብሎ መነገሩ የንቅናቄውን ሕግ የጣሰ መሆኑን አስታውቀዋል። አንድ ስብሰባ ተቀባይነት የሚኖረው ሃምሳ ሲደመር አንድ ሰው ተሰብስቦ ውሳኔ ሲያሳልፍ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

እነ ሚሊዮን በበኩላቸው፣ ሕጋዊ በመሆናችን ስብሰባውን አካሒደናል፤ ሌሎቹ ንቅናቄውን አይወክሉም፤ ስብሰባውንም ያደረግነው ሕጉን ማዕከል አድርገን ነው ሲሉ ተደምጠዋል። ሰኞ፣ ነሐሴ 20 በጠራው ስብሰባም ለመጭው ብሔራዊ ምርጫ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።

በነሚሊዮን ቶማቶ የሚመራው ቡድን በፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ በተደረገ ምርጫ ተሸንፈው የወጡ መሆናቸውን የሚናገሩት ለገሰ “ሽንፈታቸውን አውቀው መቀመጥ ይገባቸው ነበር” ሲሉ ተናግረዋል። በንቅናቄው አንድ ሰው በምርጫ መወዳደር የሚችለው ለሦስት ጊዜ ብቻ መሆኑን ጠቁመው፣ አሁን ለአራተኛ ጊዜ መወዳደር የሚፈልጉ ሰዎችም አብረው ቅሬታ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ፣ ከኹለቱም ወገኖች የአቤቱታ ማመልከቻ እንደደረሰው አስታውቆ፣ በቅርቡ ጉዳዩን መተዳደሪያ ደንባቸውን በመመርመር ውሳኔውን እንደሚያስታውቅ ገልጿል። የቦርዱ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች አማካሪ ሶልያና ሽመልስ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች የሲአን ብቻ አይደሉም። በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች በውስጣቸው በሚነሱ አለመግባባቶች ሳቢያ ማኅተሜን፣ ሰነዴን፣ ቁልፌን ወሰደ የሚሉ አቤቱታዎች ይዘው እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።

የሲዳማ ክልልን ጥያቄ ከፊት ሆኖ የሚመራው በወልደ አማኑኤል ዱባለ የተመሰረተው እና እስከ ዕለተ ሞታቸው በእሳቸው ሲመራ የነበረው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) በመባል የሚታወቀው ፓርቲ ነው። ይህ ፓርቲ እነ ኦነግ፣ ሕወሓት እና የመሳሰሉት ዘውግ ተኮር ፓርቲዎችን መመስረት ተከትሎ በደርግ ዘመን የተመሰረተ ማርኪሲስት ሌኒኒስት ፓርቲ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 43 ነሐሴ 25 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here